
18 መጋቢት 2024
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውር ተካሂዶበታል ባለው ባለፈው አርብ ሌሊት ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ልውውጥ መከናወኑን አስታወቀ።
ይህ የተገለጸው የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ያጋጠመውን ችግር አስመለክቶ ከሁለት ቀናት በኋላ ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ባንኩ በሰዓታት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ እንዲዘዋወር ምክንያቱ ያለውን የገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱን በማሻሻል ሂደት ወቅት በተፈጠረ ክፍተት ምክንያት መሆኑንም ገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በባንኩ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ችግር በተፈጠረበት ጊዜ ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ባለው ሥርዓት አማካይነት ተንቀሳቅሷል።
ይህ የገንዘብ ዝውውር መጠን “ጤናማውን እና ጤናማ ያልሆነውን” ያካተተ መሆኑን የማለከቱት የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ፣ “በዚህ ወቅት የተዘዋወረ ገንዘብ ወጪ እንዳይሆን ታግዶ ምርመራ እየተደረገ” መሆኑን አመልክተዋል።
የአገሪቱ ግዙፉ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀናት በፊት ያጋጠመው ችግር የመረጃ መረብ [ሳይበር] ጥቃት እንዳልሆነ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ባንኩ ባለፈው አርብ የገጠመው ችግር “የመረጃ-መረብ ወንጀል” አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ አቤ ሳኖ፣ ባንኩ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ባጋጠመው “የሲስተም ችግር” ምክንያት በርካታ ደንበኞች አካውንታቸው ውስጥ ያልተመዘገበ ገንዘብ ማውጣታቸውን ገልጸዋል።
በአገሪቱ ዋነኛው እና በመንግሥት የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ሌሊት ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ ተጠቃሚዎች በአካውንታቸው ውስጥ የሌለ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለማውጣት እና ለማሸጋገር ችለው ነበር።
ለሰዓታት የቆየውን ችግር በተመለከተ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 08/2016 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ከባንኩ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲወጣ ምክንያት የሆነው ችግር የተፈጠረው የገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱን በማዘመን ሂደት ውስጥ “የተፈጠረ ስህተት ነው” ብለዋል።
- በአንድ ምሽት ተማሪዎችን “ባለሃብት” ያደረገው የንግድ ባንክ የሲስተም ብልሽት18 መጋቢት 2024
- በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት እና የመንገዶች መዘጋት የደቀኑት የጤና ቀውስ18 መጋቢት 2024
- የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በሁለት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ለጉብኝት አሥመራ ገቡ17 መጋቢት 2024
በዚህ ክስተት አማካይነት ከባንኩ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ወጪ የተደረገ እና በማባይል ባንኪንግ አማካይነት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር መውጣቱን በአንዳንድ ምንጮች ቢጠቅሱም ባንኩ አስካሁን ምንም ዓይነት የተወሰደበትን መጠን የሚገልጽ መረጃ አልሰጠም።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ጨምረውም ክስተቱን “ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ነበር” በማለት የመረጃ መረብ ጥቃት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ አለመድረሱን እና በደንበኞች አካውንት ላይ የደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመኖሩን አሳውቀዋል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በሰጡት መግለጫ “የተፈጠረው ችግር በሲቢኢ ብር እና በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች ላይ ተደርጎ በነበረ አዲስ የሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ክፍተት” ምክንያት ነው ብለዋል።
ባንኩ በየጊዜው የተለያዩ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ በመግለጫቸው የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ “የተፈጠረውን ችግር እያጣራን ነው” ብለዋል።
በባንክ ሂሳባቸው በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው በርከት ያለ የገንዘብ ዝውውር ፈጽመዋል የተባሉት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውም ተነግሯል።
ቢቢሲ ያናገራቸው ተማሪዎች ባለፈው አርብ ምሽት በርካታ ተጠቃሚዎች አካውንታቸው ውስጥ ካለው በተጨማሪ የፈለጉትን ያክል ሲያዘዋውሩ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
በርካታ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ካሉ የኤቲኤም ማሽኖች ፖሊስ እስኪያስቆማቸው ድረስ ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንድ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለቢበሲ ይናገራል።
ፕሬዝዳንቱ “በቅርንጫፎች እና በዲጂታል የባንኩ አገልግሎቶች ላይ መቋረጥ የገጠመው ሲስተሙ አልሠራ በማለቱ ሳይሆን፣ አዲስ ተግባራዊ በተደረገው ማሻሻያ ሳቢያ በተፈጠረ ክፍተት የተደረጉ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን በመለየት ለማገድ መሆኑን” ገልጸዋል።
አቶ አቢ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች የደኅንነት ማረጋገጫ ያለው” ነው ሲሉ ባንኩ ምንም ዓይነት የሳይበር ጥቃት እንዳልደረሰበት ለማስረገጥ ሞክረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው ተማሪዎች በነጋታው ቅዳሜ ዩኒቨርሲቲው “የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ከባንኩ የወሰዱ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲመልሱ” የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ ማውጣቱን ያስረዳሉ።
ፕሬዝዳንቱ በተፈጠረው ክፍተት አማካይነት ገንዘብ የወሰዱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በባንኩ ጥሪ መሠረት የወሰዱትን ገንዘብ እየመለሱ እነደሆነ እና ገንዘቡን የመለሱት ላይ ባንኩ ምንም ዓይነት ክስ እንደማይመሰርት አስታውቀዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ተማሪዎች ወስደው ከነበረው ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ እስከ ሰኞ ረፋድ ድረስ ተመላሽ መደረጉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የንግድ ባንክ ሠራተኞች በሁለቱም ካምፓስ መጥተው በፍቃደኝነት ከሚመለሱ ተማሪዎች ላይ ገንዘብ እየሰበሰቡ ነበር። ዛሬም ተማሪ እየመለሰ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ባንኩ ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ በርካቶች ጥሬ ገንዘብ ከመክፈያ ማሽኖች ወጪ ከማድረጋቸው በተጨማሪ በሞባይል ባንኪንግ አማካይነት ወደ ሌሎች ባንኮች አዘዋውረዋል።
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮች ለአንድ ሰዓት ገደማ የኤቲኤም አገልግሎት እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር ቢቢሲ ከውስጥ ምንጮቹ ሰምቷል።
በቅዳሜ ዕለቱ ክስተት ከንግድ ባንክ ሒሳቦች ገንዘብ ከተዘዋወረባቸው ባንኮች ውስጥ አንዱ ዳሸን ባንክ እንደሆነ ቢቢሲ ከባንኩ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህንን ተከትሎ ከንግድ ባንክ ወደ ዳሸን ባንክ የገንዘብ ዝውውር የተደረገባቸው የባንክ ሒሳቦች መታገዳቸውን ቢቢሲ ስሙ እንዳይጠቀስ ከጠየቀ የባንኩ ባልደረባ ሰምቷል።