
ከ 5 ሰአት በፊት
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ሠራዊታቸው ጋዛ ውስጥ የሚያካሂደው ዘመቻ ዓላማ “የሐማስን አስተዳደራዊ እና ወታደራዊ አቅም በማንኮታኮት” መደምሰስ ነው በማለት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
መስከረም ወር መጨረሻ ላይ የተጀመረው የጋዛ ጦርነት አምስት ወራት ሞላው። ከ30 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን፣ እስራኤል ደግሞ “ሙሉ ድል ለመቀዳጀት” ወሳን እርምጃ ላይ መሆኗን አሳውቃለች።
ነገር ግን ሐማስ እንዲሁ በቀላሉ የሚደመሰስ ቡድን አይደለም። ምክንያቱም ቡድኑ ከወታደራዊው ባሻገር ፖለቲካዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ነው። ስለዚህ የእስራኤል ሐማስን ሙሉ ለሙሉ የመደምሰስ ግብ ተጨባጭ ወይም ሊሳካ የሚችል ነው?
መሬት ላይ እየሆነ ያለው ምንድን ነው?
እስራኤል ሐማስ በጋዛ ውስጥ ከነበሩት 24 ባታሊዮኖች 18ቱን መደምሰሷን እና “በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ሐማስ ያለውን ወታደራዊ መዋቅር ማፈራረስ አጠናቅቄያለሁ” ብላለች።
ሐማስ 1200 ሰዎችን የገደለበት እና 250 የሚሆኑትን አግቶ በወሰደበት የመስከረም 26ቱ ጥቃት ወቅት 30 ሺህ የሚደርሱ ተዋጊዎች ቡድኑ እንደነበረው የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ይገልጻል።
አስካሁን በተካሄደው ዘመቻም 13,000 ተዋጊዎቹ መገደላቸውን የእስራኤል ጦር ሲገልጽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ በየካቲት መጀመሪያ ላይ ሠራዊታቸው “20 ሺህ ሽብርተኞችን ገድሏል፣ አቁሰሏል ወይም ማርኳል፤ ይህም ማለት ከሐማስ ተዋጊ ኃይል ከግማሽ በላይ ነው” ብለው ነበር።
ነገር ግን ቢቢሲ ይህንን አሃዝ ለማረጋገጥ አልቻለም፤ ለእስራኤል ሠራዊትም እዚህ ቁጥር ላይ እንዴት ሊደርስ እንደቻለ ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
- ኔታኒያሁ ችላ ያሏቸው በተለያዩ አገራት የሚገኙ ሐማስ ሚሊዮኖችን የሚያንቀሳቅስባቸው የገንዘብ ምንጮች1 መጋቢት 2024
- ሚስቱን እና ሦስት ልጆቹን ጨምሮ 103 ዘመዶቹን ያጣው ፍልስጤማዊ አባት27 የካቲት 2024
- የተባበሩት መንግሥታት በጋዛ እና ዩክሬን ጉዳይ የሚወቀሰው ለምን ይሆን? ምንስ ማድረግ ይችላል?25 ጥር 2024
እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ከጋዛ እና ከእስራኤል በኩል የሚወጡት አሃዞች የሚቃረኑ ናቸው። የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ቁጥር እንደሚያመለክተው ከተገደሉት ከ30 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መካከል 9,000 የሚሆኑት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ አዋቂ ወንዶች ናቸው።
