
ከ 1 ሰአት በፊት
የአል ሻባብ ታጣቂዎች በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ቤተ መንግሥት አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሆቴል ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የደኅንነት ምንጮች እና የዐይን እማኞች ተናገሩ።
አልሻባብ በሆቴሉ ላይ በፈጸመው ጥቃት ከባድ ፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጥ የተሰማ ሲሆን፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዳልቀረ ተዘግቧል።
እስላማዊው ታጣቂ ቡድን ሳይል በተባለው እና በሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት በሚዘወተረው ሆቴል ላይ ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
አልሻባብ በአውሮፓውያኑ 2019 ላይ ተመሳሳይ ጥቃት በሆቴሉ ላይ ፈጽሞ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።
በሆቴሉ ውስጥ ፍንዳታ እና የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን የተናገሩ የዐይን እማኞች፣ ታጣቂዎቹ በሆቴሉ ውስጥ መሆናቸውን ለሮይተርስ ዜና ወኪል ገልጸዋል።
ለአልሻባብ ቅርበት ያለው የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው በጥቃቱ አራት የሶማሊያ ፓርላማ አባላት ቆስለዋል። ነገር ግን መንግሥት በዚህ ላይ አስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
አልሻባብ ቀደም ሲል ተዋጊዎቹ ሆቴሉን መቆጣጠራቸውን እና እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
ከፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚኖረው ፋራህ አሊ ለሮይተርስ እንደተናገረው “መጀመሪያ ከባድ ፍንዳታ ሰማን፣ ከዚያም የጠመንጃ ተኩስ ተከተለ። የተኩስ ልውውጥ ስላለ ታጣቂዎቹ ሆቴሉ ውስጥ መሆናቸውን ተረድተናል” ብሏል።
አንድ የደኅንነት መኮንን ለፈረሳይ ዜና ወኪል – ኤኤፍፒ እንደተናገረው “በርካታ ታጣቂዎች የሆቴሉን የመከላከያ አጥር በፈንጂ አውድመው ወደ ሆቴሉ ህንጻ ገብተዋል” ብሏል።
- “ሕዝብን በድሮን መትተን አናውቅም” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ10 መጋቢት 2024
- በሶማሊያ የአይኤስ አባላት የሆኑ 6 ሞሮኳውያን ሞት፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ እስር ተፈረደባቸው2 መጋቢት 2024
- በሶማሊያ ለደኅንነት ሲባል የዋና ከተማዋ ነዋሪዎች ማስክ እንዳያደርጉ ተከለከለ15 የካቲት 2024
በሆቴሉ አጥር ላይ ተንጠላጥሎ ያመለጠው ሐሰን ኑር “ስለደረሰ ጉዳት ባላውቅም ጥቃቱ በተጀመረበት ጊዜ ሆቴሉ ውስጥ በርካታ ሰዎች ነበሩ” ብሏል።
ሌላ የዐይን እማኝ ደግሞ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን በከፈቱበት በደቂቃዎች ውስጥ ፖሊሶች ወደ ሆቴሉ ደርሰው የተኩስ ልውውጥ መጀመሩን ተናግሯል።
ከአልሻባብ ጋር ግንኙነት ያለው አንድ ድረ ገጽ በጥቃቱ ቢያንስ አራት የሶማሊያ መንግሥት የፓርላማ አባላት እና የመንግሥት ቃል አቀባይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።
የሶማሊያ መንግሥት በታጣቂው ቡድን ላይ እያካሄደ ባለው የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በአልሻባብ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መቀነስ አሳይተው ነበር።
አልሻባብ በአሁኑ ጊዜ በደቡብ እና በማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ የሚገኙ ሰፊ የአገሪቱ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው እስላማዊው ቡድን በተባበሩት መንግሥታት በሚደገፈው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ላለፉት 20 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ከባድ የሽምቅ ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አልሻባብ ሞቃዲሾ ውስጥ ከቤተ መንግሥታቸው አቅራቢያ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ሐሙስ ዕለት ከወታደራዊ ባለሥልጣናት ጋር ምክክር አድርገው ነበር።
በዚህ ውይይት ላይ ዋነኛ አጀንዳ የነበረው አልሻባብ ከመንግሥት ኃይሎች ላይ ነጥቆ የተቆጣጠራቸውን ግዛቶች ለማስመለስ የሚያስችል ዕቅድ ለማውጣት እንደነበረ የሶማሊያ የዜና አገልግሎት ሶና ዘግቧል።
ከሶማሊያ በተጨማሪ በርካታ አገራት አልሻባብን በሽብር ቡድንነት የፈረጁት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እና በርካታ የአካባቢው አገራት እንዲሁም አሜሪካ ቡድኑን ለመዋጋት ሠራዊታቸውን በሶማሊያ ማሰማራታቸው ይታወቃል።
የአልሻባብ ተዋጊዎች በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎችን በተደጋጋሚ ዒላማ በማድረግ ይታወቃሉ። አሁን ሳይል ሆቴል ላይ የተፈጸመው ጥቃትም ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት ቡድኑ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ በሚገኘው ቪላ ራይስ ሆቴል ላይ ጥቃት ፈጽሞ ቢያንስ 14 ሰዎችን ሲገድል፣ ከዚያ በፊት ከሦስት ዓመት ቀደም ብሎ በኪስማዮው አሳሴይ ሆቴል ላይ በፈጸመው ጥቃት በርካታ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ቢያንስ 26 ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል።