አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ)
የምስሉ መግለጫ,አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ)፡ ፎቶ ከፋይል

14 መጋቢት 2024

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ከእስር መፈታታቸውን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከስድስት ዓመት በፊት ነሐሴ 21/2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው አስካሁን በእስር ላይ የቆዩት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ከእስር የተለቀቁት ዐቃቤ ሕግ ክሱን በማንሳቱ መሆኑን ጠበቃቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጠበቃ እና የሕግ አማካሪው እስክንድር ገዛኸኝ እንደተናገሩት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክሳቸው ተነስቶ የተለቀቁት ዛሬ መጋቢት 5/2016 ዓ.ም. መሆኑን አመልክተዋል።

ከአቶ አብዲ በተጨማሪም በተመሳሳይ በእሳቸው የክስ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩ የሌሎችም ተከሳሾች ክስ ተቋርጦ መለቀቃቸውን ጠበቃው ተናግረዋል።

ጠበቃ እና የሕግ አማካሪው አቶ እስክንድር እንደሚሉት ዐቃቤ ሕግ ባለው ሥልጣን መሠረት የክስ ማቋረጫውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ አቶ አብዲ ከመፈታታቸው ውጪ ለጊዜው የደረሳቸው ዝርዝር ማብራሪያ እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“አሁን ማረጋገጥ የምችለው አቶ አብዲ ዛሬ [ሐሙስ] ከሰዓት በኋላ ከማረሚያ ቤት መፈታታቸውን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ስላቀረበው ጥያቄ የደረሰን ነገር የለም” በማለት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከእስር መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው ከዓመታት በፊት ጀምሮ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ሲመሩ የነበሩት አቶ አብዲ፣ በክልሉ ውስጥ ከተፈጸሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ግድያዎች እና የመንግሥት ሀብት ብክነት ጋር ስማቸው ሲነሳ ቆይቷል።

በቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር ላይ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከልም በ2010 ሰኔ እና ሐምሌ ወራት ውስጥ “በሶማሌ ክልል የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ በማሰብ ‘ሄጎ’ በሚል ስያሜ የሚታወቅ ወጣቶች ቡድን አደራጅተዋል” የሚል ይገኝበታል።

በወቅቱ በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው፣ ንብረት እና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።

ዐቃቤ ሕግም ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ በተከሰተው ግጭት ምክንያትም 59 ሰዎች መገደላቸውን፣ ከ250 በላይ መቁሰላቸውን እንዲሁም በመንግሥት፣ በግል እና በሃይማኖት ተቋማት ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን ገልጿል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የምስክሮች ቃልን የመረመረው ፍርድ ቤት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) እና ሌሎች ተከሳሽ የክልሉ የቀድሞ ባለሥልጣናት ክሳቸውን እንዲከላከሉ ወስኖ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ አቶ አብዲ እና ሌሎች ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮችን ከኅዳር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለፍርድ ቤቱ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ጠበቃቸውም በሚቀጥለው ሰኞ መጋቢት 9/2016 ዓ.ም. በዚህ ሂደት ላይ የክርክር ማቆሚያ በጽሁፍ እንዲያርቡ ታዘው እየተዘጋጁ ሳለ አቶ አብዲ ከእስር መለቀቃቸውን ገልጸዋል።

የአቶ አብዲ ጠበቃ አቶ እስክንድር ገዛኽኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዐቃቤ ሕግ በቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እና አብረዋቸው በተከሰሱት ግለሰቦች ላይ ያቀረበውን ክስ በማንሳቱ ከስድስት ዓመት ገደማ እስር በኋላ ከእስር ወጥተዋል ብለዋል።