የሐማስ ፖለቲካ ቢሮ እስራኤል ገደልኳቸው ያለቻቸውን የተዋጊዎቹን አሃዝ ውድቅ በማድረግ፣ ወታደራዊ ክንፉ በጋዛ ውስጥ በሚገኙ “ሁሉም አካባቢዎች” የሚያካሂዳቸውን ዘመቻዎች “በኃይል” መቀጠሉን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሃሬትዝ የተባለው የእስራኤል ታዋቂ ጋዜጣ ሐማስ የተወሰኑትን ተዋጊ ኃይሎቹን መልሶ ማደራጀት መጀመሩን ዘግቧል።
በእስራኤሉ ሪችማን ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፉ የፀረ ሽብርተኝነት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ጡረተኛዋ የእስራኤል የጦር መኮንን ኮሎኔል ሚሪ ኢይሲን እንደሚሉት የእስራኤል ኃይሎች የሐማስን “አዛዦች ገድለዋል፣ የጦር መሳሪያ ክምችትን ይዘዋል፣ ከመሬት በታች የተዘረጉትን የሽብር መዋቅሮችን አፈራርሰዋል።”
ጄንስ ዲፌንስ ዊክሊ የተባለው የወታደራዊ መጽሔት የመካከለኛው ምሥራቅ አርታኢ የሆነው ጄሬሚ ቢኔ ግን ከመሬት በታች የተገነቡት የሐማስ ዋሻዎች “ቀደም ሲል ከተገመቱት በላይ በርካታ ናቸው” በማለት ሙሉ ለሙሉ ለማውደም እስራኤላውያን “ገና ብዙ ይቀራቸዋል” ይላል።
ይህ ደግሞ በሐማስ እጅ የሚገኙት ታጋቾች በእነዚህ ዋሻዎች ውስጥ ተይዘው ሊሆኑ ይችላል ስለሚባል እርምጃ መወስደን አዳጋች ያደርገዋል በማለት እስራኤል ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃት ይናገራሉ።
ጨምሮም በሰሜናዊ ጋዛ እስራኤል እያካሄደችው ያለው ዘመቻ “ሙሉ ለሙሉ በአንድ ጊዜ የመደምሰስ ሂደት ሳይሆን፣ ማብቂያው የማይታወቅ ቀጣይ ሂደት የሚመስል ሁኔታን ፈጥሯል” ሲሉም ያክላሉ።
እስራኤል በጋዛ በምታካሂደው ዘመቻ ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ እና በዓለም አቀፉ የፍትህ ችሎት ደግሞ የዘር ማጥፋት ክስ እየቀረበባት ቢሆንም ክሱን “የተዛባ ነው” ብላ አጣጥላዋለች።
ኔታኒያሁም አገራቸው የጀመረችውን ዘመቻ ቀጥላ የቀሩትን የሐማስ ተዋጊዎች ማስወገድ አለባት ብለው ያምናሉ።

ርዕዮተ ዓለምን መደምሰስ ይቻላል?
መሪዎቹ እስራኤልን ለማጥፋት ጥሪ ያቀርባሉ በማለት በርካታ ምዕራባውያን አገራት ሐማስን እንደ ሽብርተኛ ቡድን ነው የሚመለከቱት። ነገር ግን በከፊሉ የአረብ ዓለም ደግሞ እንደ ነጻነት እንቅስቃሴ ነው የሚታየው።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ 2006 የተደረገውን ምርጫ አሸንፎ ተቀናቃኙን የፋታህ ቡድንን በኃይል ከጋዛ ሰርጥ በማስወጣት አስካሁን ድረስ ጋዛን ሲያስተዳደር ቆይቷል።
ሐማስ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ የደኅንነት ስጋት አለብን በማለት ጋዛ ሰርጥ በአብዛኛው በአስራኤል በተወሰነ ደረጃ ደግሞ በግብፅ ከበባ ስር ቆይታለች።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጋዛ የሚገኙ የፍልስጤማውያን ቡድኖች በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ሲተኩሱ ቆይተዋል። ለእነዚህም አንዳንድ ጊዜ ምክንያት የሚሆነው በእስራኤል ወረራ ስር በሚገኙት ዌስት ባንክ እና ኢየሩሳሌም ውስጥ ከእስራኤል ኃይሎች ጋር ለሚከሰቱ ግጭቶች ምላሽ በሚል ነው።
