
ከ 4 ሰአት በፊት
በፕላስቲክ በተሰራ አነስተኛ ጀልባ ተጭነው በሜዲትሪኒያን ባሕር ላይ ሲጓዙ ከነበሩ ስደተኞች መካከል ቢያንስ 60 ያህሉ መሞታቸውን በሕይወት የተረፉ ተሳፋሪዎች ተናገሩ።
በጀልባው ላይ ከነበሩት ስደተኞች ውስጥ 25ቱ ሊተርፉ የቻሉት ኤስ.ኦ.ኤስ ሜዲትራኒያን የተባለው የሰብዓዊ ቡድን የሚያንቀሳቅሳት “ኦሽን ቫይኪንግ” ወደ ተሰኘች መርከብ በመዘዋወራቸው ነው።
ስደተኞቹ ዛዊያ ከተባለው የሊቢያ የባሕር ዳርቻ ከተነሱ ቀናት መቆጠራቸውን ለሰብዓዊ ቡድኑ ተናግረዋል።
ጀልባው ጉዞ ከጀመረ ከሦስት ቀናት በኋላ ሞተሩ በመበላሸቱ ስደተኞቹ ያለ ምግብ እና ውሃ በባሕር ላይ ሲንሳፈፉ ቆይተዋል።
በሕይወት የተረፉት ስደተኞች እንደሚናገሩት ከሞቱት ተሳፋሪዎች ውስጥ ሴቶች እና ቢያንስ አንድ ህጻን ልጅ ይገኙበታል። ስደተኞቹ ሕይወታቸው ያለፈው በውሃ ጥማት እና በረሀብ እንጂ በመስመጥ አደጋ እንዳልሆነ ታምኗል።
ስደተኞቹን የታደገችው “ኦሽን ቫይኪንግ” ላይ የነበሩት የሰብአዊ ቡድን አባላት ጀልባውን በአጉሊ መነጽር የተመለከቱት ረቡዕ ዕለት ነው። ከጣልያን የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች ጋር በመሆን የታንኳዋን ተሳፋሪዎች ማዘዋወራቸውን ኤስ.ኦ.ኤስ ሜዲትራኒያን ገልጿል።
- የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ከእስር ተፈቱ14 መጋቢት 2024
- በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ታላላቅ ውድድሮች ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብስክሌት ብሔራዊ ቡድን ፈተናከ 5 ሰአት በፊት
- እስራኤል ሐማስን ‘ለመደምሰስ’ እያካሄደች ያለው ዘመቻ እንዳሰበችው እየተሳካላት ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
የተረፉት ስደተኞች “በጣም ደካማ በሆነ የጤና ሁኔታ” ውስጥ እንደነበሩ የሰብዓዊ ቡድኑ ጠቅሷል። ራሳቸውን ስተው እና አስጊ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሁለት ተሳፋሪዎች ለተጨማሪ ህክምና በሄሊኮፕተር ወደ ሲሲሊ መወሰዳቸውንም ቡድኑ አክሏል።
ቀሪዎቹ 23 ተሳፋሪዎች ከሌሎች ሁለት ጀልባዎች ከተገኙ 200 ተጨማሪ ስደተኞች ጋር ኦሽን ቫይኪንግ መርከብ ላይ ናቸው። መርከቧ ወደ ጣልያኑ አንኮና ወደብ እየተጓዘች ቢሆንም ለመድረስ አራት ቀናት ይፈጅባታል። በዚህም ምክንያት ቡድኑ ለደህንነት ሲባል ቀረብ ወዳለ ወደብ ለመጓዝ እየጠየቁ ነው።
በባሕሩ ላይ የምትገኘው የኤስ.ኦ.ኤስ ሜዲትራኒያን ቃል አቀባይ፤ “ሰዎች ጉዞ ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል። ባለቤቱን እና የአንድ ዓመት ተኩል እድሜ ያለው ህጻን ልጁን ያጣ ሰው አግኝቻለሁ። ህጻኑ ህይወቱ ያለፈው በመጀመሪያው ቀን ሲሆን እናትየው ደግሞ በአራተኛው ቀን ሞታለች። የመጡት ከሴኔጋል ሲሆን ሊቢያ ውስጥ ሁለት ዓመት ቆይተዋል” ብላለች።
ፍሮንትኤክስ የተሰኘው የአውሮፓ ሕብረት የድንበር ኤጀንሲ ከ50 በላይ ሰዎችን የጫነ ጀልባ በሊቢያ የባሕር ጠረፍ አካባቢ ከተመለከተ በኋላ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ለቢቢሲ ተናግሯል። ይሁንና ጀልባው አሁን በኦሽን ቫይኪንግ መርከብ ላይ የተጫነችው ትሁን አትሁን አልገለጸም።