
ከ 51 ደቂቃዎች በፊት
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያጋጠመውን “የሲስተም ችግር” ተከትሎ በባንክ ሂሳባቸው በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው በርከት ያለ የገንዘብ ዝውውር ፈጽመዋል የተባሉት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸው ተሰምቷል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ 5ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ወጣት አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ለሊት ላይ በርካታ ተማሪዎች በሂሳባቸው በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም) ጥሬ ገንዝበ ወጪ ማድረጋቸውን እንዲሁም የባንኩን መተግበሪያ ተጠቅመው ገንዘብ ማዘዋወራቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
“አርብ ለሊት 6፡30 አካባቢ ከላይበረሪ ወጥቼ ዶርም ገብቼ ተኛው። እስከዛ ሰዓት ምንም አለሰማሁም ነበር። 7 ሰዓት አካባቢ ዶርም ውስጥ ተማሪዎች ሲያወሩ ሰምቼ ከእንቅልፌ ነቃሁ” ይላል ይህ ተማሪ።
“ከንግድ ባንክ መተግበሪያ ወደ ሲቢኢ ብር ገንዘብ ሲተላለፍ እየቆረጠ አይደለም ሲሉ ሰማሁ። እውነት ነው ብዬ አላመንኩም ነበር” የሚለው ይህ ተማሪ በርካታ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ካለው ኤቲኤም ማሽኖች ፖሊስ እስኪያስቆማቸው ድረስ ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይናገራል።
“በግምት ለሊት 8 አካባቢ ይመስለኛል፤ ኤቲኤም እና ኦላይን ሙሉ በሙሉ መስራት አቁሟል” ብሏል።
ይህ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪም ጨምሮም በነጋታው ቅዳሜ ዩኒቨርሲቲው የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ከባንኩ የወሰዱ ተማሪዎች በአስቸኳይ የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ የሚያስጠንቀቅ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተናግሯል።
ተማሪው አሁን ላይ ገንዘብ ተመላሽ እየተደረገ ስለመሆኑ መረጃው የለኝም ያለ ቢሆንም አርብ ለሊት ከኤቲኤም ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ የነበሩ ጥቂት ተማሪዎች በፖሊስ ተይዘው እንደነበረ ገልጿል።
- አሜሪካ ቲክቶክን ማገድ ለምን ፈለገች? እገዳውስ ተግባራዊ የሚሆነው መቼ ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
- በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት እና የመንገዶች መዘጋት የደቀኑት የጤና ቀውስከ 5 ሰአት በፊት
- ፑቲን ከምዕራባውያኑ ዴሞክራሲ “በላይ” ግልጽነት በነበረው ምርጫ አሸናፊ ሆኛለሁ አሉከ 4 ሰአት በፊት
ሌላኛው የዲላ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በተመሳሳይ አርብ ለሊት ከ6 እስከ 8 ሰዓት ድረስ ተማሪዎች ከኤቲኤም ጥሬ ገንዘብ ሲያወጡ እና በኢንተርኔት ባንኪንግ ገንዘብ ሲያዘዋወሩ ማምሸታቸውን ተናግሯል።
ተማሪው እንደሚለው በዲላ ዩኒቨርሲቲ 1 ሚሊዮን ብር እንዳዘዋወረ የሚነገርለት ተማሪ መኖሩን ጨምሮ ተናግሯል።
አርብ ምሽት ላይ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ በመውጣት ጭምር በዲላ ከተማ ከሚገኙ ገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ እንደነበረ ይህ ተማሪ ይናገራል።
ዛሬ ሰኞ መጋቢ 9 ጠዋት ላይ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ተሸከርካሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ መመልከቱን የገለጸው ተማሪው፤ ገንዘብ ያንቀሳቀሱ ተማሪዎች በፖሊስ እየተያዙ ስለመሆኑ መስማቱን ለቢቢሲ ገልጿል።
በፍቃደኝነት የወሰዱትን ገንዘብ ለመመለስ ወደ ባንክ የሄዱ ተማሪዎችም ‘ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ ተብለው’ በመያዛቸው፤ የወሰዱትን ገንዘብ መመለስ የፈለጉ ተማሪዎችም ፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ ጨምሮ ተናግሯል።
መረጃው በዩኒቨርሲቲዎች ለምን በስፋት ተሰራጨ?