“ሐማስ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም፤ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ብቻም አይደለም፤ ሐማስ ርዕዮተ ዓለም ነው” የሚሉት በአውሮፓውያን ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ክፍል የመካከለኛው ምሥራቅ አጥኚ የሆኑት ሁግ ሎቫት ናቸው።
“ይህ ርዕዮተ ዓለም በእርግጠኝነት በእስራኤል ሠራዊት ኃይል የሚጠፋ አይደለም” በማለትም ይናገራሉ።
ሐማስ በእስራኤል ላይ ለሚያካሂደው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚያገኘው ድጋፍ የጎለበተው በተለይ አሁን መሆኑን የሚናገሩት ሎቫት፣ “በፍልስጤማውያን ዘንድ የራሳቸውን አገር ለመመሥረት ያላቸውን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ በፖለቲካዊው መስክ ተስፋ የለም የሚል ስሜት ተፈጥሯል” ይላሉ።
በዌስት ባንክ የአረብ አሜሪካ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶ/ር አምጃድ አቡ ኤል ኢዝ፣ ፍልስጤማውያን ተስፋ የሚሰጥ ነገር ስለማይታያቸው በርካቶች ሐማስን ይደግፋሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በረጅሙ የሥልጣን ዘመናቸው ሁሉ የፍልስጤማውያንን አገር የመመሥረት ሃሳብን ሲቃወሙ ቆይተዋል።
ምክንያታቸውም የደኅንነት ስጋትን እና ሐማስ ለእስራኤል ዕውቅና አለመስጠቱን ነው ይላሉ። በርካታ የፓርቲያቸው እና የቀኝ ክንፍ አጋሮቻቸው ዌስት ባንክን እና ጋዛ ሰርጥን የእስራኤል ግዛት አድርገው ስለሚመለከቱ የፍልስጤም አገር መሆን ተቀባይነት የለውም።
ፒስ ናው የተባለው የእስራኤል የመብት ቡድን እንደሚለው ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቤቶች እስራኤላውያን በሰፈሩባቸው የዌስት ባንክ ክፍሎች ውስጥ እንዲገነቡ በእስራኤል መንግሥት ይሁንታን አግኝተዋል።
በዌስት ባንክ የእስራኤል ኃይሎች እና እስራኤላውያን ሰፋሪዎች 81 ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 507 ፍልስጤማውያንን መገደላቸውን በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ተደርጓል። ይህም ባለፉት 20 ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ ካጋጠሙት ሁሉ ከፍተኛ ነው ተብሏል።
በእስራኤላውያኑ በኩልም 36 በዌስት ባንክ ባሉ ፍልስጤማውያን ጥቃት መገደላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ አመልክቷል።
በፍልስጤማውያን ዘንድ ዌስት ባንክን የሚያስተዳድረው ፋታህ ፓርቲ ላይ እስራኤል ከምትፈጽመው ወረራ አንጻር ተስፋ መቁረጥ ይታያል። የፍልስጤም አስተዳደር በሙስና የተባላሸ እና ደካማ መሆኑንም በምክንያትነት ያነሳሉ።
ከመስከረም ማብቂያው የሐማስ ጥቃት በፊት በጋዛ ሰርጥ በከበባ ስር ያሉት ፍልስጤማውያን “በትልቅ እስር ቤት ውስጥ” ያሉ ያህል ነበር የሚሰማቸው ይላሉ ዶ/ር አቡ ኤል ኢዝ፣ በዌስት ባንክ ያሉት ፍልስጤማውያን ደግሞ በአይሁድ ሰፋሪዎች ጥቃት፣ በተወሰደባቸው መሬት እና በሥራ እጦት ብስጭት አላቸው።
“ወረራው፣ ጭፍጨፋው እና ግድያው እስካለ ድረስ በርካታ ፍልስጤማውያን ተስፋን ስለሚፈልጉ ሐማስ የሚለውን መስማታቸው አይቀሬ ነው” ይላሉ መምህሩ።

ለሐማስ ጥቃት የፍልስጤማውያን ምላሽ?
