የካባና ዲዛይን መሥራች ሰምሃል
የምስሉ መግለጫ,የካባና ዲዛይን መሥራች ሰምሃል ጉዕሽ

ከ 6 ሰአት በፊት

ካባና ዲዛይን ከመደበኛ ሥራ ውጪ በትርፍ ጊዜ ከሚሠራ የጊዜ ማሳለፊያ ‘ሆቢ’ የተወለደ እና ጥቂት ለማይባሉ ሰዎችም ሥራ እና ተስፋን ያስገኘ የሥራ ፈጠራ ሙከራ ነው።

የሰመሃል ጉዕሽ የትርፍ ጊዜ ሥራ የነበረው ካባና ዲዛይን አሁን ከ100 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ተፈላጊ የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ለውጭ ገበያ ከማቅረቡ በተጨማሪ፣ ጥቂት ለማይባሉ ሴት ባለሙያዎች ዕድልን የፈጠረ ነው።

አዲስ አበባ ያደገችው ሰምሃል ካባና ሌዘርን ከሰባት ዓመታት በፊት ከመጀመሯ በፊት በዩኒቨርሲቲ የኪነ-ህንጻ (አርክቴክቸር) ትምህርት በምታጠናበት ወቅት ከቆዳ ተረፈ ምርቶች የእጅ ጌጥ ትሠራ ነበር።

ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች በኋላ በአርክቴክቸር ድርጅት ተቀጠረች፤ ጎን ለጎን ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር የጀመረቻቸው ሦስት ቢዝነሶች እንደምትፈልገው ሳይሳኩላት ቀርተዋል፤ ነገር ግን ሙከራዋን አላቋረጠችም።

ሰምሃል በትርፍ ጊዜዋ ከቆዳ የሚሠሩ ቦርሳዎችን በማዘጋጀት ላይ በማዋል ካባና ሌዘርን ስትጀምር የቀጠረቻት የመጀመሪያዋ ሴት ሕይወት ላይ የነበረውን አዎንታዊ ተጽእኖን ስታይ የሙሉ ጊዜ ሥራዋ ለማድረግ ወሰነች።

“ስጀምር የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ(Hobby) ነበር፤ ነገር ግን ቋሚ ሠራተኞች መቅጠር እና ደሞዝ መክፈል ስጀምር ከመካከላቸው አንዷ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለታናሽ እህቷ ትምህርት መክፈል ጀመረች። እሷም ‘ቋሚ ሠራተኛ ሆኜ የተከፈለኝ የመጀመሪያ ደሞዝ ይህ ነው’ ትለኝ ነበር” ስትል ታስታውሰዋለች።

ሰምሃል መጀመሪያ የቀጠረቻት ሴት በዘርፉ የነበራት ውሱን ችሎታ እና እውቀት ቢሆንም፣ ቆዳ መቁረጥ እና መስፋትን በማስተማር ሕይወቷ ሲሻሻል፣ በራስ የመተማመን ስሜቷን ሲጎለብት ካየች በኋላ “ከዚህ በኋላ ይህ ሥራ የእኔ ብቻ አይደለም አልኩኝ፤ አምስት ሰዎችን ስቀጥር ደግሞ ከመደበኛ ሥራዬ መልቀቂያ አስገባሁ” ትላለች።

ሌላው ለዚህ ሥራዋ ምክንያት የሆናት ነገር በሕይወታቸው ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ፣ በተለይ ልጆቻቸውን ለብቻ የሚያሳድጉ እና ከስደት የተመሱ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ነጻነት የሚያገኙበትን እና የኑሮ መሰናክሎቻቸውን መስበር የሚል እምነት መሆኑን ለቢቢሲ ገልጻለች።

በዚህ መስክ ኢንቨስት በማድረግ ትርፍ ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎችን ሕይወት መቀየር እንደ ማኅበራዊ ኃላፊነት እና ቁርጠኝነትም ትወስደዋለች።

የኩባንያው ድረ-ገጽ እንደሚያመለክተው በተመሰረተበት በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ትልቅ ለውጥ በማስመዝገብ፣ ለደንበኞች ከፍተኛ ጥራት ያለው የኢትዮጵያ የቆዳ ፋሽን ምርቶችን የሚያገኙበት ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር የዓለም ገበያን መቀላቀል ችሏል።

