
ከ 6 ሰአት በፊት
የኬንያ መንግሥት የገቢዎች ባለሥልጣን አዳዲስ ሠራተኞችን ለመቅጠር የእርግዝና እና የኤችአይቪ/ኤድስ ምርመራ አድርጎ አመልካቾችን ውድቅ ማድረጉ ጥያቄ አስነሳበት።
የኬንያ የፓርላማ አባላት እነዚህ ምርመራ አድርገው አይቀጠሩም የተባሉት አመልካቾችን ጉዳይ በተመለከተ ምርመራ እንዲከፈትም አዘዋል።
ተቋሙ በበኩሉ ባለፈው ዓመት ምርመራውን ካደረገ በኋላ 133 አመልካቾችን ከውድድሩ መሰረዙን አስታውቋል።
እነዚህ በግብር ሰብሳቢ አስከባሪነት ለመሰማራት ሊቀጠሩ የነበሩ አመልካቾች፣ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ በሚዘጋጁበትም ወቅት ነው ምርመራው የተደረገው።
የኬንያ ሕግ በጤና ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ የሚደረግ የቅጥር አድልዎን ይከለክላል።
አዳዲስ ምልምሎች የህክምና ምርመራ እንዲያደርጉ ተገደዋል የሚለው ዜና ሐሙስ ዕለት በኬንያ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ሲገለጽ አባላቱን አማስደንገጡም በላይ አስቆጥቷል።
“በምልመላው ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰት እንደተፈጸመ ምንም ጥርጥር የለውም” ሲሉ በፓርላማው የብሔራዊ ትስስር እና የእኩልነት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አዳን ሐጂ ገልጸዋል።
“ከ20 በላይ የሕገ መንግሥቱን አንቀጾችን እና የሰብዓዊ መብት ሕጎችን እንደጣሳችሁ ተቀበሉ” ሲሉም የተቋሙን ከፍተኛ ባለሥልጣናት አሳስበዋል።
እነዚህን ምርመራዎችን ደግፈው የተናገሩት የገቢዎች ባለሥልጣን ኮሚሽነር ሪስፓህ ሲሚሁ በበኩላቸው ወታደራዊ ሥልጠናዎችን የሚያካሂደው የኬንያ የመከላከያ ኃይል ለ1 ሺህ 406 ምልምሎች ሥልጠና መስጠቱን አስታውሰው “ሁልጊዜም ቢሆን ለአዲስ ተመልማዮች የኤችአይቪ/ኤድስ እና የእርግዝና ምርመራዎች ይደረጋሉ” ብለዋል።
- ታግተው የነበሩ አምስት የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች መገደላቸው ተነገረ15 መጋቢት 2024
- ባሕር ሲያቋርጥ የሞተው ኢትዮጵያዊ ሚስት እና ልጆቹ የፈረንሳይ መንግሥትን ከሰሱከ 7 ሰአት በፊት
- ቦይንግ በ787 ድሪምላይነር አውሮፕላኑ ላይ ያጋጠመ ክስተትን ተከትሎ ምርመራ ጀመረከ 6 ሰአት በፊት
“የገቢዎች ባለሥልጣን ወታደራዊ ሥልጠናዎችን ስለሚያካሂድ ይህም በሥልጠና ወቅት ጥሩ የአካል ብቃት እንዲኖራቸው ይጠይቃል” በማለት ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።
“ይህ አሰራር ለተመልማዮቹ በጤና እና ደኅንነት ላይ የተመሠረተ የሥልጠና ዝግጁነትን እንዲኖር ለማድረግ እንዲሁም በተመልማዮች ላይ የሚደርሱ ስጋቶችን ለመቀነስ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።
የገቢዎች ባለሥልጣን ኮሚሽነር ጄኔራል ሃምፍሬይ ዋትታንጋ ለኮሚቴው የ133ቱ ተመልማዮች ውጤት በምሥጢር የተያዘ መሆኑን ገልጸው፣ ኤችአይቪ/ኤድስን መሠረት በማድረግ ተቋሙ በማንኛውም ሠራተኛ ላይ መድልዎ እንደማይፈጽም ተናግረዋል።
ሕጉ የጤና ሁኔታን መሠረት ባደረገ የሥራ ምልመላ መድልዎን በሚከለክልበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሥራ አመልካቾቹ ለምን ውድቅ ተደረጉ በሚልም የፓርላማ አባላቱ ጥያቄ አንስተዋል።
የፓርላማ አባላቱ የገቢዎች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ያቀረቡትን ማብራሪያ ውድቅ በማድረግም ሁሉም ወታደራዊ ሥልጠናዎች የኤችአይቪ ምርመራ አያስፈልጋቸውም ብለዋል። እንዲሁም የወታደሮች ምልመላ እንዴት ይካሄዳል የሚለውም ጥያቄ ተነስቷል።
የፓርላማ አባላቱ ተመልማዮቹ መድልዎ ገጥሟቸዋል በተባለው ጉዳይ ላይ ሙሉ ምርመራ ለመክፈትም ቃል ገብተዋል።