
ከ 5 ሰአት በፊት
አፍሪካ ውስጥ አሉ ከሚባሉ የብስክሌት ውድድሮች ቁንጮ ነው የሚባለው ቱር ደ ሩዋንዳ በቅርቡ ተጠናቋል።
በዚህ ውድድር በዓለማችን አሉ የሚባሉ እንደ እስራኤል ፕሪሚዬር እና ዩኤኢ ያሉ ክለቦችን ጨምሮ በርካታ ብሔራዊ ቡድኖች ተሳትፈዋል።
በውድድሩ ከተሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብስክሌት ቡድን ነው።
ከየካቲት 10 አስከ 17 በዋና መዲናዋ ኪጋሊ እና በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄደው ውድድ 740 ኪሎ ሜትሮችን ሸፍኗል።
አብዛኞቹ በውድድሩ የተሳተፉ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ሩዋንዳ በማቅናት ልምምድ ማድረግ የጀመሩት ቢያንስ ከውድድሩ አንድ ሳምንት በፊት ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ በድን ኪጋሊ የደረሰው ግን የካቲት 8 አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ነው።
የብሔራዊ ቡድኑን አሠልጣኝ ጨምሮ ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው የሄዱ አምስት ተወዳዳሪዎች ፌዴሬሽኑ ዝግጅት አልነበረውም ሲሉ ይወቅሳሉ።
አልፎም በቂ ትጥቅ እና የብስክሌት አቅርቦት ችግር እንዳለ ቢያማርሩም፤ ፌዴሬሽኑ ግን በዚህ አይስማማም። ለመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ ሩዋንዳ ምን ገጠመው? ምንስ ውጤት አመጣ?
“መሳተፋችን አንድ ነገር ነው”
በአውሮፓውያኑ 2023 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሻምፒዮን የነበረው ብዛይ ተስፉን ጨምሮ አምስት ተወዳዳሪዎች ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው በውድድሩ ተሳትፈዋል።
ከአምስቱ ተወዳዳሪዎች መካከል የድሬ ዳዋው አሚር ጃፋር ጣሀ በራሱ ወጪ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ወደ ኪጋሊ በማቅናት ከዓለም አቀፉ የብስክሌት ማኅበር ጋር ልምምድ እያደረገ ነው የሰነበተው።
ብሔራዊው ቡድኑን ከወከሉት አምስት ብስክሌተኞች 7 ቀናት የፈጀውን ውድድር ማጠናቀቅ የቻለውም አሚር ብቻ ነው።
የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ዮሴፍ አለማየሁ “ስንመጣ ምንም ዝግጅት አላደረግንም” ይላሉ።
“አንድ ብስክሌተኛ ምን ዓይነት አቋም ላይ ነው ያለው የሚለውን ማወቅ አለብን። ዝግጅት ማድረግ አለብን። አንድ ብስክሌተኛ ወደ ሌላ አገር ሄዶ ለመወዳደር ቢያንስ ለ4 ወራት መዘጋጀት አለበት። እኛ ምንም ዝግጅት ሳይኖር ነው የምንሳተፈው” ሲሉ ከውድድሩ በፊት ቡድናቸው የነበረበትን አቋም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለው ኢንስትራክተር ዮሴፍ “አሚር ብቻ ነው ያጠናቀቀው። አራቱ አቋርጠዋል። ይህ አለመሥራታችንን፣ አለመዘጋጀታችንን ያመለክታል” ይላሉ።
