
18 መጋቢት 2024
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያጋጠመውን “የሲስተም ችግር” እንዳጋጠመው ቅዳሜ ዕለት አሳውቋል።
ይህንንም ተከትሎ በባንክ ሂሳባቸው በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው በርከት ያለ የገንዘብ ዝውውር ፈጽመዋል የተባሉት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸው ተሰምቷል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ወጣት አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ሌሊት ላይ በርካታ ተማሪዎች በሂሳባቸው በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም) ጥሬ ገንዘብ ወጪ ማድረጋቸውን እንዲሁም የባንኩን መተግበሪያ ተጠቅመው ገንዘብ ማዘዋወራቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
“አርብ ሌሊት 6፡30 አካባቢ ከላይብረሪ ወጥቼ ዶርም ገብቼ ተኛሁ። እስከዚያ ሰዓት ምንም አልሰማሁም ነበር። ሰባት ሰዓት አካባቢ ዶርም ውስጥ ተማሪዎች ሲያወሩ ሰምቼ ከእንቅልፌ ነቃሁ” ይላል ይህ ተማሪ።
“ከንግድ ባንክ መተግበሪያ ወደ ሲቢኢ ብር ገንዘብ ሲተላለፍ እየቆረጠ አይደለም ሲሉ ነበር። እውነት ነው ብዬ አላመንኩም ነበር” የሚለው ይህ ተማሪ፤ በርካታ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ካሉ የኤቲኤም ማሽኖች ፖሊስ እስኪያስቆማቸው ድረስ ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይናገራል።
“በግምት ሌሊት 8 ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል፤ ኤቲኤም እና ኦላይን ሙሉ በሙሉ መሥራት አቆመ” በማለት የገንዘብ ዝውውሩ ለሰዓታት መካሄዱን ገልጿል።
ይህ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ጨምሮም በነጋታው ቅዳሜ ዩኒቨርሲቲው የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ከባንኩ የወሰዱ ተማሪዎች በአስቸኳይ የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ የሚያስጠንቀቅ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተናግሯል።
ተማሪው አሁን ላይ ገንዘብ ተመላሽ እየተደረገ ስለመሆኑ መረጃው የለኝም ያለ ቢሆንም፣ አርብ ሌሊት ከኤቲኤም ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ የነበሩ ጥቂት ተማሪዎች በፖሊስ ተይዘው ነበረ ብሏል።
- አሜሪካ ቲክቶክን ማገድ ለምን ፈለገች? እገዳውስ ተግባራዊ የሚሆነው መቼ ነው?18 መጋቢት 2024
- በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት እና የመንገዶች መዘጋት የደቀኑት የጤና ቀውስ18 መጋቢት 2024
- ፑቲን ከምዕራባውያኑ ዴሞክራሲ “በላይ” ግልጽነት በነበረው ምርጫ አሸናፊ ሆኛለሁ አሉ18 መጋቢት 2024
ሌላኛው የዲላ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በተመሳሳይ አርብ ሌሊት ከ6 እስከ 8 ሰዓት ድረስ ተማሪዎች ከኤቲኤም ጥሬ ገንዘብ ሲያወጡ እና በኢንተርኔት ባንኪንግ ገንዘብ ሲያዘዋወሩ ማምሸታቸውን ተናግሯል።
ተማሪው እንደሚለው በዲላ ዩኒቨርሲቲ 1 ሚሊዮን ብር እንዳዘዋወረ የሚነገርለት ተማሪ መኖሩን በተማሪዎች መካከል በስፋት ሲነገር እንደነበር አመልክቷል።
አርብ ምሽት ላይ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ በመውጣት ጭምር በዲላ ከተማ ከሚገኙ ገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ እንደነበረ ተማሪዎች አረጋግጠዋል።
ዛሬ ሰኞ መጋቢ 9/2016 ዓ.ም. ጠዋት ላይ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ተሸከርካሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ መመልከቱን የገለጸው ተማሪ፤ ገንዘብ ያንቀሳቀሱ ተማሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋል መጀመራቸውን ሰኞ ጠዋት ለቢቢሲ ገልጿል።
በፍቃደኝነት የወሰዱትን ገንዘብ ለመመለስ ወደ ባንክ የሄዱ ተማሪዎችም ‘ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ ተብለው’ በመያዛቸው፤ የወሰዱትን ገንዘብ መመለስ የፈለጉ ተማሪዎች ሳይቀር ፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ ጨምሮ ተናግሯል።
መረጃው በዩኒቨርሲቲዎች ለምን በስፋት ተሰራጨ?
