
ከ 4 ሰአት በፊት
ለልማት እና ለማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚፈለጉ ይዞታዎችን ለማስለቀቅ በፌደራሉ መንግሥት ሲከፈል የነበረው ካሳ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች እንዲከፈል የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው “ክልሎች የካሳ ክፍያን ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ላይኖራቸው ይችላል” የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቁሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን አዋጅ የሚያሻሽለው ረቂቅ ለምክር ቤት የቀረበው ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 10/2016 ዓ.ም. ነው።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከአምስት ዓመት በፊት በወጣው አዋጅ ሦስት አንቀጾች ላይ ጉልህ የሆነ ማሻሻያዎችን ያደርጋል።
አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበትን ማብራሪያ እና የሚሻሻሉ አንቀጾችን በምክር ቤቱ ዋና የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ለአባላት በንባብ አቅርበዋል።
አቶ ተስፋዬ በንባብ ያሰሙት እና ቢቢሲ የተመለከተው የረቂቁ ማብራሪያ፤ “ለልማት ተነሺዎች ከሚከፈለው የካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የመሠረተ ልማት ገንቢው ተቋም ካሳ እንዲፈጽም፣ የወሰን ማስከበር ሥራዎችን እንዲያከናውን እንዲሁም መሠረተ ልማቱንም እንዲገነባ ማድረጉ አላስፈላጊ ጫና እና የጊዜ ብክነት እየፈጠረ ይገኛል” ሲል ያትታል።
ማብራሪያው አክሎም የመሬት ይዞታ እንዲለቀቅ የተፈለገው ፌደራል መንግሥቱ አካል ለሚከናወን መሠረተ ልማት እና የማኅበራዊ አገልግሎት ማስፋፊያ ከሆነ ንብረት የመገመት፣ የመክፈል እና የማንሳት ሥራ ሙሉ በሙሉ ለክልል ወይም ለከተማ አስተዳደር አካላት እንደሚሰጥ ያብራራል።
ባለፉት ጥቂት ወራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ሚኒስትሮቻቸው ከተጋነነ የካሳ ግመታ እና ክፍያ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ተደምጠዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የሚኒስትሮች ቅሬታ በረቂቁ ማብራሪያ ላይም ተንጸባርቋል። ማብራሪያው፤ “ንብረቶች ከሚያወጡት ዋጋ በላይ እጅግ የተጋነነ ዋጋ እንዲከፈል” ጥያቄ ማቅረብ፤ “የእርሻ ማሳዎች ከሚሰጡት ምርት በላይ እጅግ የተጋነነ ምርታማነት ከአንድ ማሳ እንደሚገኝ ተደርጎ ዋጋ እንደሚሰላ” አስፍሯል።
በዚህ ምክንያትም፤ “መሠረተ ልማቶቹ ተገንብተው መስጠት የሚገባቸውን የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጥቅም እንዳይሰጡ ከማድረጉም በላይ በመንግሥት ወጪ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ” ሲል ማብራሪያው ጠቅሷል።
ይህን ተከትሎም በፌደራል መንግሥት ለሚከናወን መሠረተ ልማት ከመሬት ይዞታቸው ለሚለቁ ባለይዞታዎች ካሳ የመክፈል ግዴታን የልማት ሥራው ለሚካሄድበት የክልል፣ የወረዳ ወይም የከተማ አስተዳደር ሰጥቷል። ክፍያው የንብረት ካሳ፣ የልማት ተነሺ ድጋፍ፣ የኢኮኖሚ ጉዳት ካሳ፣ የማኅበራዊ ትስስር መቋረጥ እና የሥነ ልቦና ጉዳት ካሳን ይጨምራል።
ይህ የአዋጁ ማሻሻያ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር አባላት ስጋት አዘል ጥያቄ ቀርቦበታል።
- በአንድ ምሽት ተማሪዎችን “ባለሃብት” ያደረገው የንግድ ባንክ የሲስተም ብልሽት18 መጋቢት 2024
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ችግር ባጋጠመው ወቅት ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ዝውውር መካሄዱ ተነገረ18 መጋቢት 2024
- በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት እና የመንገዶች መዘጋት የደቀኑት የጤና ቀውስ18 መጋቢት 2024
ረቂቁን “ከካሳ ክፍያዎች ጋር የተያያዙ [የሚከሰቱ] የጊዜ መጓተቶችን ስለሚያስቀር ይሄንን ለሌላ አካል ለመስጠት የሚያስችል ማሻሻያ ነው” ሲሉ ያሞካሹት አቶ ፍቅሩ ወርቁ የተባሉ የፓርላማ አባል፣ ረቂቁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ቢመለከተው ያሉትን ጉዳይ በጥያቄ መልክ አንስተዋል።
አቶ ፍቅሩ ቋሚ ኮሚቴው እንዲመለከተው ያሉትን ጉዳይ “አዲስ የተመሠረቱ ክልሎች የሠራተኛ ደመወዝ የመክፈል አቅም ባነሳቸው ሰዓት ይሄንን ትላልቅ ጉዳይ ወደ ክልሎች ማውረድ ተግባራዊነቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?” ሲሉ ጥያቄ ሰንዝረዋል።
አቶ ፍሬው ተስፋዬ የተባሉ ሌላ አባል በበኩላቸው፤ “አሁን ባለው ሁኔታ ወረዳዎች የመክፈል አቅማቸው ውስን እንደሆነ የሚታወቅ ነው” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
