
ከ 6 ሰአት በፊት
ላታም የተባለው አየር መንገድ ንብረት በሆነ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ላይ ያለ ቁልፍ በድንገት በመነካቱ በመንገደኞች ላይ ቀላል ጉዳት ካጋጠመ በኋላ ምርመራ ተጀመረ።
በዚህ ክስተት ምክንያትም የምርመራው ውጤት አስኪታወቅ ድረስ አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ የ787 ድሪምላይነር አውሮፕላን አብራሪዎች በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለውን የመቀመጫቸውን ሁኔታ እንዲፈትሹ አሳስቧል።
ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው የአውሮፕላኑ የበረረ አስተናጋጅ ባልታሰበ ሁኔታ የተጫነችው ቁልፍ የአብራሪውን መቀመጫ ወደ አውሮፕላኑ መቆጣጠሪያ አስፈንጥሮት፣ የአውሮፕላኑ አፍንጫም ቁልቁል ወደ መሬት እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል።
ከአውስትራሊያ ወደ ኒው ዚላንድ በበረራ ላይ በነበረው በዚህ አውሮፕላን ላይ ባጋጠመው በዚህ ክስትት ምክንያት በርካታ መንገደኞች ከመቀመጫቸው ተፈናጥረው ከአውሮፕላኑ ጣራ ጋር መጋጨታቸው ተነግሯል።
ከቀናት በፊት የላታም አየር መንገድ ንብረት በሆነው በረራ ላይ በጋጣመው በዚህ ድንገተኛ ሁኔታ ምክንያት 50 በሚደርሱ ተሳታፋሪዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።
- የቦይንግን ምሥጢር በማጋለጡ በጀግንነት የሚወደሰው ግለሰብ ሞቶ መገኘት ያስከተለው ጥያቄ14 መጋቢት 2024
- ቦይንግ ሰራሹ አውሮፕላን የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ በረራ ላይ የተገነጠለው ብሎኖች ጎድለውት ነው ተባለ7 የካቲት 2024
- በረራ ላይ ሳሉ የተኙ ሁለት የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ አብራሪዎች ምርመራ ተከፈተባቸው11 መጋቢት 2024
የክስተቱን ምክንያት ለማወቅም ምርመራ የተጀመረ ሲሆን፣ ቦይንግ የተመሳሳይ አውሮፕላኖች አብራሪዎች ከጉዞ በፊት የወንበራቸውን ሁኔታ እንዲፈትሹ መክሯል።
አንድ ተሳፋሪ ክስተቱን በተመለከተ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በርካታ ሰዎች በጭንቅላታቸው ላይ የመጋጨት ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን እና በአውሮፕላኑ ኮርኒስ ላይም መሰበር ማጋጠሙን ገልጿል።
የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሠራተኞች ከክስተቱ በኋላ እንዳሳወቁት በተፈጠረው ድንገተኛ ሁኔታ ከተጎዱት መካከል አንድ ሰው በከባድ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።
ቦይንግ “በአውሮፕላኑ ላይ ስላጋጠመው ሁኔታ የሚገኝ ውጤትን ምርመራውን የሚያደርጉት ባለሥልጣናት የሚያሳውቁ ይሆናል” በማለት ዝርዝር ሁኔታ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ጨምሮም ለጥንቃቄ ሲባል የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች አብራሪዎች ከዚህ በፊት በወጣው የአብራሪዎች መቀመጫዎችን የመቆጣጠሪያ ቁልፎችን በተመለከተ በወጣው መመሪያ መሠረት ፍተሻ እንዲያደርጉ አሳስበቧል።
ክስተቱ ያጋጠመው የቺሊ እና የብራዚል ንብረት የሆነው አየር መንገድ ላታም በበኩሉ “እየተካሄደ ያለውን ምርመራ ለመደገፍ ከባለሥልጣናት ጋር በትብብር እየሠራ” መሆኑን ገልጿል።
አውሮፕላኑ ከኒው ዚላንዷ ኦክላንድ ከተማ ወደ ቺሊ ዋና ከተማ ሳንቲያጎ እንዲበር ፕሮግራም ተይዞለት የነበረ ሲሆን፣ ባጋጠመው ሁኔታ ምክንያት ጉዞው ተሰርዞ ወደ መጪው ማክሰኞ ተላልፏል።
ይህ ድንገተኛ ክስተት በቦይንግ አውሮፕላን ላይ ያጋጠመው ባለፈው ጥር ወር አንድ የቦይንግ አውሮፕላን በሩ ተገንጥሎ በተደረገ ምርመራ በሩ ከታሰረባቸው ብሎኖች መካከል የተወሰኑት አለመኖራቸው ከታወቀ በኋላ ነው።
በተጨማሪም ከጥቂት ዓመታት በፊት በቦይን የምርት ደኅንነት ደረጃ ላይ ጥያቄዎችን በማንሳት የድርጅቱን ምሥጢር ያጋለጠው የቦይንግ ሠራተኛ በዚህ ሳምንት አሜሪካ ውስጥ ሞቶ መገኘቱ ይታወቃል።