
ከ 9 ሰአት በፊት
በህንድ በረመዳን ስግደት ላይ የነበሩ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች በማደሪያቸው ቤታቸው ውስጥ የደረሰባቸውን ጥቃት ተከትሎ አምስት ሰዎች በቀጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ባለፈው ዕሁድ በሰሜናዊ የህንድ ክፍል በሚገኘው ጉጅራት ዩኒቨርስቲ የመስገጃ ቦታን በተመለከተ የተፈጠረው በጥላቻ የተሞላ ክርክር ወደ አላላዊ ጥቃት መሸጋገሩን የአካባቢው ባለስልጠናት ተናግረዋል።
በዚህም ሳቢያ አምስት ተማሪዎች መጎዳታቸውን የፖሊስ ምንጮች ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ ላይ ጥቃት የፈጸሙትን ሰዎች ለመቅጣት የጉጅራት ግዛት መንግሥት “ጥብቅ እርምጃ” እየወሰደ እንደሚገኝ የህንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ባለፈው ዕሁድ ምሽት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ተማሪዎቹ ማደሪያ በመግባት እየሰገዱ የነበሩ ተማሪዎችን “ይህንን ማድረግ ያለባችሁ መስጊድ ነው” በሚል ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው የአህሜዳባድ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ማሊክ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ጥቃት ሲያደርሱባቸው እና ድንጋይ ሲወረውሩ ነበር። ማደሪያ ክፍላቸውንም አውድመውታል” ሲሉም አክለዋል። በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ሌላ የፖሊስ ኃላፊ ደግሞ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አምሰት ተማሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ጠቅሶ ተጨማሪ ሰዎች በቅርቡ እንደሚታሰሩ ለቢቢሲ ገልጿል።
በቀጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከሃይማኖታዊ ወይም ፖለቲካዊ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው ያለው ነገር የለም።
- በአንድ ምሽት ተማሪዎችን “ባለሃብት” ያደረገው የንግድ ባንክ የሲስተም ብልሽት18 መጋቢት 2024
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ችግር ባጋጠመው ወቅት ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ዝውውር መካሄዱ ተነገረ18 መጋቢት 2024
- ማንኮራፋት እንዴት ትዳርን አስከ መፍረስ ሊያደርስ ይችላል? ምንስ መፍትሄ አለው?19 መጋቢት 2024
ጥቃቱ የደረሰበት ስፍራ ላይ ድንጋዮች እና የተሰባበሩ ተሽከርካሪዎችን ቢቢሲ ተመልክቷል። በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ቪዲዬዎች የሂንዱን መፈክር የሚያሰሙ ሰዎች ተማሪዎች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ፣ ተሽከርካሪዎችን ሲያወድሙ እንዲሁም ድንጋይ ሲወረውሩ ታይቷል።
ከተጎዱት ተማሪዎች ሶስቱ ህክምና ተደርጎላቸው ከሆስፒታል የወጡ ሲሆን የተቀሩት ተማሪዎች ሆስፒታል ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
አስተያየቱን ለታይምስ ኦፍ ኢንድያ የሰጠው አፍጋኒስታናዊው ተማሪ ናቪድ ሳዲቅ እሱ እና ሌሎች ተማሪዎች በረመዳን ወቅት ምሽት ላይ የሚደረገውን ጸሎት [ተራዊህ] እያደረጉ ሳሉ ወደ ማደሪያቸው ሶስት ተማሪዎች ገብተው በጥያቄ እንዳጣደፏቸው ገልጿል።
ከጥቂት ክርክር በኋላ እነዚሁ ሰዎች ከሌሎች በርከታ ሰዎች ጋር ለጥቃት መመለሳቸውን ገልጾ በድንጋይ እና በብረት ዘንግ ጥቃት እንዳደረሱባቸው እና ንብረታቸውን እንዳወደሙ ይናገራል።

ኖማን የተባለ ሌላ ተማሪ ተመሳሳይ ክስተት ከዚህ ቀደም እንዳጋጠመ ጠቅሶ ከውጪ ሀገራት የመጡ ተማሪዎች ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው ጠቅሷል።
ፖሊስ በዩኒቨርስቲው ወደ 300 የሚጠጉ ተማሪዎች እንዳሉ ጠቅሶ አብዛኞቹ ከአፍጋኒስታን፣ ስሪላንካ እና ከአፍሪካ ሀገራት የመጡ እንደሆኑ ገልጿል።
ጥቃት የደረሰባቸው ተማሪዎች በህንድ መንግሥት የትምህርት ዕድል ያገኙ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
የዩኒቨርስቲው ምክትል አስተዳዳሪ ጥቃቱ በደረሰባቸው እና ባደረሱት ሰዎች መካከል ቀደም ብሎ ውጥረት እንደነበር ገልጸዋል።
“እንዳለኝ መረጃ ከሆነ ስግደቱ ዋነኛ ጉዳይ አልነበረም” ብለዋል።
ጨምረውም የውጪ ሀገራት ተማሪዎች የተሻለ ጥበቃ ወዳለው ቦታ እንደሚዘዋወሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በጸሎት ላይ የነበሩ ሙስሊሞች ለጥቃት ሲዳረጉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በአውሮፓውያኑ 2021 በክፍት ቦታ በጋራ ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች በሂንዱ ተከታዮች ጥቃት ደርሶባቸዋል።