ምንም እንኳን ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ቢሆንም፣ በፍልስጤማውያን ዘንድ ሐማስ ያለው ድጋፍ መጨመሩን አንድ የሕዝብ አስተያየት መለኪያ አመልክቷል።
አስተያየቱን የሰበሰበው እና መቀመጫውን ዌስት ባንክ ያደረገው የፍልስጤማውያን ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ኻሊል ሺካኪ እንዳሉት፣ በጦርነቱ ጊዜ የሐማስ ድጋፍ በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ ቁጥር ጨምሯል።
የሕዝብ አስተያየቱ የተሰበሰበው እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም አድርገው ፍልስጤማውያን ሴቶች እና ህጻንት ከእስራኤል እስር ቤቶች በተለቀቁበት ባለፈው ኅዳር ወር ነው።
ይህም በአንዳንድ ፍልስጤማውያን ዘንድ ሐማስ የተከተለው የኃይል እንቅስቃሴ የፍልስጤማውያንን ፍላጎት በማሳካቱ ረገድ “በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ” እንደሆነ እንዲመለከቱት እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
የሰፋሪዎች ጥቃት እና የፍልስጤም አስተዳደር በጋዛ ውስጥ ለሚካሄደው ጦርነት የሰጠው ምላሽ ደካማ መሆን የፈጠረው ተስፋ መቁረጥ የዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን ለሐማስ ያላቸውን ድጋፍ እንዲጨምር አድርጎታል ይላሉ ዶ/ር ሺካኪ።
ዋነኛው የጦርነት ቦታ በሆነው ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ግን ለሐማስ የታየው የድጋፍ ጭማሪ የጎላ አይደለም። ነገር ግን በግዛቲቱ ውስጥ የሐማስ የሕዝብ ድጋፍ ከ38 በመቶ ወደ 42 በመቶ ከፍ ብሏል።
በተጨማሪም ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ የፈጸመው ጥቃትን ትክክለኛነት በተመለከተ ከጋዛ ይልቅ በዌስት ባንክ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቷል። በጋዛ 57 በመቶው ጥቃቱን ሲደግፉ በዌስት ባንክ ግን 82 በመቶ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ዶ/ር ሺካኪ በጦርነቱ ዋጋ እየከፈሉ ያሉት የጋዛ ነዋሪዎች ከዌስት ባንክ ይልቅ የሐማስን እርምጃ ከሙሉ ልብ አልደገፉትም ብለዋል። አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጋዛ የነበረው የቢቢሲ ዘጋቢም ነዋሪዎች በሐማስ ላይ ቁጣቸውን የመግለጽ ምልክቶች የነበሩ ቢሆንም፣ በይፋ በሐማስ ላይ ተቃውሞ ለማሰማት አዳጋች መሆኑን ጠቅሷል።

አዲስ ፀረ እስራኤል ትውልድ እየመጣ ነው?
