አያ ናካሙራ

ከ 7 ሰአት በፊት

በዓለም ላይ ስማቸው ከገነነ ሙዚቀኞች መካከል አንዷ ናት – አያ ናካሙራ።

አያ በፈረንሳይኛ በመዝፈን ከቋንቋው ተናጋሪዎች ባሻገር በዓለማችን ተደማጭ ከሆኑ ጥቂት ሙዚቀኞች መካከል አንዷ ናት።

ጃጃ (Djada) የሚለው ሙዚቃዋ በዩቲዩብ 954 ሚሊዮን ተመልካቾችን አግኝቷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ነው በሐምሌ ወር በሚከፈተው የፓሪስ ኦሊምፒክስ ላይ የ28 ዓመቷ አያ እንድትዘፍን በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የተጋበዘችው።

አያ በኦሊምፒክስ መክፈቻ ላይ ትዘፍናለች መባሉንም ተከትሎ በማንነት እና በቋንቋ ላይ ውዝግቦችን አስነስቷል።

አያ የተወለደችው በፈረንሳይ ቅኝ በተገዛችው ማሊ ቢሆንም ዕድገቷም ሆነ ዜግነቷ ፈረንሳይ ነው።

የዘመኑን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች (ፍራንኮፎን) በልዩነት ላይ የተመሠረተ ጥምር ባህል መመሥረቱን ለማሳየት ከዚህ የተሻለ መንገድ ሊኖር አይችልም በሚል በአንድ በኩል አያ መመረጧ ተወድሷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሙዚቃዋ ከፈረንሳይ ይልቅ ለአፍሪካ እና ለአሜሪካ የሚቀርብ ነው፤ እንዲሁም በፈረንሳይኛ ቋንቋ መዝፈኗ ዝቅ የሚያደርግ ነው በሚል የሚቃወሟት አልታጡም።

በመክፈቻው እንድትዘፍን ተጋብዛለች መባሉም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ መወዛገቢያ ሆኗል። በተለይም የቀኝ ክንፍ ጽንፈኛው ሪኮንክሰስ ፓርቲ ደጋፊዎች የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ ስሟን እያነሱ ዘልፈዋታል።

ራሳቸውን ለናቲፍስ (የአገሬው ተወላጆች) የተባሉ የቀኝ ጽንፈኛ ቡድን የራሳቸውን ፎቶ የያዘ ባነር “አያ አይሆንም። ይህ ፓሪስ እንጂ ባማኮ ያለው ገበያ አይደለም” የሚል መልዕክት የያዘ ፎቶ ለጥፈዋል።

አያም በምላሹ “ዘረኛ ልትሆኑ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን መስማት አልተሳናችሁም። ያ ነው የሚያቃጥላችሁ። በአገሪቱ ውስጥ አንደኛ የመከራከሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኛለሁ፤ ነገር ግን ለእናንተ ምን ዕዳ አለብኝ? መልሱ ምንም ነው” በሚልም በኤክስ ገጿ ላይ ጽፋለች።

የአገሪቱ ሚኒስትሮች፣ የኦሊምፒክ አዘጋጆች እና ሌሎች ሙዚቀኞች አያን በመደገፍ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከእነዚህም መካከከል የፈረንሳይ የባህል ሚኒስትር ራቺዳ ዳቲ “ዘረኝነትን ሽፋን በማድረግ አንድን ሰው ማጥቃት። አርቲስቷን በማንነቷ ኢላማ ማድረግ ተቀባይነት የለውም። ወንጀል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አያ የተወለደችው በአውሮፓውያኑ 1995 በማሊዋ መዲና ባማኮ ነው።

ቤተሰቦቿ በማሊ ውስጥ ባህላዊ ሙዚቃን ከትውልድ ትውልድ የሚጫወቱት እና ታሪክ ነጋሪ በመባል የሚታወቁት ከግሪዮቶች ማኅበረሰብ ነው።

አያ ናካሙራ

ህጻን እያለችም ስሟ አያ ዳኒኮኮ ይሰኝ ነበር።

ወደ ፈረንሳይም የመጣችው ገና በልጅነቷ ሲሆን፣ በፓሪስ ኦልናይስ ሶስ ቦይስ ሰፈር ነው ያደገችው።

ትምህርቷንም የተከታተለችው በዚያው አካባቢ ነው። ስሟንም ሂሮስ በተሰኘው የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም ላይ የጀግና ገጸ ባህርይ የነበራትን ናካሙራን በመውሰድ ቀየረች።

አያ ወደ ሙዚቃው ዓለም የገባችው በአውሮፓውያኑ 2014 ነው።

አስካሁንም አራት አልበሞች እና በርካታ ነጠላ ዜማዎችን ያወጣች ሲሆን፣ በፈረንሳይ ሙዚቃ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት መካከል ናት።

