ክንፈ ዳኘው

ከ 4 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ መንግሥት የፍትህ ሚኒስቴር በእነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መዝገብ ቀርበው የነበሩ ክሶች ለሕዝብ ጥቅም ሲባል እንዲቋረጡ መወሰኑን አስታወቀ።

በተመሳሳይ በቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) መዝገብ የነበሩ ክሶች እንዲቋረጡ መደረጋቸውም ይፋ ተደርጓል።

በቀድሞ ርዕሰ መስተዳደር ላይ ተመስርቶ የነበረው ክስ መቋረጡ ከተገለጸ በኋላ ከእስር መፈታታቸውን ጠበቃቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በአቶ አብዲ መሐመድ ኡመር የክስ መዝገብ በ1ኛ የሕገ-መንግሥትና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት የክርክር ሂደት ላይ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

በእነ ሜ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መዝገብ ስር ያሉ ተከሳሾች ደግሞ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሙስና ወንጀል ክስ ክርክር ሲካሄድበት የነበረ ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር ለዘላቂ የሕዝብ ጥቅም ሲባል እነዚህ የክስ ሂደቶች እንዲቋረጡ መወሰኑን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ዘግቧል።

ነገር ግን ክሶቹ አንዲቋረጡ የተሰጠው “ለሕዝብ ጥቅም” የሚለው ምክንያት ምን እንደሆነ የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ላይ ክስ መስርቶ የነበረው በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩት በነበረው የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከተፈጸሙ ግዢዎች ጋር በተያያዘ የሙስና ወንጀል ነው።

ሜቴክ ግዢ የፈጸመባቸው ሆቴሎች እንዲሁም የተለያዩ መሳሪዎች ግዢዎች የተካሄዱት ከተቋሙ የግዢ መመሪያ እና ከሕጋዊ አሠራር ውጪ መሆኑ በክስ መዝገቡ ላይ ተጠቅሶ ነበር።

በዚህ ዓይነት መልኩ ግዢ ተፈጽሞባቸዋል ከተባሉት መካከል አንዱ ግዙፍ የጭነት መርከብ ሲሆን እና ሌሎች ከፍተና የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ መሳሪያዎች መሆናቸው ተገልጾ ነበር።

በዚህም ሳቢያ ሜቴክ “ከሥልጣኑ አልፎ ተያያዥነት በሌለው የትራንስፖርት ዘርፍ ለማሰማራት በመወሰን፣ ያለ ኮርፖሬሽኑ የግዢ መመሪያ መርከብ በመግዛት፣ ያለጨረታ መርከቦቹ አንዲጠገኑ በማድረግ” ኪሳራ እንደደረሰ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አመልክቶ ነበር።

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ፤ በእነዚህ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ታኅሣሥ 2011 ዓ.ም. ሲሆን ላለፉት አምስት ዓመታት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ቆይቷል።