
Ayele Anawete
ዞዝ አምባ ጊዮርጊስ
ዞዝ አምባ ጊዮርጊስ ከጎንደር ከተማ በአርባያ በኩል 130 ኪ.ሜ ጎሀላ ከተባለች ከተማ የአንድ ስዓት ተኩል የእግር ጉዞ በኃላ በደን የተሸፈነ ኮርበታማ ስፍራ ይገኛል ።
የዞዝ አምባ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ በምስራቅ ላሊበላ ፣ሰቆጣንና የተከዜን ተፋሰስ ይዞ ፣በምዕራብ ወገራን፣ጎንደር ዙሪያና ደንቀዝን ፣ በስሜን የስሜን ተራሮችን በምዕራብ ደግሞ እብናትን በርቀት ለመቃኘት የሚያስችል ቦታ ነው ።
የዞዝ አምባ ቤተክርስቲያኑ አንድ አለት ተፈልፍሎ አናቱ ብቻ ከዋናው ቋጥኝ ጋር ተያይዞ የተሰራ ነው ።የተሰራዉም በቅዱስ ላሊበላ ሲሆን ገዳሙ የተመሰረተው በአፄ ይስሃቅ (1414-1429) ዘመነ መንግስት አባ አብሳዱ በተባሉ አባት ነው ።
ቤተክርስቲያኑ ዉስጥ ቅኔ ማህሌት ፣ቅድስትና መቅደስ በግምት 40 ሜትር ጥልቀት ያለው ፀበልና “የሙሽራ ቤት ” ተብሎ የሚጠራ የክርስትና ማንሻ ክፍል አለው ። ከቤተክርስቲያኑ ጣሪያ ጋር የተያያዙ በደንብ የተወቀሩ 8 ያህል አምዶች ቆመዋል።
መስኮቶች በመስቀል ቅርፅ የተሰሩ ናቸው ።በዚህ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ዉስጥ በርካታ የብራና መፅሐፍትና ንዋየ ቅዱሳት ይገኛሉ ።
የግራኝ አህመድ ስጦታዎች ናቸዉ የሚባሉ 3 የክብር በትሮች የግራኝ መቀመጫና የአርበኛ ፅሁፍ ያለበት ደወል፣ ራስ ወሌ ብጡል በስጦታ ያበረከቱት የብር መስቀል ከቅርሶች ትቂቶች ናቸው ።
በዞዝ አምባ ጊዮርጊስ በዓመት 2 ታላላቅ ሀይማኖታዊ ከብረ ብዓላት የሚከብሩ ሲሆን 1ኛዉ ታህሳስ 12 ሌላኛው ደግሞ ሚያዚያ 23 ቀን ነው ። ወደ ዞዝ አምባ በሚደረግ ጉዞ ስውሩ ቤተ ሣሙኤል በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ጅምር የዋሻ ውስጥ ቤተክርስቲያን ፣ ደንቀዝ ልዩ ስሙ ጎመንጌ በተባለ ስፍራ የሚገኘው የአፄ ሱስንዮስ ቤተመንግሥት ፍርስራሽ ፣ ግራኝ አህመድ የሞተበት የሚባለው “ግራኝ በር” እንዲሁም ጎንድ ተክለሀይማኖት በእግር መንገድ የሚጎበኙ ታሪካዊ ስፍራዎች ናቸው ።
