የዩናይትድ አየር መንገድ አውሮፕላን

ከ 5 ሰአት በፊት

በአሜሪካዋ ኦሬገን ግዛት አንድ የዩናይትድ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ አውሮፕላን የአውሮፕላን አካል ጠፍቶ ሳለ ያለምንም ጉዳት ማረፉ ተሰምቷል።

የበረራ ቁጥሩ 433 የሆነው አውሮፕላን ከሳን ፍራንሲስኮ ተነስቶ ሮግ ቫሊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሥፍራው ሰዓት አቆጣጠር 5፡30 አርፏል።

25 ዓመት የሞላው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን 139 መንገደኞች እና 6 የበረራ ሠራተኞችን ጭኖ ነበር።

የአውሮፕላኑ አካል እንደጠፋ ሳይታወቅ አውሮፕላኑ ቢያርፍም ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም።

ቦይንግ የተሰኘው ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ደኅንነታቸው ያልተጠበቀ አውሮፕላኖች እያመረተ ነው ተብሎ ወቀሳ እየዘነበበት ይገኛል።

የሮግ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነባር መኮንን የሆኑት አምበር ጁድ፤ አውሮፕላኑ በሰላም ማረፉን ተናግረው የአውሮፕላኑ አካል መጥፋቱ የታወቀው ከበረራ በኋላ በተደረገ ምርመራ ነው ብለዋል።

“አንድ በአንድ መርምረን፤ አስፈላጊ ጥገናዎችን ካደረግን በኋላ አውሮፕላኑ ወደ አገልግሎት ይመለሳል” ብለዋል መኮንኗ።

አክለው “ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ለማጣራት ጠበቅ ያለ ምርመራ እናካሂዳለን” ብለዋል።

የጠፋው የአውሮፕላኑ አካል ከማረፊያ ጎማው አጠገብ ያለ ‘ፊዩዝላጅ ፓነል’ የተባለው ከአውሮፕላኑ ሆድ ሥር የሚገኝ ውጫዊ አካል መሆኑን ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተሠራጩ ምስሎች አሳይተዋል።

በአየር ማረፊያው የነበረው መጪና ተጓዥ በረራዎች ተቋርጠው ስብርባሪ ከተገኘ ተብሎ ፍለጋ ቢካሄድም ምንም ሊገኝ አልቻለም።

የ Twitter ይዘትን ይለፉት

ይዘቱን Twitter ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በTwitter. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የTwitter ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።Accept and continue

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ Twitter ይዘት መጨረሻ

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሸን ባለሥልጣን እንዴት የአውሮፕላኑ አካል ሊጠፋ እንደቻለ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን ገልጧል።

ቦይንግ፤ በተለይ ባፈለው ጥር 737 ማክስ-9 የተሰኘው አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ አንደኛው በር ተገንጥሎ መውደቁን ተከትሎ ከባድ ትችት እየደረሰበት ነው።

የአላስካ ኤርላይንስ ንብረት የሆነው የበረራ ቁጥሩ 1282 አውሮፕላን በግራ በኩል ክፍት ሆኖ መብረር ስለማይችል ተመልሶ ለማረፍ ተገዷል።

ይህንን በተመለከተ ለአሜሪካ ሕግ አውጭዎች ቃላቸውን የሰጡት የፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊ ማይክ ዊቴከር ማክስ 737 ላይ ምርመራ ካደረጉ በኋላ “የቦይንግ የጥራት ሥርዓት ተቀባይነት የሌለው እና ተጨማሪ ምርመራ የሚሻ ነው”ብለዋል።

የክስተቱ የመጀመሪያ ዙር ምርመራ ውጤት እንደሚጠቁመው የአውሮፕላኑን በር አጥብቀው መያዝ የሚገባቸው አራት ብሎኖች አልተገጠሙም።

የባለሥልጣኑ ኃላፊ ዊቴከር፤ ቦይንግ በፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሕግ መሠረት የማይተዳደር ከሆነ ለማንኛውም አደጋ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል።

ባለፈው ሰኞ ከአውስትራሊያ ወደ ኒው ዚላንድ እየተጓዘ የነበረ 787-9 ድሪምላይነር አውሮፕላን ያለማስጠንቀቂያ ድንገት ወደታች ሲወርድ ቀበቶ ያላደረጉ መንገደኞች ወደ መተላለፊያውና ወደ ጣራው ተገጫጭተው ወድቀው 50 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ለዚህ ክስተት ምላሽ የሰጠው ቦይንግ አንድ የበረራ አስተናጋጅ በስኅተት የተጫነችው ቁልፍ የአብራሪዎቹን ወንበር ወደፊት ገፍቶታል፤ ይህ ደግሞ አውሮፕላኑ አፍንጫውን ዝቅር አድርጎ እንዲበር ያደርጋል ብሏል።

ባለሙያዎች፤ ምንም እንኳ ቦይንግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ክስተቶች ገጥመውት ወቀሳ ቢደርስበትም የመንገደኞች አውሮፕላን አሁንም ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት ዓይነት ነው ይላሉ።