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገንዘብ መክፈያ እና ማዘዋወሪያ ሥርዓቱ ላይ ያጋጠመው ችግር በተለይ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ በስፋት ተሰራጭቷል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው ይህ የባንክ አገልግሎት ሥርዓት ችግር እንደገጠመው እና ገንዘብ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል መረጃው እንዴት በፍጥነት ሊናፈስ እንደቻለ ባያውቅም “ሁሉም ተማሪ ግን ስለጉዳዩ ሲያወራ ነበር። መረጃ ሲቀባበልም ነበር” ብሏል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው በበኩሉ ተማሪዎች በስልክ አማካይነት መረጃ ሲለዋወጡ ነበር ይላል።
ከለሊቱ 6 እስከ 8 ሰዓት ድረስ ተማሪዎች በብዛት ሲደዋወሉ እንደነበረ አስታውሶ፤ “እኔ ሳይለንት ላይ አድርጌ ተኝቼ ነበር። ብዙ ጓደኞቼ ደውለውልኝ ነበር። ጓደኛዬ ጋር 20 ወይም 30 ጊዜ እየደወሉ ሲጠሩት ነበር” ብሏል።
ዕለቱ የሳምንቱ ማብቂያ ምሽት በመሆኑ እንዲሁም ተማሪዎች በጥናት ምክንያት አምሽተው መቆየታቸው እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አባላት ባሏቸው ቡድኖች አማካይነት መረጃ መተላለፉ ብዙ ተማሪዎች ጋር እንዲደርስ ሳያደርገው አልቀረም።
በተጨማሪም ወጣት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በርካታ ጓደኞች ስለሚኖሯቸው እና በመካከላቸው መረጃዎችን በቀላሉ እና በፍጥነት ስለሚለዋወጡ፤ ይህ ክስተት በተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት መግኘት መቻሉን የሚናገሩ አሉ።

የዩኒቨርሲቲዎች ማሳሰቢያ
በንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ችግር አጋጥሞ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገንዘብ አዘዋወረዋል መባሉን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዎች ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያዎችን አውጥተዋል።
ጅማ፣ አዲስ አበባ እና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎቻቸው ማሳሰቢያ ካስተላለፉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ስሜ አይጠቀስ ያሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዲላ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ተማሪዎች ወስደው ከነበረው ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ እስከ ሰኞ ረፋድ ድረስ ተመላሽ መደረጉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የንግድ ባንክ ሠራተኞች በሁለቱም ካምፓስ መጥተው በፍቃደኝነት ከሚመለሱ ተማሪዎች ላይ ገንዘብ እየሰበሰቡ ነበር። ዛሬም ተማሪ እየመለሰ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ምንጫችን እየተሰበሰበ ያለውን ገንዘብ መጠን ግን በትክልል እንደማያወቁ የተናገሩ ሲሆን፣ በግምት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ መደረጉን ገልጸዋል።
የሂሳብ እግድ
ባንኩን ያጋጠመው ችግር ተከትሎ በርካቶች ገንዘብ በጥሬ ከመክፈያ ማሽኖች ወጪ ከማድረጋቸው በተጨማሪ በሞባይል ባንኪንግ አማካይነት ወደ ሌሎች ባንኮች አዘዋውረዋል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ለአንድ ሰዓት ገደማ የኤቲኤም አገልግሎት እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር ቢቢሲ ከውስጥ ምንጮች ሰምቷል።
በቅዳሜ ዕለቱ ክስተት ከንግድ ባንክ ሂሳቦች ገንዘብ ከተዘዋወረባቸው ባንኮች ውስጥ አንዱ ዳሸን ባንክ እንደሆነ ቢቢሲ ከባንኩ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህንንም ተከትሎ ከንግድ ባንክ ወደ ዳሸን ባንክ የገንዘብ ዝውውር የተደረገባቸው የባንክ ሂሳቦች መታገዳቸውን ቢቢሲ ስሙ እንዳይጠቀስ ከጠየቀ የባንኩ ባልደረባ ሰምቷል።
ይህ የዳሸን ባንክ ሠራተኛ ምን ያህል ሂሳቦች እንደታገዱ ባያውቅም፤ በንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ችግር ማጋጠሙ ከተገለጸ በኋላ ከ4500 በላይ የገንዘብ ዝውውሮች መደረጋቸውን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ከአርብ መጋቢት 6/2016 ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ከሌላ ባንክ ገንዘብ ገቢ ከተደረገለት ሂሳብ ገንዘብ ወጪ እንዳይደረግ ዳሸን ባንክ ለሠራተኞቹ ትዕዛዝ ያስተላለፈበትን የኢሜይል መልዕክት ቢቢሲ ተመልክቷል።
በዚህ ኢሜል ላይ ገንዘብ ወጪ እንዳያደርጉ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው አርብ ዕለት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ቅዳሜ ጠዋት ከንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር የተደረገባቸው የንግድ ባንክ አካውንቶች ናቸው።
የንግድ ባንክ ምላሽ
ክስተቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ብሔራዊ ባንክ ባወጡት መግለጫ ሰዎች ሂሳባቸው ላይ በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ወጪ እና የገንዘብ ዝውውር አድርገዋል በተባለው ላይ ያሉት ነገር የለም።
ችግሩ ያጋጠመው ባንክ እና ማዕከላዊው ባንክ ያወቷቸው መግለጫዎች የባንክ አገልግሎት መቋረጥ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁሉም አገልግሎቶቹ ላይ መቋረጥ የገጠመኝ “በሲስተም ችግር ምክንያት ነው” ብሏል።
ብሔራዊ ባንክ እንዲሁ የንግድ ባንክ አገልግሎት የተቋረጠው ከባንኩ የደኅንነት ፍተሻ እና ማሻሻያ ሥራ ጋር ተያይዞ ነው ያለ ሲሆን፣ ክስተቱ የደንበኞችን እና አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል አለመሆኑን አረጋግጫለሁ ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ቢሆንም ግን አስካሁን ድረስ ከብሔራዊ ባንክም ሆነ ከንግድ ባንክ በዚህ ክስተት ምክንያት ምን ያህል ገንዘብ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ሊዘዋወር እንደቻለ እና እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች ያሉት ነገር የለም።