
ከ 9 ሰአት በፊት
በቻይና ውስጥ የሚጋቡ ጥንዶች ቁጥር ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጭማሬ አሳየ።
ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ውስጥ 7.68 ሚሊዮን አዳዲስ ተጋቢ ጥንዶች የነበሩ ሲሆን ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ12.4 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን መረጃዎች አሳይተዋል።
የአገሪቱ የሲቪል ጉዳይ ሚኒስቴር ከአውሮፓውያኑ 2022 በበለጠ 845 ሺህ አዳዲስ ተጋቢዎች መመዝገባቸውንም አመላክቷል።
በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የተጋቢዎች ቁጥር የታየው በአውሮፓውያኑ 2013 ፣ 13.47 ሚሊዮን ተጋቢዎች በተመዘገቡበት ወቅት ነው።
የአገሪቱ መንግሥት በቻይና ውስጥ ያለውን ዝቅተኛ የወሊድ ምጣኔን ለመቀየር እያደረገው ካለው እርምጃም ጋር ተያይዞ ጋብቻን በከፍተኛ ሁኔታ እያበረታታ ይገኛል።
ቻይና የህዘቧን ብዛት ለመቆጣጠር በሚል በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ አስገዳጅ እና አወዛጋቢ የነበረውን የአንድ ልጅን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጓን ተከትሎም በቀጣዮቹ አስርት ዓመታት የወሊድ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል።
አገሪቱ የህዝብ ብዛቷን ለመጨመር በመጀመሪያ በ2015 በኋላም በ2021 አዳዲስ ፖሊሶችን አጽድቃለች።
በቅርቡም የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ መንግሥታቸው “ከውልደት ጋር የሚስማማ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና የረጅም ጊዜ የተመጣጠነ የህዝብ እድገትንም ለማስፈን” እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።
- ታዋቂዋ ደቡብ አፍሪካዊት የቴሌቪዥን አቅራቢ ባሳየችው “ያልተገባ” ባሕርይ ከተሳፈረችበት አውሮፕላን ተወገደች19 መጋቢት 2024
- ማንኮራፋት እንዴት ትዳርን አስከ መፍረስ ሊያደርስ ይችላል? ምንስ መፍትሄ አለው?19 መጋቢት 2024
- በአንድ ምሽት ተማሪዎችን “ባለሃብት” ያደረገው የንግድ ባንክ የሲስተም ብልሽት18 መጋቢት 2024
የአገሪቱ የመንግሥት ዕቅድ አውጪም የወሊድ እና የትምህርት ወጪን በመቀነስ፣ የወላጅ እረፍት ፖሊሲዎችን በማሻሻል እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የወሊድ ምጣኔን ለማሳደግ እንደሚሰራ ቃል መግባቱም በቅርቡ በታተመ ሪፖርት ላይ ወጥቷል።
የቻይና የህዝብ ቁጥር ዝቅተኛ በሆነው የወሊድ ምጣኔ እና ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሞት ጋር ተያይዞ ለባለፉት ዓመታትም መቀነስ አሳይቷል።
የአገሪቱም የምጣኔ ኃብት ከማሽቆልቆሉ ጋር ተያይዞ ወጣቶች መጋባትን እንደ ምርጫ ሳያዩት ቆይተዋል። ወጣት ሴቶች ደግሞ አገሪቷ ያሻሻለቻቸው የንብረት ሕጎች ለወንዶች ባለቤትነት ይወግናሉ በሚል ስጋት ጋብቻን እንደሚፈሩትም ተገልጿል።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሚጋቡ ሰዎች በተጨማሪ ለፍቺ የሚያመለክቱ ጥንዶች ቁጥር መጨመሩን ነው።
በተጨማሪም ፖሊሲ አውጭዎች በቻይና ካለው እያረጀ ካለው ህዝብ ቁጥር መጨመር ጋርም እየታገሉ ይገኛል። በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከጠቅላላው የአሜሪካ ህዝብ ጋር የሚመጣጠን 300 ሚሊዮን ቻይናውያን ጡረታ እንደሚወጡ ይጠበቃል።
ጋብቻ እና የወሊድ ምጣኔ የተሳሰሩ መሆናቸውን የሚናገሩት ታዛቢዎች የጋብቻ መጨመር የወሊድ መጠኑን እንደሚጨምረው ያምናሉ።