የካባና ሰራተኞች 80% ሴቶች መሆናቸው ድርጅቱ ይገልጻል
የምስሉ መግለጫ,የካባና ሠራተኞች 80 በመቶው ሴቶች ናቸው

ከሴት ልጅ ለሴት ልጅ

ሀና፣ ሰላም፣ ደስታ፣ በረከት፣ ሚክኤላ . . . በካባና ዲዛይን ለሚያመርታቸው የተለያዩ ዋሌት ቦርሳዎች፣ ትልቅ እና ታንሽ የእጅ ቦርሳዎች እና ለሌሎችም ምርቶች የተሰጣቸው መጠሪያ ስሞች ናቸው።

ሰምሃል ቦርሳዎቹ በኩባንያው ውስጥ ባሉ ምርጥ ሠራተኞች ስም እንዲሰየሙ ማድረግ ከምርቶቹ በስተጀርባ ያሉትን ሠራተኞች ክብር ለመስጠት ታስቦ የሚደረግ እንደሆነ ታስረዳለች።

“እነዚህ በሕይወታቸው ጀግኖች ናቸው፤ ስለዚህ እኔ ማድረግ የምችለው ቢያንስ ስማቸውን የምርቶቻችን መጠሪያ እንዲሆን ማድረግ ነው” ስትል ለሠራተኞቿ ያላትን አድናቆት ትገልጻለች።

በዚህ ዘርፍ ውስጥ የምትፈጥረው የሥራ ዕድል ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን የምትናገረው ሰምሃል፤ በመጀመሪያ የቀጠረቻቸው ሠራተኞች ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ እና በከባድ ችግር ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው ትልቅ ፈተና ነበረ ትላለች።

“ግንኙነታችን በሥራ ውል ላይ ብቻ የሚቆም አልነበረም። ይልቁንም አብሮ የቤት ኪራይ መፈለግ፣ የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገሮች ሟሟላት ያስፈልግ ነበር። ሌላው ፈተና ደግሞ ልጆቻቸው የት ይቆያሉ? የሚለው ነው” ነው የምትለው ሰመሃል፤ ለዚህ ደግሞ በፋብሪካው ውስጥ ጊዜያዊ መጠለያ በማዘጋጀት ሥልጠና እንዲያገኙ እና ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማድረጓን ትናገራች።

“በሺዎች የሚቆጠሩ ቦርሳዎችን ወደ ውጭ እንልካለን፣ የሥራ ዕድል ፈጥረናል። ነገር ግን በስኬቶቼ በጣም የምኮራባቸው እንደዚህ ዓይነት ሕይወት ቀያሪ የሆኑ ነገሮችን ነው። ልጆቻቸው አሁን ያሉበትን ሁኔታ ማየት ውስጣዊ ደስታ ይሰጠኛል” ትላለች።

በአሁኑ ወቅት 80 በመቶ የካባና ሠራተኞች ሴቶች ናቸው፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ ሴቶችን ለአመራርነት ማብቃት ለእኔ በጣም አስፈላጊ ነበር ስትል ሰምሃል ትናገራለች።

“በአካባቢያችን ችግር ያለባቸው እናቶች የሚፈልጉት እርዳታን ሳይሆን ዕድልን ነው። ከመካከላቸው አንዷ አሁን የተመረተ እቃ ጥራት ቁጥጥር የሚደረግበት ክፍል ኃላፊ ናት። እጇን ይዤ አይደለም እዚህ ያደረስኳት፤ እኔ ዕድል ብቻ ነው ያመቿቸሁላት። ስለዚህ ነገሮችን ሆን ብለን ማድረግ ከቻልክ ማሳካት ይቻላል።”

ካባና ለሚያመርታቸው የተለያዩ ቦርሳዎች መጠሪያ የታታሪ ሠራተኞቹን ስም አድርጓል
የምስሉ መግለጫ,ካባና ለሚያመርታቸው የተለያዩ ቦርሳዎች መጠሪያ የታታሪ ሠራተኞቹን ስም አድርጓል

ለስኬታማ ቢዝነስ የሚያስፈልገው ምንድን ነው?

