የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ

20 መጋቢት 2024, 15:48 EAT

የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በዲፕፌክ የተሰሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመጠቀም የወሲብ ፊልም ላይ ‘መታየታቸውን’ ተከትሎ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ ሊጠይቁ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጉዳቱን ያደረሱት ግለሰቦች 100 ሺህ ዩሮ እንዲከፍሉም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል።

የእውነት የሚመስሉ ሐሰተኛ ምሥሎችና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በዲፕፌክ (deepfake) መተግበሪያ በመጠቀም የተሰራው የወሲብ ፊልም በኢንተርኔት ላይ ለዕይታ መዋሉንም ተከትሎ ነው ክሱ የተመሰረተው።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በሰርዲያ ግዛት ሳሳሪ ከተማም በሚገኘውም ፍርድ ቤት ምስክርነታቸውን ለመስጠት ሰኔ መጨረሻ ላይ ቀጠሮ ተይዟል።

ዲፕፌክ የተሰኘው ቴክኖሎጂ የአንድን ሰው ምስልና ተንቀሳቃሽ ምስል አሳማኝ በሆነ መልኩ በሌላ በመተካት በዲጂታል በማቀነባበር የሚሰራ ነው።

በተጨማሪ የአንድን ሰው ምስልና ተንቀሳቃሽ ምስል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሌላ አካል ላይ በማገናኘትም እንዲሁም በዓለማችን የማይገኙ የሰዎችን ምስልም ኮምፒውተርን በመጠቀም ሲሰራም ዲፕ ፌክ ይሰኛል።

እነዚህን ቪዲዮዎች ሰርቷል ተብሎ የተጠረጠረው የ40 ዓመት ግለሰብ እና የ73 ዓመት አባቱ በምርመራ ላይ ናቸው።

ቪዲዮዎቹን በበይነ መረብ ለመለጠፍ ያገለገለውን የሞባይል ስልክ በመከታታል ፖሊስ ሊያገኛቸው እንደቻለም ተገልጿል።

ሁለቱም ግለሰቦች በስም ማጥፋት (ዲፋሜሽን) ወንጀል ተከሰዋል።

በጣሊያን ህግ መሰረት አንዳንድ የስም ማጥፋት ክሶች በወንጀል የሚያስቀጡ ሲሆን የእስር ቅጣትም ሊያስከትሉ ይችላሉ።

በክሱ መሰረት ቪዲዮዎቹ ከወራት በፊት በአሜሪካ የወሲብ ፊልም ማሳያ (ፖርኖግራፊ) ድረ ገጽ መለጠፉንም ተከትሎ “ለሚሊዮኖች” ጊዜ ታይቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሯ የጉዳት ካሳ ጥያቄያቸው ከተሳካ የሚያገኙትን 100 ሺህ ዩሮ በወንዶች ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ድጋፍ ለማድረግ እንዲውል እንደሚያበረክቱ የህግ ባለሙያ ቡድናቸው አስታውቋል።

ክሱ ምሳሌያዊ እንደሆነ እና ለጉዳት የካሳ ክፍያ ጥያቄውም በእንዲህ አይነት ጥቃቶች ሰለባ ለሆኑ ሴቶች ክስ ለመመስረት እንዳይፈሩ መልዕክት ለመላክ እንደሆነም የጠቅላይ ሚኒስትሯ አንደኛዋ ጠበቃ ማሪያ ጁሎያ ማሮንጊዪ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሯ ዲፕፌክ ቪዲዮዎች ይህንን ስልጣን ከመያዛቸው ከአውሮፓውያኑ 2022 በፊት የተሰሩ ናቸው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ ዲፕፌኮች አብዛኞቹ ወሲባዊ ይዘት አላቸው። ሴቶች ላይ ያነጣጠሩት 99 በመቶ ናቸው።

የጥቃቱ ሰለባዎች ፊታቸውን በዲጂታል መልኩ በተቀነባበሩ የወሲባዊ ፊልሞች ማየታቸው ያደረሰባቸውን ሰቆቃም ሲናገሩ ይሰማል።