አያ በተለይም በሌላው ዓለም ስሟ ከጫፍ እስከ ጫፍ የገነነ ነው።

በርካታ የፈረንሳይ ሙዚቀኞች ፈረንሳይኛ ቋንቋ በሚናገሩ ታዳሚዎች ቢወሰኑም፣ አያ ግን በሚገርም ሁኔታ በሙዚቃ ከፍተኛው ዝና ላይ ለመቀመጥ ችላለች።

አገሪቱ ፕሬዝዳንትም ይህንን ዝናዋም በማየት ነው የዓለማችን ታላቁ የስፖርት መድረክ በሆነው የፓሪስ ኦሊምፒክ መክፈቻ ላይ እንድትዘፍን የጋበዟት።

ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እንደሚሉት አያ በኦሊምፒክ ላይ የፈረንሳይ ክላሲክ ሙዚቀኛ እና የ20ኛው ክፍለ ዘመን ቁንጮ የሆነችውን ኤዲት ፒያፍን ሙዚቃ ትጫወታለች።

ነገር ግን አብዛኛው የፈረንሳይ ሕዝብ በዚህ ያልተስማማ ይመስላል።

አያ የዚህችን ሙዚቀኛ በኦሊምፒክ መክፈቻ ላይ ልትጫወት እንደምትችል ዜናው ከወጣ በኋላ አዶክሳ በተሰኘው ተቋም በተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት መሠረት በርካቶች ለሙዚቀኛዋ ጥሩ አመለከካት እንደሌለው ጠቁሟል።

ከተጠየቁት ውስጥ 80 በመቶዎቹ ሙዚቀኛዋን እንደሚያውቋት ቢገልጹም፣ 30 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ለእሷ ጥሩ አመለካከት ያላቸው።

የአያን ሙዚቃ ከሚያውቁት 73 በመቶዎቹ የሚሆኑት ሙዚቃዋን እንደማይወዱት ተናግረዋል። አብዛኞቹ ማለትም 63 በመቶ የሚሆኑት በኦሊምፒክ መክፈቻ ላይ እድትዘፍን በመመረጧ ላይ እንደማይስማሙ ገልጸዋል።

አንደኛው አወዛጋቢ ትችት የመጣው የቀኝ ክንፍ አክራሪው ሪኮንሰስ ፓርቲ አባል የሆኑት ማሪዮን ማርቻል “ውደዷትም፣ ጥሏትም፤ እውነታው ይህች ዘፋኝ በፈረንሳይኛ አትዘፍንም” ሲሉ ተናግረዋል።

ከፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት ፖለቲከኛዋ በአያ ናካሙራ ላይ ስምምነት እንደተደረሰ አድርጎ በኦሊምፒክ ላይ ለመጋበዝ የተደረሰው ውሳኔ ፖለቲካዊ ነው ብለዋል።

“ሆን ብለው ብዝኃነት ያላትን ፈረንሳይን ለማሳየት መርጠዋል። ነገር ግን [አያ ናካሙራ] የፈረንሳይን ቋንቋ አትወክልም” ሲሉም ተደምጠዋል።

እንደ ዋቢ አድርገውም ፖለቲከኛዋ የሚጠቅሱት በዩቲዩብ ላይ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካች ያገኘውን ጃጃን (Djadja) ነው።

ከዘፈኑ ግጥሞች ውስጥ አንዳንድ መስመሮችን ዋቢ በማድረግም ትክክለኛ ፈረንሳይኛ እንዳልሆነ እና ቅልቅል መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ፖለቲከኛዋም ሆነ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ያሉ ፈረንሳውያን አያ ናካሙ የፈረንሳይ ቋንቋ እና ባህል ተወካይ ወይም ተጠሪ ልትሆን አትችልም እያሉ ይገኛሉ።

ነገር ግን እነዚህን ተቃውሞዎች የሚያፈርሱት ደግሞ በኦሊምፒክ መክፈቻ ላይ አያ የምትጫወተው የራሷን ሙዚቃዎች ሳይሆን የኤዲት ፒያፍ ነው የሚል ነው።

የምትዘፍንበት ቋንቋ ትክክለኛ ፈረንሳይኛ አይደለም ቢሉ እንኳን በኦሊምፒክ ላይ የሌላ ሙዚቀኛ ዘፈን ከመጫወቷ ጋር ተያይዞ እንዴት ተቃውሞ ይነሳባታል ይላሉ።

ከሁሉም በላይ አያ በፈረንሳይ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ስኬት ከመጎናጸፏ ጋር ተያይዞ፣ ይህ የመዋሃድ አዎንታዊ ምልክት እና በዓለም ዙሪያ ባሉ ወጣቶች ዘንድ ካላት ተቀባይነት አንጻር ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደር ትችላለች ይላሉ።