March 20, 2024 – Konjit Sitotaw 

የአብይ አህመድ አገዛዝ ለአዲስ አበባና ለከተማዋ ነዋሪዎች ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ ላለፉት ስድስት ዓመታት ስናየው የከረምነው እውነታ ነው ። ለዚህ ማስረጃ ማቅረብ ሳያስፈልግ ዓለም ያወቀው ተግባሩ ምስክር ነው ። ይህ ጥላቻው ከእለት ወደ እለት እየባሰበት መጥቶ ዛሬ ላይ መላ አዲስ አበባን ወደማፈራረሱ አድርሶታል ።
ዛሬ አዲስ አበባና ታሪኳ በአዳነች አቤቤ አጥፊ ሀይሎች እየተናዱ ፣ እየጠፉና እንዳልነበሩ እየሆኑ ነው ። አዲስአበባ ትላንቷን እያጣች ማንነቷን እየተነጠቀች ትገኛለች ። አዲስ አበባን ዘረኞች እያረሷት ፣ ተረኞች እያወደሟት ይገኛሉ ። ትዝታዋ እየተፋቀ በታሪክ አልባና እሷን በማይመስል ማንነት እየተዋጠች እንደሆነ እዚህም አዚያም በልማት ስም የሚደረጉ ተግባሮች ማሳያ ናቸው ።

ነዋሪዋ እየተፈናቀለ በነዋሪው ህይወት ፈንታ ችግኝ ተከብሮ እየተተከለባትም ትገኛለች።በከተማችን ሠውነት ረክሶ ዛፍ ከብሯል ። ዜግነት ተጥሎ የሚያብለጨልጭ መብራት ነግሷል ። አዲስ አበባን የማያውቋት አዲስ አበባን እያጠፏት ነው ስንልም በምክንያት ነው ። ፍቅር ላበደረ በቀል፣ይቅርታን ለለገሰ ቂም ፣ ሠላምን ለናፈቀ ቁርሾ መስጠት የአዲስ አበባና የብልጽግና ህይወት ከሆነ ሰነባብቷል ።


ግብግቡ እናጠፋችኃለን አንጠፋም ቢሆንም እውነቱን ለመናገር ለብልጽግና የጥፋት እጆች መዘርጋት የእኛ የአዲስ አበባ ልጆች ዝምታ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው መካድ አይቻልም ። ይህ ዝምታችን በበዛ መጠን የመጥፋት መጠናችንም አብሮ ይጨምራል ። የአዲስ አበባ ህዝብ የብልጽግና ልክ ያለፈ የጥፋት እጆችን ለመቁረጥ ትግል እየጀመረ መምጣቱን የተረዳው አገዛዙ ሰሞኑን ደግሞ ሳይቀድሙኝ ልቅደማቸው በሚል እሳቤ ይመስላል ጥፋቱን በእጥፍ አጠናክሮ ቀጥሏል ። የአማን እንቅስቃሴ ፣ የአራዳው የህቡእ አደረጃጀት ወደትግል መግባትና የሠራተኛ ክፍሉ እንቢታ ከለት ወደ እለት እያሰጋው መላው የአዲስ አበባ ህዝብ ወደዚህ ትግል ጠቅልሎ ገብቶ የጥፋት እጆቼን ይቆርጣቸዋል ብሎም ሰግቷል። ስለሆነም አማን ለመላው የአዲስአበባ ህዝብ ከጥፋት ለመዳን ዝምታችን ይብቃ ፣ ትግሉን ያልተቀላቀላችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ፣ በመላው ኢትዮጵያና በመላው ዓለም ያላችሁ የአዲስ አበባ ወዳጆች ትግሉን ተቀላቀሉን የሚል ጥሪን በድጋሚ ማስተላለፍ ይወዳል ።

በዝምታ ወደሞት ፣ በዝምታ ወደስደትና ታሪክ አልቦነት መጓዛችን ይብቃ።በየአካባቢያችን ተደራጅተን ትግላችንን እናቀጣጥል ። ይበቃል እንበል ።

አማን ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ትግሉን ቀጥሏል።መላው የአዲስ አበባ ነዋሪም የህልውናውን ትግል ይቀላቀል ዘንድ የአዲስ አበባ ማኀበራዊ ንቅናቄ (አማን) ጥሪውን ያስተላልፋል ።

#ይበቃል
10/07/2016 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማኀበራዊ ንቅናቄ (አማን)