March 15, 2024 – Konjit Sitotaw

የአሜሪካ የላይኛው ምክር ቤት አባላት የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቁ

የአሜሪካ የላይኛው ምክር ቤት አባላት ሴናተር ቲና ስሚዝ፣ ጄፍ ሜርክሌይ፣ ኤሚ ክሎቡቻር፣ ጆን ሂክንሎፐር፣ ክሪስ ቫን ሆለን፣ እና ቲም ኬይን፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ እንዲሱጡ ጠይቀዋል።

ሴናተሮቹ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን እና የአሜሪካ አለማቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር በኢትዮጵያ በጦርነት እና ግጭት ምክንያት ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ቀጣይነት ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ በፃፉት ደብዳቤ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ያለው የእርስ በርስ ግጭትና የአየር ንብረት መዛባት በሀገሪቱ ያለውን አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ አባብሶታል ያሉት የምክር ቤት አባላቱ 4.4 ሚሊዮን ሰዎች በአገር ውስጥ እንደተፈናቀሉና ኢትዮጵያ ወደ 942,ሺ የሚጠጉ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞችን አስጠልላ እንደምትገኝ ገልፀዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ 20.1 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ሴናተሮቹ የጠቆሙ ሲሆን በኢትዮጵያ በ2024 የሰብዓዊ እርዳታ እቅድ መሰረት ለዜጎች ድጋፍ ለማድረግ 3.24 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገውና ለ6.6 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ ለማድረግ 500 ሚሊዮን ዶላር በአስቸኳይ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሴናተሮቹ የባይደን አስተዳደር በሀገሪቱ የሚደረገውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማሳደግ ከሌሎች ለጋሽ አገራትና የተራድኦ ድርጅቶች ጋር እንዲተባበር የጠየቁ ሲሆን በተጨማሪም በሀገሪቱ ሰብአዊ ፍጡራን ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ግጭቶችን ለማስወገድ ግፊት እንዲደረግም ጠይቀዋል።