
20 መጋቢት 2024, 17:38 EAT
ለግብርና ኢንቨስተሮች በከፊል ተሰጥቶ የነበረው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ መሬት እንዲመለስ መወሰኑን የመጠለያው ኃላፊ አቶ ባንኪ ቡደሞ ያኪሶ ለቢቢሲ ገለጹ።
ከመጠለያው ተቆርሶ ለግብርና ኢንቨስተሮች ተሰጥቶ የነበረው 117 ሄክታር እንዲመለስ የተወሰነውም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ቢሮ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሆኑም ተገልጿል።
ከመጠለያው ከፊል ስፍራ ለግብርና ኢንቨስተሮች መሰጠቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳ ጥበቃ ባለስልጣን እና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር።
የዝሆኖቹን የመጠለያ ድንበር አልፎ ገብቶ ለኢንቨስተሮች ተሰጥቷል የሚለውንም ጉዳይ የዞኑ አስተዳደር አልተቀበለውም ነበር።
የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያም ጉዳዪን ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ቢሮ ወስዶ እንዲታይለት መጠየቁንም ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የክልሉ የፕሬዚዳንት ቢሮ ለኦሮሚያ ክልል ጥበቃ ባለስልጣን የዝሆኖች መጠለያ ድንበር ታልፎ መሬት ተሰጥቷል የሚለውን እሰጣእገባ እልባት እንዲገኝለት እንዲሁም ከመጠለያው ተወስዶ እየታረሰ ከሆነ እንዲቆም አቅጣጫ ማስቀመጡን አቶ ባንኪ ይናገራሉ።
የጥበቃ ባለስልጣኑም ኮሚቴ አቋቁሞ ባደረገው ማጣራት ከመጠለያው ስፍራ ተቆርሶ ለኢንቨስተሮች መሰጠቱን ማግኘቱንም ተከትሎ የተወሰደው መሬት እንዲመለስም የዞኑ ካቢኔ ውሳኔ አስተላልፏል ብሏል።
ኃላፊው እንደሚሉት መሬቱን ከመመለስ በተጨማሪ በህግ መጠየቅ ያለባቸው አካላትም እንዲጠየቁ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባቸዋል ያሏቸው ኢንቨስተሮች ከተፈቀደላቸውም መሬት በላይ ከማረስ በተጨማሪም ደኑን መመንጠራቸውን ገልጸዋል። ከኢንቨስተሮች በተጨማሪም የመጠለያውን መሬት በህጋዊነት የሰጠው አካል ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ እንደሚኖርም ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ስፋቱ 6980 ካሬ ኪሎ ሜትር የሆነው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ውስጥ ለእርሻ ልማት በሚል ለኢንቨስተሮች ተሰጥቶ ሲታረስ የነበረው መሬት በፓርኩ ሰሜናዊ ክፍል ኤረር ሸለቆ በሚባለው ስፍራ ያለ ነው።
ስፍራው የዝሆኖቹ ዋነኛ የመራቢያ እና የመንቀሳቀሻ ስፍራ በመሆኑ በእንስሳቱ አጠቃላይ ደኅንነት ላይ አደጋን ሊያስከትል ይችል እንደነበርም ተገልጿል።
ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ከፊል ስፍራ ተቆርሶ ለግብርና ኢንቨስተሮች መሰጠቱ ያስቆጣቸው ሦስት ምሁራን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል።
- በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ መሬት ለኢንቨስተሮች መሰጠቱ በዝሆኖች ደኅንነት ላይ ስጋት ፈጠረ30 ነሐሴ 2023
- የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ለኢንቨስተሮች መሰጠቱን በመቃወም ሦስት ምሁራን ለጠ/ሚ ዐቢይ ደብዳቤ ጻፉ28 መስከረም 2023
- የባቢሌ ዝሆኖች ህልውና አደጋ ላይ ነው14 ነሐሴ 2019
የባቢሌ ፓርክ ደን ተመንጥሮ ለኢንቨስተሮች መሰጠቱ ከፍተኛ የድርቅ አደጋ እንደሚጋርጥ በመግለጽም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ እንዲገቡ ምሁራኑ በደብዳቤያቸው ጠይቀው ነበር።
በምሥራቅ ሐረርጌ የሚገኘው ይህ መጠለያ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች መካከል መገኘቱ ከዚህ ቀደምም ሲያወዛግብ የነበረ ስፍራ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው በተለይም ከፊል መሬቱ ኢንቨስትመንት መሰጠቱ ከሶማሌ ክልል ጥያቄ አስነስቶም እንደነበር ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከመጠለያው ስፍራ ተቆርሶ በመንግሥት በህጋዊ መልኩ መሰጠቱ በፓርኩ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ “ህገወጥ ነዋሪዎችን” ያበረታታ እና ለማስወጣትም የሚደረገው ጥረትም ማነቆ ሆኖ እንደነበር ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት ውሳኔውን መርምሮ ወደኋላ መመለሱም ትልቅ ትምህርት ያስተላልፋል ብለዋል።
በዚህ ፓርክ ውስጥ 40 ሺህ አባወራዎች መስፈራቸው ለማህበረሰቡም ሆነ ለዝሆኖቹ ህልውና አደጋ መደቀኑንም በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
ነዋሪዎቹ እና ዝሆኖቹ በአቅራቢያ ስፍራ በመኖራቸውም ህብረተሰቡ እየተጎዳ እንደሆነ የገለጹት አቶ ባንኪ በዚህ ዓመት ብቻ 13 ሰዎች መግደላቸውን ገልጸዋል።
መጠለያቸው የተነካባቸው አደጋ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ የገለጹት ኃላፊው ነዋሪዎቹ ሙሉ በሙሉ ወጥተው የዝሆኖች መኖሪያነት ብቻ እንዲሆንም መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተብሏል።
በዚህ መጠለያ ወደ 320 የሚሆኑ ዝሆኖች ያሉ ሲሆን ለጥርሳቸው ሲባል የሚደረግ ህገወጥ አደንም ህልውናቸውን እየተፈታተነው ይገኛል።በዚህ ዓመት ብቻ ስድስት ዝሆኖች በህገወጥ አዳኞች ተገድለዋል።
የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1962 ዓ.ም. ነበር የተመሠረተው።
ይህ የዝሆኖች መጠለያ በአፍሪካ ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ብቸኛው የጥቁር ዝሆኖች መጠለያ ፓርክም ነው።
በኢትዮጵያ ብቸኛ የጥቁር ዝሆኖችን መጠለያ ባቢሌ ፓርክ ከ30 በላይ አጥቢ እንሰሳት 220 ብርቅዬ አእዋፋት መጠለያ ሆኖ ቆይቷል።
የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በፓርኩ ውስጥ ከ31 በላይ አጥቢ እንስሳት እና ከ220 በላይ የአዕዋፋት ዝርያዎች ይገኛሉ።