ጋና በነበረው የአፍሪካ ሻምፒዮን የገጠማቸውን የሚያስታውሱት አሠልጣኙ፣ ለሩዋንዳው ውድድርም ቀድሞ የመዘጋጀት ዕድሉ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።
- “በብስክሌት ውድድር በአፍሪካ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ እፈልጋለሁ” ፡ ኪያ ሮጎሮ21 የካቲት 2024
- ከዩኒቨርስቲ ትምህርት ብስክሌትን የመረጠው ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ18 የካቲት 2024
- ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች መሮጥ ይቻላል? ኢትዮጵያውያን ወይስ ኬንያውያን ታሪክ ይሠራሉ?4 መጋቢት 2024
“ቀድመን ተገናኝተን የምንተዋወቅበት ጊዜ ስላልነበረን የቡድን ሥራ መሥራት አንችልም። ጋና ሄደን የሆነውም ይህ ነው።”
የኢትዮጵያ ሻምፒዮኑ ብዛይ ተስፉም በአሠልጣኙ ሐሳብ ይስማማል። የብስክሌት እና የትጥቅ ችግር እንዳለ የሚናገረው ብዛይ፣ የክለቡ ንብረት በሆነ ብስክሌት ነው የተወዳደረው።
“በሚቀጥለው ይህ ችግር ይቀረፋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” የሚለው ብዛይ በቱር ደ ሩዋንዳ መሳተፍ በራሱ ትልቅ ነገር እንደሆነ ያምናል።
ኢንስትራክተር ዮሴፍ ብስክሌተኞቹ የተቻላቸውን ጥረት እንዳደረጉ፤ ነገር ግን ችግሩ የብስክሌት ፌዴሬሽን እንደሆነ ይናገራሉ።
“ብስክሌተኞች ምን ማድረግ ይችላሉ? ሥራቸው ሲመረጡ መምጣት ነው። ዋናው ጥፋት የፌዴሬሽኑ ነው። ዋናው ነገር ለአገር ማሰቡ ነው። ለአገር ከታሰበ ቀድሞ መዘጋጀት ይቻላል። ቀድሞ መመልመል ይቻላል። ስፖርቱን እያጣነው፤ እየጠፋ ነው።”
በተለይ “ሊገባኝ አልቻለም” የሚሉት ጉዳይ የውድድሩ አዘጋጆች የሆቴል ወጪን የሚሸፍኑ ሆነው ሳለ “ቲኬት ተገዝቶ ቀድመን መጥተን ልምምድ ማድረግ አለመቻላችን ነው” ይላሉ።
“ሆቴል ተዘጋጅቶልናል፤ ምግብ አለ። የአውሮፕላን ቲኬት ሸፍነውልን ቢያንስ አንድ ሳምንት ቀደም ብለን ብንመጣ መዘጋጀት እንችል ነበር። አርፍደን ነው የመጣነው። አገሪቱን አናውቃትም” በማለት ቅድመ ዝግጅት አለመኖሩ በቡድኑ ውጤት ላይ የነበረውን ተጽእኖ ያመሳሉ።

የትጥቅ ችግር
በቅርቡ የብስክሌት ጫማውን የሰቀለው ታዋቂው ብስክሌተኛ ፅጋቡ ግርማይን ጨምሮ፣ ሦስት ጊዜ ቱር ደ ፍራንስ አሸናፊው እንግሊዛዊው ክሪስ ፍሩም እና ኤርትራዊው መርሐዊ ቅዱስ በውድድሩ ተሳትፈዋል።
የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን በክለብ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ አክሊሉ አረፋይነ ምርጥ ወጣት ብስክሌተኛ ተብሎ ተመርጧል።
ፅጋቡ ግርማይ እና ሌላኛው የድሬ ዳዋ ብስክሌተኛ ኪያ ሮጎራ ዓለም አቀፉ የብስክሌት ማኅበርን (ዩሲአይ) ወክለው ተሳትፈዋል።
ፅጋቡን ጨምሮ ኢንስትራክተር ዮሴፍ እና ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ፌዴሬሽኑ የራሱ ብስክሌት እና ትጥቅ የለውም፤ ይህ ደግሞ ጉዳት ነው ይላሉ።
ኢንስትራክተሩ እንደሚሉት ብሔራዊ ቡድኑን ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች ቢኖሩ የብስክሌት እና የትጥቅ ችግርን መፍታት ይቻል ነበር።
“ሁሌም ለብስክሌት ውድድር ስንሄድ የሚቀርብልን ምክንያት በጀት የለንም የሚል ነው” የሚሉት አሠልጣኙ “ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መጥፋቱ” ግራ ያጋባቸዋል።
“የአገራት ሻምፒዮኖች በማሊያቸው ይለያሉ። ለምሳሌ የኤርትራውን ሻምፒዮን በማሊያው መለየት ትችላለህ። የእኛ ልጅ [ብዛይ ተስፉ] ይህ ማሊያ አልነበረውም” የሚሉት ኢንስትራክተር ዮሴፍ መምጣታቸውን አንኳ እርግጠኛ የሆኑት ውድድሩ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ነበር።
ቢቢሲ በውድድሩ ስፍራ እንደታዘበው አብዛኞቹ ብሔራዊ ቡድኖች እና ክለቦች ከአንድም ሁለት ዓይነት ለተለያዩ ውድድሮች የሚሆኑ ብስክሌቶች ይዘው ነበር ሩዋንዳ የተገኙት።
“እኛ ሸራ የሚባለውን ያረጀ ብስክሌት ነው የምንጠቀመው። ዲስክ የሚባለው ብስክሌት ቢሆን ኖሮ ቁልቁለት ስንወርድ አይከብደንም ነበር። በፈጣሪ ድጋፍ ልጆቻችን ምንም ሳይጎዱ ተጠናቀቀ እንጂ ሸራ ብስክሌት አደጋ አለው። ዲስክ ብስክሌት ከየት ያመጣሉ” ይላሉ አሠልጣኙ።
ኢንስትራክተር ዮሴፍ ብሔራዊ ቡድኑ ስፖንሰር ማጣቱ እጅግ ያሳስባቸዋል። ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች አሉ ግን አልተሠራበትም ይላሉ።
“ስፖንሰር ያስፈልገናል። ከማን እናንሳለን? ትልቅ አገር ነን። በቀጣይ ማፈር የለብንም። አሁን የመጣነው ባለፈው ዓመት ተጠርተን በመቅረታችን እና ከደገምነው ሁለተኛ ስለማንጠራ ነው። ነገር ግን ለመሳተፍ መምጣት አንፈልግም።”
ሌላው ቢቢሲ በውድድሩ ስፍራ የተመለከተው ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተወዳዳሪዎች እንደሌሎቹ አቻዎቻቸው በቂ የሆነ ኃይል ሰጪ ምግብ እንዳልቀረበላቸው ነው።
በብስክሌት ውድድር ‘ፊዲንግ ዞን’ የሚባለው ብስክሌተኞች ውድድር ላይ ሳሉ ኃይል ሰጪ ምግቦች እና መጠጦች የሚወስዱበት ሥፍራ ነው።
የነበረን አቅም በቂ አልነበረም የሚሉት አሠልጣኙ “እኛ ሙዝ እና ቸኮሌት ነው የያዝነው። ነገር ግን ብስክሌተኞች ጄል፣ ባር. . .እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ይፈልጋሉ። ውድድር ላይ እያለን ሌሎች ቡድኖች ደግፈውናል። ዩሲአይ እና ዩኤኢ ኃይል ሰጪ ምግብ ሲሰጡን ነበር” ይላሉ።

ፌዴሬሽኑ ምን ይላል?
