
ከ 9 ሰአት በፊት
የሐማስ ከፍተኛ የጦር መሪ ማርዋን ኢሳ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን የዋይት ሃውስ ባለሥልጣን ጃክ ሱሊቫን ተናገሩ።
ምክትል የጦር አዛዡ ኢሳ በእስራኤልና በሐማስ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተገደለ ከፍተኛው የጦር መሪ ነው።
ጋዛን የተቆጣጠረው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን የጦር መሪው ሞቷል ስለመባሉ በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።
የእስራኤል የመገናኛ ብዙኃን ምንጮች ኢሳ ከአንድ ሳምንት በፊት እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኘው ኑሴራት የስደተኞች ካምፕ የሚገኝ ዋሻን ኢላማ አድርጋ በፈፀመችው የአየር ጥቃት መገደሉን ዘግበዋል።
የሐማስ የጦር ክንፍ የሆነው ኢዘዲን አል ቃሳም ብርጌድ ምክትል አዛዥ በእስራኤል በጥብቅ ከሚፈለጉ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር።
የአውሮፓ ሕብረት 1 ሺህ 200 ሰዎችን ከገደለው እንዲሁም ጦርነት ከቀሰቀሰው ከጥቅምት ሰባቱ ጥቃት ጋር በተያያዘ የሐማሱን መሪ በሽብርተኛ መዝገብ ውስጥ አካቶታል።

የጦር መሪው በመጀመሪያው የፍልስጤም ተቃውሞ ወቅት ለአምስት ዓመታት በእስራኤል ታስሮ ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ 1997ም በፍልስጤም ባለሥልጣን በቁጥጥር ሥር ውሎ ሁለተኛው የፍልስጤም ተቃውሞ እስከጀመረበት 2000 ድረስ በእስር አሳልፏል።
ጥቅምት ሰባት ላይ ሐማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በመግባት ጥቃት ፈፅሞ እስራኤል የአፀፋ ምላሽ መስጠት ከጀመረች ወዲህ በርካታ የሐማስ ከፍተኛ መሪዎች ተገድለዋል።
ከእነዚህ መካከል በቤሩት ደቡባዊ ከተማ ዳህየህ በደረሰ ፍንዳታ የሞተው የሐማስ የፖለቲካ መሪ ሳሌህ ኣል አሮሪ ይገኝበታል።
የዋይት ሃውስ የጸጥታ አማካሪ ሱሊቫን እንዳሉት ሌሎች የሐማስ መሪዎችም በጋዛ ጥልቅ በሆነ የኔትዎርክ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው እንደሚገኙ ይታመናል።
አማካሪው፣ አሜሪካ እስራኤል ከፍተኛ የሐማስ መሪዎችን ለማደን ለምታደርገው ዘመቻ ድጋፍ እንደምታደርግም ቃል ገብተዋል።
ሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር በጦርነቱ አቅጣጫ ዙሪያ የስልክ ንግግር አድርገዋል።
ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ እስራኤል በሐማስ ላይ እየተቀዳጀችው ያለችውን ስኬት የጠቀሱት አማካሪው ሱሊቫን፣ ፕሬዚደንት ባይደን ከኔታንያሁ ጋር በነበራቸው የስልክ ልውውጥ የሰላማዊ ሰዎች ሞት መጨመሩ እንዳሳሰባቸው መናገራቸውን ገልጸዋል።
የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከጀመረ አንስቶ ከ31 ሺህ በላይ ሰላማዊ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጋዛ የሟቾቹ ቁጥር መጨመርና የሰብዓዊ ቀውስ መባባሱ ዓለም አቀፍ ውግዘትን ያስከተለ ሲሆን በርካታ የእስራኤል አጋሮችም ራሳቸውን እንዲነጥሉ አድርጓል።
- እስራኤል ሐማስን ‘ለመደምሰስ’ እያካሄደች ያለው ዘመቻ እንዳሰበችው እየተሳካላት ነው?15 መጋቢት 2024
- በጋዛ የሚገኘው የእርዳታ ማዕከሉ ላይ የእስራኤል ጦር ጥቃት እንደፈጸመበት ተመድ ገለጸ14 መጋቢት 2024
- በጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ እንደሆነ ዶ/ር ቴድሮስ ተናገሩ5 መጋቢት 2024
ፕሬዚደንት ባይደንም በንግግራቸው ኔታንያሁ በጋዛ ግልጽና ጦርነቱ እንዲያበቃ አዲስ ስልት መያዝ እንዳለባቸው ግፊት ማድረጋቸውን ሱሊቫን ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ “ የሐማስን የማሸነፍ ዓላማ እንደግፋለን፤ ነገር ግን ይህ እንዲሆን ዘላቂነት ያለው እና አስተማማኝ ስልት እንደሚያስፈልግ እናምናለን” ማለታቸውንም አማካሪው ጨምረው ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በራፋህ ላይ የሚፈፀመውን ወረራ በተመለከተ አሜሪካ ባላት ስጋት ላይ ለመነጋገር የእስራኤል መሪ፣ የጦር፣ የደኅንነት እና የሰብዓዊ ባለሥልጣናትን የያዘ ቡድን በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ዋሽንግተን ለመላክ እንዲስማሙ ማድረግ መቻላቸውን አመልክተዋል።
ይህ ስብሰባ እስከሚካሄድ ድረስም እስራኤል በራፋህ ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት ታዘገያለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ሱሊቫ አክለዋል።
ፕሬዚደንት ኔታንያሁም ይህንን ጥሪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ያረጋገጡ ሲሆን ሁለቱ መሪዎች በጦርነቱ ላይ ስላሉ አሁናዊ መረጃዎች እንዲሁም የግጭቱ ዋና ግብ ላይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እነዚህ አላማዎች ሐማስን ማጥፋት ፣ ታጋቾችን ማስለቀቅ እና ጋዛን የእስራኤል ስጋት እንዳትሆን ማድረግ እንዲሁም እነዚህን አላማዎች ለማሳካት አስፈላጊ እርዳታን ማቅረብ እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል።
ባይደን ስልክ ከመደወላቸው አስቀድሞ በአሜሪካ አንድ ከፍተኛ ዲፕሎማት ኔታንያሁ ላይ ከፍተኛ ትችት ሰንዝረው ነበር።
ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ቹክ ሹመር ሐሙስ ዕለት “ ኔታንያሁ ከአገሪቷ ፍላጎት ይልቅ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ጥቅም እያስቀደሙ ነው” ሲሉ በእስራኤል አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አወቅርበዋል።
የኔታንያሁ ሊኪዩድ ፓርቲ በበኩሉ “እስራኤል ደካማ አገር አይደለችም” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖሊሲዎች በብዙኃኑ እንደሚደገፉ ገልጿል።
ባይደን አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ሹመር የሰጡትን አስተያየት እንደሚያውቁ ገልጸው፤የሴኔቱ መሪ በርካታ አሜሪካውያን የሚጋሩትን ስጋታቸውን ነው የገለጹት ብለዋል።