ሰምሃል በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው የቆዳ ምርቶችን የሚያመርተውን ኩባንያ ከወላጆቿ ቤት አንድ ክፍል ውስጥ አልፎ አንድ ትንሽ ጋራዥ ውስጥ ሆና ነው የጀመረችው።

ይህን ቢዝነስ በበቂ የፋይናንስ አቅም ሳይሆን የመሥራት አቅም እና ድህነትን ማሸነፍ የሚል ግብን ይዛ ስትጀምረው፤ ‘ሁሉም ነገር ማድረግ ትችያለሽ’ የሚለው የቤተሰቦቿ ማበረታቻ ሰምሃል በሥራዋ ውጤታማ እንድትሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው።

“አባቴ ድህነት ጠላት ነው ይል ነበር፤ ሕይወትን ድህነትን በማሸነፍ ነው የምንኖረው። ወላጆቼ ለአምስት ዓመት ተኩል የኪነ-ህንጻ ትምህርቴን ጨርሼ በመስኩ አለመቀጠሌ አላስደነገጣቸውም፤ ወይም አላስቆሙኝም። ይልቁንም በውስጥሽ የሚሰማሽን ተከተይ ነበር ያሉኝ። ያ እንዳላቆም አበረታኝ” ስትል ተናግራለች።

ካባና በሁለት እግሩ መቆም ሲጀምር የመጀመሪያዎቹን 200 ወደ ውጪ አገር የሚላኩ የቦርሳ ምርት በትዕዛዝን ተቀበለ።

በወቅቱ ከአንድ ማሽን በቀር በእጇ በቂ ገንዘብ ያልነበራት ሰምሃል፣ የቆዳ ጥሬ ዕቃ አቅራቢ እና ማሽን አቅራቢዎችን የተቀበለችውን ትዕዛዝ የሚያሳይ ወረቀት በማሳየት ብቻ በብድር እንሲጧት በድፍረት ነበረ የጠየቀቻቸው።

በወቅቱ ወጣት ጀማሪ የቢዝነስ ሥራ ፈጣሪ ሴቶች የነበረው እምነት ዝቅተኛ በመሆኑ ከባንክ እና ከሌሎች አበዳሪ ተቋማት እምነት አለማግኘት ከእንቅፋቶቹ አንዱ ነበር፤ ሆኖም ሰምሃል ይህም ተስፋ አላስቆረጣትም።

“የተቀበልነውን ትዕዛዝ ሠርተን ስናጠናቅቅ ደግሞ ገዢዎቹ 100 ቦርሳዎችን በጥራት ጉድለት ምክንያት ውድቅ አደረጓቸው። ይህም ሆነው እንስሳት ቤት ውስጥ በሚታረዱበት ጊዜ በቢላ የተነኩ ቆዳዎች በመኖራቸው ምክንያት ነበር። እኔ ግን ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ስላልነበረኝ በጣም አስደንጋጭ ነበር።”

ሰምሃል በዚህ ችግር ምክንያት የሚፈጠረውን ኪሳራ ለማስቀረት ገዢዎቿ ያልተቀበሏቸውን ቦርሳዎች ወደ ትናንሽ ዋሌቶች በመቀየር ሰርታ ለማስረከብ ሃሳብ አቅርባ ማሳመን ቻለች።

“ምንም እንኳን ባላተርፍበትም የሠራሁትን ተቀበሉኝ። ይህ በሥራ ውስጥ በሚያጋጥሙ ችግሮች ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብኝ ካስተማሩኝ ክስተቶች አንዱ ነው። ከሀብታም ቤተሰብ አልመጣሁም፤ ስለዚህ ሥራ ላይ ችግር አጋጠመኝ ብሎ መተው ሳይሆን ጥርስን ነክሶ መቀጠል ነበር ያለብኝ።”

ከቤተሰቦቿ እና ከጓደኞቿ የምታገኘው ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እና አባል ከሆነችባቸው ማኅበራት የምታገኛቸው የመፍትሄ ሐሳቦች እንዲህ ባሉ ፈታኝ ሁኔታዎች አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ትናገራለች።

“ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ በጣም አስፈላጊ ነው፤ አባቴ ሁልጊዜ የዓላማዬ ግብ ምን እንደሆነ እንድረዳ አድርጎ ነው ያሳደገኝ። ‘ተስፋ መቁረጥ፣ መውደቅ ምርጫ አይደለም፤ ማሳካት የምትፈልጊው አንድ ነገር ካለ በእነዚህ ውስጥ ማለፍ አለብሽ’ ይለኝ ነበር። ስለዚህ አስተዳደጌ ማሳካት የምፈልገውን እንዳልረሳ የሚያደግር ነበር” ትላለች።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽ እና በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በድርጅቷ ምርቶች እና ገበያ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸው በማስታወስ ተስፋ እንድትቆርጥ ሊያደርጓት ከሚችሉ ምክንያቶች ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ታነሳለች።

ወረርሽኙ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት የውጭ ንግድ በመቋረጡ ሳቢያ የገበያዋ ትኩረት በአገር ውስጥ እንዲሆን አደረገች። በወቅቱ ከሌሎች ጋር በመጣመር የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጨርቆች እና ሌሎች የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚያገለግሉ ቁሶችን ወደ ማምረት ፊቷን አዞረች።

ካባና

የካባና ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ኃላፊነት

ሰምሃል ጉዕሽ በስዊድን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የዘላቂ አስተዳደር አመራር ፕሮግራም ሥልጠና እና ትምህርት ወስዳለች። በአውሮፓውያኑ 2020 ደግሞ የኦባማ የአፍሪካ ወጣቶች አመራር ፕሮግራም ዕጩ ነበረች።

በ2018 (እአአ) የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ወጣት ሴት ሥራ ፈጣሪ በማለት ሸልሟታል። አሁን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካባናን ‘ሞዴል’ ኩባንያ ብሎ ሸልሞታል።

ሰምሃል በስዊድን፣ በኬንያ እና በሌሎች አገራት ያገኘችውን ተሞክሮ በተለይ የቆሻሻ እና የፍሳሽ አወጋገድ አሠራሮቿን የበለጠ እንዲሻሻል በማድረግ ከሥራ ፈጠራ ጎን ለጎን ለአካባቢ ጥበቃም የበኩሏን እያበረከተች ነው።

“ስንጀምር ከቆዳ ፋብሪካ የሚለቀቅ ውሃ ከፍተኛ የአካባቢ ብክለት የሚያስከትል አደገኛ ኬሚካል ያለበት መሆኑን ስለምናውቅ ወደ አካባቢ ከመለቀቁ በፊት ውሃውን ከሚያክሙ እና አካባቢን ከማይበክሉ የቆዳ አቅራቢዎች ጋር ነው የምንሠራው” ትላለች።

በተጨማሪም የቆዳ ማምረት ሂደት በአካባቢ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ብክለት ለመከላከል ለዓመታት በፋብሪካዋ የተከማቹ የቆዳ ምርቶች እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል ጫማ፣ ምንጣፍ እና ሌሎች ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን በማምረት እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል ጀምራለች።

ካባና ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ሴቶች ሥልጠናዎች መስጠት እና ሌሎችንም ሥራዎች በማከናወን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ድርጅት ነው። ወደፊት ደግሞ ሥራውን ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ አካባቢዎች ለማስፋት የሚያግዝ ፋውንዴሽን የማቋቋም ዕቅድ እንዳላት ሥራ አስፈጻሚዋ ሰመሃል ትናገራለች።

ከሥራ ውጪ አካላዊ እንቅስቃሴ፣ የእግር ጉዞ እንዲሁም አቻ ሴት ሥራ አስፈጻሚዎች በሚያካሂዱት ውይይት ላይ መሳትፍን የምታዘወትረው ሰምሃል “ስኬት ውስጣዊ እና ውጫዊ ደስታ ነው። የምወደውን ነገር እየሰራሁ በመሆኔ እርካታ ይሰማኛል” በማለት ካባናን አብረዋት ከሚሰሩ ባልደረቦቿ ጋር ከዚህ የላቀ ስኬት ላይ ለማድረስ ታልማለች።