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስርዓቱ ላይ ያጋጠመው ችግር በተለይ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ በስፋት ተሰራጭቷል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው በንግድ ባንክ ሰርዓት ላይ ስላጋጠመው ችግር መረጃው እንዴት በፍጥነት ሊናፈስ እንደቻለ ባያውቅም “ሁሉም ተማሪ ግን ስለጉዳዩ ሲያወራ ነበር። መረጃ ሲቀባበልም ነበር” ብሏል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው በበኩሉ ተማሪዎች በስልክ አማካይኝነት መረጃ ሲለዋወጡ ነበር ይላል።
ከለሊቱ 6 እስከ 8 ሰዓት ድረስ ተማሪዎች በብዛት ሲደዋወሉ እንደነበረ አስታውሶ፤ “እኔ ሳይለንት ላይ አድርጌ ተኝቼ ነበር። ብዙ ደውለውልኝ ነበር። ጓደኛዬ ጋር 20 ወይም 30 ጊዜ እየደወሉ ‘ና ስራ’ ሲሉት ነበር” ብሏል።
ተማሪዎች በጥናት ምክንያት አምሽተው መቆየታቸው፣ እንዲሁም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አባላት ባሏቸው ቡድኖች አማካይነት መረጃ ማስተላለፍ ቀላል በመሆኑ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ መረጃው በቀላሉ እና በፍጥነት ሊሰራጭ እንደሚችል አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ።
የዩኒቨርሲቲዎች ማሳሰቢያ
በንግድ ባንክ ላይ ችግር አጋጥሞ አብዛኛዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገንዘብ አዘዋወረዋል መባሉን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዎች ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያዎችን አውጥተዋል።
ጅማ፣ አዲስ አበባ እና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎቻቸው ማሰሰቢያ ካስተላለፉ ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ስሜ አይጠቀስ ያሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዲላ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ተማሪዎች ወስደው ከነበረው ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ እስካሁን ተመላሽ መደረጉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ንግድ ባንኮች በሁለቱም ካምፓስ መጥተው በፍቃደኝነት ከሚመለሱ ተማሪዎች ገንዘብ እየሰበሰቡ ነበር። ዛሬም ተማሪ እየመለሰ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ምንጫችን እየተሰበሰበ ያለውን ገንዘብ በትክልል እንደማያወቁ የተናገሩ ሲሆን በግምት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ መደረጉን ገልጸዋል።
የሂሳብ እግድ
ባንኩን ባጋጠመው ችግር ደንበኞች ገንዘብ በጥሬ ወጪ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ወደ ሌሎች ባንኮች ገንዘብ አዘዋወረዋል።
ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ለአንድ ሰዓት ገደማ የኤቲኤም አገልግሎት እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር ቢቢሲ ከውስጥ ምንጮች ሰምቷል።
በቅዳሜ ዕለቱ ሁነት ከንግድ ባንክ ሂሳቦች ገንዘብ ከተዘዋወረባቸው ባንኮች ውስጥ አንዱ ዳሽን ባንክ እንደሆነ ቢቢሲ ከባንኩ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያመለክታል። ይህንንም ተከትሎ ከንግድ ባንክ ወደ ዳሽን ባንክ የገንዘብ ዝውውር የተደረገባቸው የባንክ ሂሳቦች መታገዳቸውን ቢቢሲ ስሙ እንዳይጠቀስ ከጠየቀ የባንኩ ባልደረባ ሰምቷል።
ይህ የዳሽን ባንክ ሠራተኛ ምን ያክል ሂሳቦች እንደታገዱ ባያውቅም፤ በንግድ ባንክ ሰርዓት ላይ ችግር ማጋጠሙ ከተገለጸበት በኋላ ከ4ሺህ 500 በላይ የገንዘብ ዝውውሮች መደረጋቸውን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ከአርብ መጋቢት 6/2016 ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ከሌላ ባንክ ገንዘብ ገቢ ከተደረገለት ሂሳብ ገንዘብ ወጪ እንዳይደረግ ዳሽን ባንክ ለሠራተኞቹ ትዕዛዝ ያስተላለፈበትን የኢሜይል መልዕክት ቢቢሲ ተመልክቷል። በዚህ ኢሜል ላይ ገንዘብ ወጪ እንዳያደርጉ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው አርብ ዕለት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ቅዳሜ ጠዋት ከንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር የተደረገባቸው የንግድ ባንክ አካውንቶች ናቸው።
የንግድ ባንክ ምላሽ
ክስተቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ብሔራዊ ባንክ ባወጡት መግለጫ ሰዎች ሂሳባቸው ላይ በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ወጪ እና የገንዘብ ዝውውር አድርገዋል በተባለው ላይ ያሉት ነገር የለም።
ሁለቱም ባንኮች ያወጡት መግለጫ የባንክ አገልግሎት መቋረጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁሉም አገልግሎቶቹ ላይ መቋረጥ የገጠመኝ “በሲስተም ችግር ምክንያት ነው” ብሏል።
ብሔራዊ ባንክ እንዲሁ የንግድ ባንክ አገልግሎት የተቋረጠውበባንኩ የደኅንነት ፍተሻ እና ማሻሻያ ስራ ጋር ተያይዞ ነው ያለ ሲሆን ክስተቱ የደንበኞችን እና አጠቃላይ የፋይናንስ ሰርዓቱን አደጋ የሚጥል አለመሆኑን አረጋግጫለሁ ሲል መግለጫ አውጥቷል።