
19 መጋቢት 2024, 07:35 EAT
ደቡብ አፍሪካዊቷ እውቅ የቴሌቪዥን አቅራቢ ሻሚሶ ሞሳካ ባሳየችው “ያልተገባ” ባሕርይ ምክንያት ከተሳፈረችበት አውሮፕላን እንድትወርድ መደረጉን ባለሥልጣናት ገለጹ።
ከደርባን ወደ ጆሀንስበርግ በሚደረገው የሀገር ውስጥ በረራ ነው ይህ የሆነው።
የሀገር ውስጥ በረራ የሚያደርገው ሴምኤር ሰኞ ባወጣው መግለጫ ተፅዕኖ ፈጣሪዋ “የደኅንነት መመሪያዎችን” አልከተልም በማለቷ በረራው በ90 ደቂቃ ዘግይቷል ብሏል።
መግለጫው አክሎ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች የተለኮሰውን ሞተር ለማጥፋት መገደዳቸውን ገልጿል።
ሞሳካ ከቢቢሲ ለቀረበላት ጥያቄ ምላሽ ባትሰጥም የተፈጠረውን ክስተት በኢንስታግራም ገጿ በቀጥታ አስተላልፋለች።
140 ሺህ የኢንስታግራም ተከታዮች ያሏት ሻሚሶ ሞሳካ፤ ኤምቲቪ በተሰኘው ጣቢያ ቤዝ ሳውዝ አፍሪካ የሙዚቃ ፕሮግራም አቅራቢ ናት።
- በአንድ ምሽት ተማሪዎችን “ባለሃብት” ያደረገው የንግድ ባንክ የሲስተም ብልሽት18 መጋቢት 2024
- ፑቲን ከምዕራባውያኑ ዴሞክራሲ “በላይ” ግልጽነት በነበረው ምርጫ አሸናፊ ሆኛለሁ አሉ18 መጋቢት 2024
- አሜሪካ ቲክቶክን ማገድ ለምን ፈለገች? እገዳውስ ተግባራዊ የሚሆነው መቼ ነው?18 መጋቢት 2024
በኢንስታግራም ገጿ ያጋራችውን ቪድዮ በርካቶች ያዩት ሲሆን ተከታዮቿ ለሷ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
የፖሊስ መኮንኖች ከአውሮፕላኑ እንድትወርድ ሲያስገድዷት፤ እሷ ደግሞ ሌላ በረራ እንድሳፈር ካልተደረግኩ አልወርድም ስትል ቪዲዮው ላይ ትታያለች። የአየር መንገዱ ሠራተኞች ይህን ጥያቄዋን ውድቅ አድርገውታል።
ታዋቂዋ ግለሰብ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ድጋፍ ለማግኘት እና ምንም ዓይነት ያልተገባ ባሕርይ እንዳላሳየች ለማስረዳት ስትሞክር ትታያለች።
ሞሳካ ጉዳዩ ዘረኝነት የታከለበት ነው የሚል ወቀሳ የምታቀርብ ሲሆን የአየር መንገዱ ሠራተኞች ምን ጥፋት እንዳጠፋሁ ሊነግሩኝ ፈቃደኛ አይደሉም ትላለች።
የሴምኤር ዋና የፋይናንስ ኦፊሰር ሎራ ቫን ድር ሞለን “ምንም ዓይነት ዘርን መሠረት ያደረገ ነገር የለም” ሲሉ ዘ ሲቲዝን ለተሰኘው ጋዜጣ ተናግረዋል።
ሎራ አክለው ሞሳካ “የደኅንነት መመሪያዎችን ለመከተል ፈቃደኛ ስላልሆነች ከበረራው ልናስወግዳት ተገደናል” ይላሉ።
ይህ የሆነው እሑድ ዕለት በኪንግ ሻካ ዙሉ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ነው።
ሴምኤር ጉዳዩን ለደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አሳልፎ መስጠቱን እና ከዚህ በኋላ ፖሊስ እንደሚከታተለው አሳውቋል።