
ከ 3 ሰአት በፊት
የእስራኤል ኃይሎች በጋዛ በሚገኘው አል ሺፋ ሆስፒታል ላይ በሌሊት በከፈቱት ጥቃት በሆስፒታሉ ውስጥ በታንክ የታገዘ ከባድ ተኩስ እንደነበር ተዘገበ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ፣ መከለካያ ኃይሉ በሆስፒታሉ የተወሰኑ አካባቢዎች “ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት” ዘመቻ እያካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል።
መከላከያ ኃይሉ፣ ከፍተኛ የሐማስ አሸባሪዎች በሆስፒታሉ ውስጥ ራሳቸውን እንደገና አደራጅተው ጥቃት ለመክፈት ሆስፒታሉን እየተጠቀሙበት ነው ብሏል።
የዐይን እማኞች በጋዛ ከተማ በሚገኘው የሆስፒታሉ ሕንጻ የተፈፀመውን ጥቃት አሰቃቂ እንደነበር ገልጸዋል። በዋትስ አፕ ቡድን ላይ በተጋራውና አንድ ግለሰብ ከወንድሙ ጋር በተለዋወጠው የድምጽ ቅጅ “ታንኮች ከበውናል። በድንኳኑ ውስጥ ተደብቀን ነው ያለነው። በግቢው ውስጥ ከፍተኛ የታንክ ተኩስ ይሰማናል” ብሏል።
በቢቢሲ ባልተረጋገጡና በማኅበራዊ ሚዲያ በተጋሩ ምስሎችም በሆስፒታሉ አካባቢ ከባድ የተኩስ ድምጽ ይሰማል።
ሙሐመድ አል ሳይድ የተባሉ ግለሰብ ከሆስፒታሉ ውስጥ ለጋዜጠኞች በላኩት የድምጽ መልዕክትም “በሆስፒታሉ ውስጥ የሞቱ እና የቆሰሉ ወታደሮች አሉ። ወታደሮቹ የተወሰኑ ወጣት ወንዶችን አስረዋል። እዚህ ያለው ሁኔታ አስከፊ ነው” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።
- እስራኤል ሐማስን ‘ለመደምሰስ’ እያካሄደች ያለው ዘመቻ እንዳሰበችው እየተሳካላት ነው?15 መጋቢት 2024
- በጋዛ ከእስራኤል ጎን ተሰልፈው የተዋጉ ዜጎቿ እስር እንደሚጠብቃቸው ደቡብ አፍሪካ አስታወቀች14 መጋቢት 2024
- “በረመዳን ፆም በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን እየተራቡ እና እየሞቱ ነው”13 መጋቢት 2024
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በአል ሺፋ ላይ አዲስ ዘመቻ ሊከፍት ማቀዱን ቀደም ብሎ በይፋ አልገለጸም።
ሆኖም ከጥቃቱ ከሰዓታት በፊት የመከለካያ ኃይሉ ቃል አቀባይ ሪር አዲም ዳንኤል ሃጋሪ፣ የእስራኤል ጦር አፋጣኝ እርምጃ የሚያስፈልጋቸው የደኅንነት ሥራዎች ላይ ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ በከበባው ወቅት ሥራውን መቀጠል እንደሚችል እና ህሙማንና ሰራተኞች ሆስፒታሉን ለቀው መውጣት እንደሌለባቸውም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ሆኖም ሐማስ እጅ እንዲሰጥ ጥሪ ከማቅረባቸው ቀደም ብሎ በሆስፒታሉ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ለቀው መውጣት እንደሚችሉ ገልጸው ነበር።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ዘመቻውን “ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን የጣሰ” ሲል ኮንኖታል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃይ ፍልስጤማውያን በሆስፒታሉ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።
ከእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ቀደም ብሎ አል ሺፋ ሆስፒታል በጋዛ የሚገኝ ትልቅ የህክምና ተቋም ነበር።
በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ መሠረት ሆስፒታሎች በጦርነት ወቅት ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ ቢሆንም ላልተጋባ አላማ የሚውሉ ከሆነ በተወሰኑ ሁኔታዎች ይህንን ጥበቃ ሊያጡ ይችላሉ።
እስራኤል፣ ሐማስ የሕክምና ተቋማትን ለዘመቻው እንደ ሽፋን እየተጠቀመባቸው ነው በማለት ስትከስ ቆይታለች። በኢራን የሚደገፈው ታጣቂው ቡድን ግን ክሱን አስተባብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቅምት ወር ላይ በአል ሺፋ ሆስፒታል ላይ ዘመቻ በከፈተበት ወቅት በሆስፒታሉ ውስጥ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ሐማስ የሚጠቀምበትን ኔትወርክ እና የጦር መሣሪያዎች ማግኘቱን ገልጿል።
የካቲት ወር ላይም የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሁለተኛ ጥልቁ ሆስፒታል በሆነው አል ናስር ሆስፒታል ላይ የምድር ጥቃት ከፍተው ነበር።
ጥቃቱ በተከፈተበት ወቅት የሆስፒታሉ ሐኪሞች እንደታሰሩ እና ዓይናቸው ተሸፍኖ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎም የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ ካሜሩን በጉዳዩ ላይ እስራኤል ምላሽ እንድትሰጥ ጥሪ አቅርበው ነበር።
መከላከያ ኃይሉ በበኩሉ በናስር ሆስፒታል ውስጥ የጦር መሣሪያ እና ስለታገቾቹ ማስረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ ጥቃት የከፈተው ጥቅምት ወር ላይ የሐማስ ታጣተቂዎች የእስራኤልን ደቡባዊ ድንበር ጥሰው በመግባት 1 ሺህ 200 የሚሆኑ ሰዎችን ከገደሉና እና 253 ሰዎችን አግተው ከወሰዱ በኋላ ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በፍልስጤማውያን ግዛት ውስጥ ከ31 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።