
ከ 8 ሰአት በፊት
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በሁለት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ለሥራ ጉብኝት ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ መግባታቸው ተገለጸ።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ገጻቸው ላይ እንደገለጹት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ዛሬ እሁድ መጋቢት 8/2016 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ አሥመራ ገብተዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ጉብኝት በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተደረገላቸው ግብዣ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ አቀባበል ያደረጉላቸውም ራሳቸው ፕሬዝዳንቱ ናቸው።
በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ወደ ሶማሊያ የፕሬዝዳንትነት መንበር የተመለሱት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ለአምስት ጊዜ ወደ ኤርትራ ለጉብኝት ማምራታቸው ይታወቃል።
የፕሬዝዳንቱ የአሁኑ የአሥመራ ጉዞ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ሶማሊያን ያስቆጣ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ በሁለት ወራት ውስጥ የተደረገ ሁለተኛው ነው።
ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት የምትላት እና ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት፣ በምላሹም የአገርነት እውቅን ለመስጠት ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት መከሰቱ ይታወቃል።
- “ሕዝብን በድሮን መትተን አናውቅም” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ10 መጋቢት 2024
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሊያ የአየር ክልል በኩል መብረር ማቆሙን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጹ2 መጋቢት 2024
- የአፍሪካ ቀንድ ትኩሳት፡ ቀውስ በማያጣው ቀጠና ያሉ አገራት ግንኙነት25 ጥር 2024
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነቱን በመሪዎቻቸው አማካይነት አዲስ አበባ ላይ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. መፈራረመቻውን ተከትሎ ተቃውሞዋን ያሰማችው ሶማሊያ ድጋፍ ለማግኘት ፕሬዝዳንቷ ወደ ተለያዩ አገራት ተጉዘው ነበር።
በዚህም የመጀመሪያዋ አገር ኤርትራ ስትሆን ስምምነቱ በተፈረመ በሳምንቱ ታኅሣሥ 29/2016 ዓ.ም. ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በአሥመራ ጉብኝት አድርገው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ጋር ሠራዊቷን ያሰለፈችው ኤርትራ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት የመቀዛቀዝ ምልክቶች ታይተውበታል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ ኤርትራ ካደረጉት ጉዞ በተጨማሪ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበውን ግብፅንም ጎብኝተዋል።
የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ጉብኝትን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በግብፅ ተመሳሳይ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኤርትራ ለሁለት ቀናት ጉብኝት ያቀኑት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከኤርትራ ባለሥልጣናት ጋር በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ የተገለጸ ነገር የለም።
በቀድሞው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ዘመን ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኤርትራ የተላኩ ወታደሮቻቸውን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፕሬዝዳንት ሐሰን በተደጋጋሚ ወደ ኤርትራ የተመላለሱ ሲሆን፣ የአሁኑ ጉዟቸው ከቀሩት ወታደሮቻቸው ጉዳይ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ኤርትራ ውስጥ ለዓመታት በወታደራዊ ሥልጠና ላይ የቆዩት የሶማሊያ ወታደሮች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እና ምን ያህሎቹ በአሁኑ ጊዜ እዚያው እንደሚገኙ በይፋ የተገለጸ አሃዝ የለም።