ጉምቱው ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ፅጋቡ ግርማይ የብስክሌት ስፖርት ገንዘብ የሚጠይቅ እንደሆነ ጠቁሞ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን “አቅም የለውም” ይላል።
“ብስክሌት እንደ ሩጫ አይደለም። ፋይናንስ ይጠይቃል። ቁሳቁስ ለመግዛት ዶላር ይጠይቃል። ጫማው፣ ብስክሌቱ. . . ውድ ነው። ፌዴሬሽኑም አቅም የለውም። ይህ ችግር በእኔ ጊዜም ነበረ፤ አሁንም አለ።”
ፅጋቡ እንደሚለው የፌዴሬሽኑ ትልቁ ችግር “አንድ ሰው ተሹሞ ብዙም ሳይቆይ ጥሎ መሄዱ ነው።”
አንድ ሰው ወደ ፌዴሬሽኑ ይመጣና ሦስት አራት ዓመት ሠርቶ ይሄዳል። ከዜሮ ጀምሮ ስፖርቱን እያወቀው ሲመጣ ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳል። እንደገና አዲስ ይመጣል። የሚመጣውም ሰው እንደዚያው ስፖርቱን መላመድ ሲጀምር ይለቃል” ይላል ፅጋቡ።
ይህ ሁኔታ ሳይስተካከል በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ አዳዲስ ብቅ የሚሉ ብስክሌተኞችን ወደኋላ እንዳያስቀራቸው እና የአገሪቱንም የብስክሌት ስፖርት የበለጠ እንዳይሆዳው ፅጋቡ ስጋት አለው።
“እኔ የምመክረው ወጣት ስፖርተኞች ይህ ሊበግራቸው እንደማይገባ ነው። ችግሩ ላይ ካተኮሩ ወደኋላ ያስቀራቸዋል። በእኔ ጊዜ የነበረው ችግር አሁንም አለ። ነገር ግን ልጆች እየወጡ ነው። ፌዴሬሽኑ ጥሩ ስለሆነ አሊያም መሬት ያለው ሥርዓት የተስተካከለ ስለሆነ አይደለም። በራሳቸው ጥረት ነው። አሁን የሚመጡ ወጣት ልጆችም ይህን ማድረግ አለባቸው።”
የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም ወልደአብ የበጀት እጥረት እና የስፖንሰር አለመኖር እንዳለ ቢስማሙም፣ ሩዋንዳ ላይ ለነበረው ጉዳይ ፌዴሬሽኑ ተጠያቂ አይደለም ይላሉ።
የሩዋንዳው ውድድር ከቲኬት በቀር ሙሉ ወጪ በአዘጋጆች እንደተሸፈነ ኃላፊው ይናገራሉ።
አቶ ፍፁም የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አንድ ብስክሌት እንደሌለው አምነው፤ ብስክሌተኞች ለውድድር ሲሄዱ የራሳቸውን አሊያም የክለብ ብስክሌት ይዘው እንደሚሄዱ ያስረዳሉ።
“የብስክሌት ዋጋ ቀድሞም ከ200 ሺህ ብር በላይ ነበር፤ አሁን ደግሞ ጨምሯል” በማለትም ብስክሌተኞች የራሳቸውን ብስክሌት ይዘው መሄዳቸው “ይህ በየትኛውም ዓለም ያለ ነው” ባይ ናቸው።
ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ብስክሌቶች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ እና ለክለቦች እንዲቀርቡ ለማድረግ “እየሠራን ነው” ይላሉ።
አክለውም ስፖንሰር ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነገር ግን “አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት የብስክሌት ውድድሮችን ለማድረግ አልቻልንም” ሲሉ ፌዴሬሽኑ ያለበትን ፈተና ያስረዳሉ።
ኢንስትራክተር ዮሴፍ በሚቀጥለው ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቱር ደ ሩዋንዳ ሲሳተፍ ብዙ ነገሮች ተቀይረው ማየት ይሻሉ።
“ዕድሉ ቢሰጠን ውጤት እናመጣለን። ብንሠራበት ውጤታማ እንሆናለን። አንድም ጊዜ ሦስት አራት ወር ተዘጋጅተን ተወዳድረን አናውቅም። የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ለውጥ የለም።
“ከዚህ በኋላ አንድ ዓመት አለን። ቀላል አይደለም። ልንሠራበት ይገባል” ሲሉ ለቀጣይ ዓመት ውድድር ከወዲሁ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን እና ከተዘጋጁ ውጤት እንደሚያመጡ ከወዲሁ ተስፋ አድርገዋል።