ዶ/ር አቡ ኤል ኢዝ እንደሚያምኑት በአሁኑ ወቀት በጋዛ ያሉ በርካታ ወጣት ፍልስጤማውያን “በእስራኤል እና በወረራዋ ጥላቻ ተሞልተዋል።”
“ቤተሰባቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ እናቶቻቸውን. . . እህት ወንድሞቻቸውን ስላጡ፤ ይህንን ለመበቀል ቀጣዩ ትውልድ ይህንን ወታደራዊ ቡድን ይቀላቀላል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።
ኮሎኔል ኤይሲን ደግሞ ለሐማስ የበለጠ ድጋፍ ይፈጠራል በሚል ስጋት ምክንያት ወታደራዊ ግብን ከማሳካት ወደ ኋላ እንዲባል ሊያደርግ አይገባም ይላሉ።
“ዘግናኝ፣ ከልክ ያለፈ ጭፍጫ” ያሉትን በመስከረም መጨረሻ ላይ ሐማስ የፈጸመውን ጥቃት በመጥቀስም “ቀድሞውንም ጽንፈኛ ስለሆኑ፣ ምላሻችን በቀዳሚነት የሐማስን አቅም መደምሰስ ነው። ይህም ርዕዮተ ዓለማቸውን አሁን ካሉበት የበለጠ የከፋ አያደርገውም” ብለዋል።
ዶ/ር ሺካኪ በበኩላቸው “ከትልቅ ጦርነት በኋላ ሰላም ከመጣ ወጣቶች የግድ ጠመንጃ እንዲያነሱ የሚገፋቸው ምክንያት አይኖርም” የሚል እምነት አላቸው።
ከዚህ ጦርነት በኋላ ምን ተስፋ አለ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ለጋዛ ያላቸውን ዕቅድ አሳውቀዋል። በዚህም እስራኤል “ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ” የምትሆነውን የጋዛን የደኅንነት ኃላፊነት ላልተወሰነ ጊዜ ተቆጣጥራ፣ ፀረ እስራኤል ከሆኑ ቡድኖች ጋር ግንኙነት የሌላቸው ፍልስጤማውያን ጋዛን ያስተዳድራሉ።
“ወደፊትም ቢሆን ሐማስ አንዳች ነገር ማድረጉ አይቀርም” የሚሉት ኮሎኔል ኤይሲን፣ ነገር ግን እስራኤል እያካሄደችው ባለው ዘመቻ “ስጋት የሚሆኑትን አብዛኞቹን መደምሰስ ትችላለች” የሚል እምነት አላቸው።
“በሃቅ ሐማስን በማዳከም ገለል ማድረግ የሚፈልግ ካለ፣ ይህ ሊሆን የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ዘላቂ ፖለቲካዊ በር በመክፈት ነው” የሚሉት ደግሞ ሎቫት ናቸው።
ነገር ግን የፍልስጤማውያን አገር ተመሥርቶ ሁለቱም አገራት ጎን ለጎን ወደሚቀመጡበት መፍትሄ የሚወስደው መንገድ ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ ላይ አይደለም።
ኔታኒያሁ በቅርቡ በኤክስ ገጻቸው ላይ “ከዮርዳኖስ በስተምዕራብ ባለው አካባቢ እስራኤል በሚኖራት ይዞታ ላይ በሙሉ የደኅንነት ቁጥጥሯ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይሆንም፣ ይህም የፍልስጤም አገር ከመመሥረት ተቃራኒ ነው” ብለው ጽፈዋል።
ይህ ደግሞ የእስራኤል ዋነኛ አጋር ከሆነችው ከአሜሪካ አቋም ጋር የማይስማማ ነው። ለእስራኤል እና ለፍልስጤም ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚገኘው “ወደ ፍልስጤም አገርነት የሚያደርሰውን ጨምሮ ቀጠናዊ አካሄድን በመከተል ብቻ ነው” የሚል አቋም አሜሪካ አላት።
የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር እስራኤል በጋዛ ላይ ማብቂያ የሌለው ወረራ አድርጋ መቀጠል እንደሌለባት አጽንኦት ሰጥቶ አሳስቧል።
አሁን ካለው ሁኔታ በተለየ ሌላ አማራጭ ማግኘት ካልተቻለ፣ በአካባቢው ወደፊት እየተባባሰ የሚሄድ ተጨባጭ የግጭት ስጋት መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
የወታደራዊ መጽሄቱ የመካከለኛው ምሥራቅ አርታኢ ጄሬሚ ቢኔ እስራኤል ሙሉ ድል የምትቀዳጅበት ሁኔታ አይታየውም፤ “እስራኤል ሐማስን በከፍተኛ ደረጃ ልታዳክመው ትችላለች፤ ነገር ግን ዋናው ነገር ከዚያ በኋላስ ቡድኑ መልሶ እንዳያንሰራራ ልታደርግ ትችላለች? የሚለው ነው” ይላል።