የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር

ከ 4 ሰአት በፊት

የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር በገዛ ፈቃዳቸው ከሥልጣን ሊለቁ መሆኑን አስታወቁ።

ከፓርቲ ሊቀ መንበርነታቸው ወዲያውኑ የሚነሱ ሲሆን ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተመረጠ በኋላ ደግሞ ሥልጣናቸውን ይለቃሉ ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን መልቀቃቸውን ባስታወቁበት ወቅትም “አገራቸውን የመሩበት ዓመታት በሕይወታቸው የተሳካ ተግባር ያከናወኑበት” እንደሆነም ገልጸዋል።

ከሥልጣን የለቀቁትም በ”ግላዊ እና ፖለቲካዊ” ምክንያቶች እንደሆነም ተናግረው “ለዚህ ኃላፊነት የተሻለው ሰው አይደለሁም” በማለት ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 2017፣ በ38 ዓመታቸው የፓርቲያቸው ፋይን ጋኤል ሊቀ መንበር መሆን የቻሉት ሊዮ ቫራድካር፣ የአየርላንድ በዕድሜ ትንሹ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ታሪክ ሰርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በደብሊን መቀመጫውን ያደረገውን የጥምር ፓርቲዎች መንግሥት ከፊያና ፌይል እና ግሪን ፓርቲ ከተሰኙት ፓርቲዎች ጋር እየመሩ ይገኛሉ።

ረቡዕ ዕለትም በደብሊን ከሚገኝ የመንግሥት ህንጻዎች ደረጃ ላይ ሆነው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አየርላንድን ከሥራ አጥነት እንደታደጓት እንዲሁም ከበጀት ጉድለት ወደ በጀት ትርፍ እንዲሁም ከምጣኔ ኃብት መሽመድመድ አውጥተው ወደ ብልጽግና እንደመሯትም ተናግረዋል።

በተለይም በአየርላንድ “የህጻናት መብትን በማስከበር፣ ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ማኅበረሰብ እና ለሴቶች እኩልነት በመስራት አገራቸውን ዘመናዊ እና እኩልነት የሰፈነባት በማድረጋቸው ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን ዘመናቸው የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እና ጽንስ ማቋረጥን ሕጋዊ እንዲሆን ለማድረግም የአየርላንድ ሕገመንግሥትን ለመቀየር የተደረጉ ሕዝበ ውሳኔዎችን ደግፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣናቸው ዘመን ሌሎች አሳካኋቸው ብለው የጠቀሷቸው የህጻናት እንክብካቤ ተደራሽነትን ማሻሻል እንዲሁም መንግሥት በሥነ ጥበብ፣ ባህል፣ ዓለም አቀፍ ልማት እና የሕዝብ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚያደርጋቸውን ወጪዎችን መጨመር ይገኙበታል።

ሆኖም “ያልተሳካልን አንዳንድ ዘርፎች አሉ” ሲሉም ተናግረው “በእንደዚህ አይነት ቀን ሌሎች ነቅሰው እንዲያወጧቸው ብተወው ይቅር እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

አሁን ያለው መንግሥት “እንደገና ሊመረጥ ይችላል” ቢሉም ነገር ግን “ከእንግዲህ ለኃላፊነቱ የተሻለው ሰው እንዳልሆንኩ” ይሰማኛል ብለዋል።