እንደራሴው አክለውም “በእኔ አተያይ [የካሳ ክፍያ] የጋራ ኃላፊነት ሆኖ ቢመጣ የሚል ሃሳብ አለኝ። ካሳን በመክፈል በኩል የፌደራል እና የክልል መንግሥታት የሚተባባሩበት እና በጋራ የሚሠሩበት አማራጭ በጥልቀት ቢታይ” ሲሉ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
እንደ አቶ ፍሬው ሁሉ ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ወንድወሰን አድማሴም፤ “ክልል እና ፌደራል በጋራ የሚይዙት ማሻሻያ ነው መሆን ያለበት እንጂ ሙሉ ኃላፊነቱ ለክልል የሚሰጥ ከሆነ ያስቸግራል የሚል ሃሳብ ያለኝ” ሲሉ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰጥተዋል።
“በበርካታ ክልሎች ደመወዝ ያልተከፈለው የመንግሥት ሠራተኛ” መኖሩን ያነሱት ደግሞ አቶ ወንድወሰን፤ “ደመወዝ መክፈል ያልቻለ ክልል የልማት ተነሺዎችን [ካሳ] ክፈል ብንለው ሁለቱንም ሳይፈጽም መሃል ላይ እንዳይቀር” ሲሉ ስጋታቸውን ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ አስተጋብተዋል።
ከክልሎች የመክፈል አቅም በተጨማሪ ሌላው የምክር ቤት አባላት የሰነዘሩት ጥያቄ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የተጀመሩ የመንግሥት የመሠረት ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጉዳይ ነው።
አንዲት የምክር ቤት አባል፤ “በነባሩ አዋጅ ሲሠሩ የነበሩ እና ተንጠልጥለው ያሉ የካሳ ጥያቄዎች ተገምቶላቸው ያልተከፈለ ወይም ደግሞ ለተወሰነ ተከፍሎ ለተወሰነ የሚቀር በመኖሩ ዜጎች በዚህ አንቀጽ መሻሻል ምክንያት የሚጠይቁት አካል በግልጽ በአዋጁ ቢቀመጥ መልካም ነው” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል እታፈራሁ ዘገየ፤ “ከዚህ አዋጅ መውጣት በፊት የነበሩ በፌደራል መንግሥት እየተገነቡ ያሉ የተቋረጡም፣ በተለይ ደግሞ የካሳ ያልተከፈላቸው. . . በምንድን ነው ሊስተናገዱ የሚችሉት?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያልተከፈለ 14 ቢሊዮን ብር ገደማ ካሳ መኖሩን ያወሱት አቶ ወንደወሰን የሁለቱን የምክር ቤት አባላት ሃሳብ የሚደግፍ አስተያየት ሰንዝረዋል።
አቶ ወንድወሰን አዋጁ “የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በዚህ አዋጅ ነው የሚመለሱት ወይስ ቀደም ያለው የሚለውን በደንብ ማሳየት አለበት” ብለዋል።
የምክር ቤት አባሉ ቀድመው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ያለባቸው በቀደመው አዋጅ መሠረት መሆን አለበት የሚል ግምት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አቶ ወንድወሰን አክለውም “ይኼ [አዋጅ] ተግባራዊ ሊሆን የሚገባው ለአዲስ ፕሮጀክቶች መሆን አለበት ይኼ ካልሆነ በጣም ያስቸግራል” ብለዋል።
“[አዋጁ] የሽግግር ጊዜ ሊኖረው ይገባል” ያሉት አቶ ወንድወሰን፤ “ይሄ አዋጅ ወደ ሥራ ሲገባ በነባሩ አዋጅ የሚካተቱትን ለይቶ ይኼ አዲሱ አዋጅ ደግሞ ተግባራዊ የሚደረግበት ጊዜ በግልጽ ተቀምጦ ካልሆነ ትንሽ የሚያስቸግርበት ሁኔታ አለ” ሲሉ ስጋታቸውን አንስተዋል።
ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በተደጋጋሚ ስሞታ ሲያቀርብ ይደመጣል።
ተቋሙ ባለፈው ጥር ወር የስድስት ወር አፈጻጸሙን ለምክር ቤቱ ባቀረበበት ወቅት፤ “በተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር፣ በተጋነነ የካሳ ግምት፣ በተቋራጮች አቅም ማነስ እና በተለያዩ ምክንያቶች ፕሮጀክቶች በጊዜያዊነት መቆማቸውን” አስታውቆ ነበር።
ረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ያደረገበት ሌላኛው ጉዳይ ይግባኝ የሚቀርብበትን ሥነ ሥርዓት ነው።
ረቂቁ ለፌደራል ፕሮጀክቶች ከይዞታ መነሳት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ማናቸውም ዓይነት የፍርድ ቤት ክርክሮች የፌደራል መንግሥቱ ተቋም ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ቦታ ባለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንደሚሆን የሚያትት አዲስ ድንጋጌ አካትቷል።
በተጨማሪም “በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ የተቋምን የባንክ ሂሳብ የማገድ ወይም በቀጥታ ክፍያ እንዲፈጸም የሚሰጥ ትዕዛዝ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ትዕዛዝ አማካኝነት ብቻ ይሆናል” የሚል አዲስ ንዑስ አንቀጽ ተጨምሯል።
ረቂቅ አዋጁ ለክልሎች፣ ለአዲስ አበባ እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች አዲስ ሥልጣን ሰጥቷል።
በዚህም መሠረት ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ለፌደራል የመሠረተ ልማት እና የማኅበራዊ አገልግሎት ግንባታ መሬት እንዲለቁ ለተደረጉ ባለይዞታዎች ተገቢውን ካሳ የመክፍል ወይም እንዲከፈል የማድረግ ሥልጣን አላቸው።
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር ዕይታ ለከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ደግሞ ለሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቶታል።