ሄይቲ

ከ 6 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወንበዴ ቡድኖች እየታመሰች ካለችው ሄይቲ ዜጎችን በልዩ በረራ እንደሚያስወጣ አስታወቀ።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ መውጫ አጥተው በሄይቲ ለሚገኙ አሜሪካውያን ከመዲናዋ 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ከምትገኘው ካፕ-ሄይሺየን ከተማ በረራ እንደሚደረግ ለዜጎቹ መልዕክት አስተላልፏል።

ሚኒስቴሩ በመልዕክቱ በረራው የሚደረገው በካፕ-ሄይሺየን ያለው የጸጥታ ሁኔታ የተረጋጋ ከሆነ ብቻ መሆኑን እና አውሮፕላኑን መሳፈር የሚችሉት የአሜሪካ ዜጎች ብቻ መሆናቸውን አስታውቋል።

አሜሪካ ቀደም ሲል መሠረታዊ ግልጋሎት ላይ ያልተሰማሩ የኤምባሲ ሠራተኞችን አስወጥታለች።

የደቀቀ የምጣሄ ሃብት ባላት ሄይቲ የተቀሰቀሰው አመጽ ተባብሶ ቀጥሎ የአገሪቱ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።

ፖሊስ በወንበዴ ቡድኖች የተያዙ የመዲናዋን አካባቢዎች መልሶ ለመቆጣጠር እና ጂሚ ቼሪዚዬር የተባለ የወንበዴ ቡድን መሪ ለመያዝ ጥረት እያደረገ ነው።

ትናንት ቅዳሜ የፖሊስ ቃል አቀባይ ሊዮኔል ላዛሬ ፖሊስ ባካሄደው ዘመቻ በርካታ “ሽፍቶች” ተገድለዋል ብለዋል።

ፖሊስ፤ ከሆነ ባርቢኪው በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ጂሚ የሚመራው የወንበዴ ቡድን ላይ በተካሄደ ሌላ ዘመቻ መንገዶችን ማስከፈቱን እና ጦር መሳሪያዎችን መያዙን ጨምሮ አስታውቋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የሄይቲ መንግሥት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ፖሊስ በሌላ ዘመቻ የመዲናዋን ዋነኛ ወደብ ከወንበዴ ቡድኖች ለማጽዳት ዘመቻ አካሂዶ ነበር። አሁን ላይ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ይህ የፖሊስ ዘመቻ ሳይሳካ መቅረቱን እየገለጹ ነው።

በአሁኑ ወቅት በርካታ አገራት በሄይቲ ያላቸውን ኤምባሲዎቻቸውን እየዘጉ ዜጎቻቸውን በአየር እያስወጡ ይገኛሉ።

ሄይቲን እያመሱ ካሉ የወንበዴ መሪዎች መካከል ቀዳሚው ባርቢኪው የሚባለው ግለሰብ ነው። ይህ ግለሰብ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኤሪኤል ሄነሪ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

ከሳምንታት ጫና በኋላ ባሳለፍነው ማክሰኞ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ የተገደዱት ሄንሪ እስካሁን ወደ አገራቸው ሄይቲ እንዲመለሱ አልተፈቀደላቸውም።

በላቲን አሜሪካ የምትገኘው ሄይቲ 11.5 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሲሆን ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ ጋር ትዋሰናለች።

ባለፉት ዓመታት አለመረጋጋቶች፣ አምባገነናዊ ስርዓት እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሄይቲ ሰላም እና አለመረጋጋት እንዲርቃት የሚያደርጉ ምክንያቶች ሆነው ቆይተዋል።

እአአ 2010 ላይ በሄይቲ አጋጥሞ የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ200ሺህ በላይ ሰዎችን ከመግደሉ በላይ የአገሪቱን መሠረተ ልማቶች በከፍተኛ ደረጃ አውድሞ ነበር።