
ዜና በትግራይ ክልል በጦርነት ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች ብድር የሚከፍሉበት ጊዜ እንዲራዘምላቸው ጠየቁ
ቀን: March 17, 2024
በትግራይ ክልል በጦርነቱ ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች ከጦርነቱ በኋላ ምንም ዓይነት የሥራ እንቅስቃሴ ማድረግ ስላልቻሉ፣ ከተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡
የትግራይ ክልል ባለሀብቶች ጥያቄውን ያቀረቡት ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ማክሮኢኮኖሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
የትግራይ ክልል የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ኃይሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በትግራይ ክልል ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች ተገቢውን ብድር ከባንኮች እንዲያገኙ በማድረግ ያለባቸውን ብድር የሚከፍሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡
በጦርነት ወቅት መንግሥት ባንክ በአዋጅ እንዲዘጋ ካደረገ በኋላ በክልሉ ጦርነት እንጂ ምንም ዓይነት የሥራ እንቅስቃሴ እንዳልነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህንን በመረዳትና ያሉትን ችግሮች ቁጭ ብሎ በማጤን ባለሀብቶቹ የተበደሩትን ብድር ብቻ እንዲከፍሉ መደረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ባለሀብቶቹ ከተበደሩት ብድር ውጪ ወለድ ክፈሉ መባሉ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ወለዱን ጨምሮ የብድር ክፍያ የጊዜ ገደብና ሌሎች ነገሮች እንዲቀሩ ለብሔራዊ ባንክና ለገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ ማስገባታቸውን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ባለሀብቶች ብድር እንዲከፍሉ ትዕዛዝ መቀመጡ ገልጸው፣ ጊዜውም በጣም አጭር በመሆኑ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ እንዲጨመርላቸው መጠየቃቸውን አብራርተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመራው ኮሚቴ የወለዱ መጠን ሙሉ ለሙሉ እንዲተው፣ እንዲሁም ባለሀብቶቹ ያለባቸውን ብድር ለመክፈል ሌላ ብድር እንዲመቻችላቸው ጥያቄ መቅረቡንና በቀጣይ ሳምንትም ምላሽ እንዲሰጥበት መስማማት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት ንብረታቸው የወደመባቸው ኢንቨስተሮች ምንም ዓይነት ድጋፍ ባለማግኘታቸው ከውድድር ሊወጡ መቻላቸውን፣ የክልሉ የኢንቨስመትንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል መኮንን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ኢንቨስተሮች ከመንግሥት ድጋፍ ሳይደረግላቸው የተበደራችሁትን ብድር ክፈሉ መባሉ አግባብ አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ኢንቨስተሮች የተበደሩትን ብድር እንዲከፍሉ ጊዜ በተራዘመ ቁጥር ወለዱ እየጨመረ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
በዚህ የተነሳ አብዛኛው ባለሀብት ጭንቀት ውስጥ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት የባለሀብቶችን ችግር በመረዳት ያለባቸውን ወለድ ማስቀረት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በፊት በተደጋገሚ የመንግሥትን በር በማንኳኳት ባለሀብቱ ያለበትን ዕዳ እንዲሰረዝለት ኮሚሽኑ ጥያቄ ማቅረቡን፣ ነገር ግን ከጥያቄ ውጪ ምን ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች የብድር ሁኔታን በተመለከተ ማብራሪያ ለመጠየቅ ሪፖርተር ባንኮችን ለመጠየቅ በተደጋገሚ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