
ከ 5 ሰአት በፊት
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአምስተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን መንበራቸው ላይ ለመቆየት አሸንፈዋል።
በዚህም እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ ባሉት ቀጣይ ስድስት ዓመታት ሩሲያን እንደሚመሩ እርግጥ ሆኗል።
ድል ከተጎናጸፉ በኋላ ባደረጉት ንግግር የእሳቸው በሥልጣን መቀጠል “ሩሲያ ጠንካራ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድትበለጽግ ያስችላታል” ብለዋል።
ድላቸውም ክብረ ወሰን በሰበረ መልኩ የመራጮችን 87 በመቶ ድምጽ በማግኘት የተገኘ ነው። ከዚህ ቀደም በነበረው ምርጫ ያሸነፉት 76.7 በመቶ በሆነ ድምጽ ነበር።
ፑቲን ያሸነፉበት ምርጫ ተቃሚዎች በሌሉበት፣ ቤተ መንግሥታቸው ክሬምሊን የሩሲያን ፖለቲካ፣ መገናኛ ብዙኃንን እና ምርጫን አጥብቆ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ነው።
በርካታ ምዕራባውያን መሪዎች ምርጫውን ነጻ እና ፍትሃዊ አይደለም በማለት አውግዘዋል።
ከእነዚህም መካከል የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አንዱ ሲሆኑ “በሥልጣን የሰከረ አምባገነን” እንዲሁም “የግል ሥልጣኑን ለማራዘም የማይሠራው ክፋት የለም” ሲሉ ወርፈዋቸዋል።
የ71 ዓመቱ ፑቲን በአውሮፓውያኑ 1999 ማጠናቀቂያ ነበር ወደ ሥልጣን የመጡት። ከጆሴፍ ስታሊን በኋላም ሩሲያን ለረዥም ጊዜ ለመምራት ችለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፍታ በርካታ ዜጎቿ በጦርነቱ ቢገደሉም፣ ሦስተኛ ዓመቱን ከያዘው ወረራ ጋር ተያይዞ በምዕራቡ ዓለም የተገለለች ብትሆንም፣ ፑቲን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃያል የሆኑባቸው ሦስት ምክንያቶች አሉ።
- ፑቲን ከምዕራባውያኑ ዴሞክራሲ “በላይ” ግልጽነት በነበረው ምርጫ አሸናፊ ሆኛለሁ አሉ18 መጋቢት 2024
- ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ሰላም የሚኖራት “ዓላማችን ሲሳካ ብቻ ነው” አሉ14 ታህሳስ 2023

1. ሳንሱር የሰፈነባት እና ተቃዋሚ የሌለባት ሩሲያ
“ፑቲን በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ዓይነት የፖለቲካ ውይይቶች እንዴት ማፈን እንደሚቻል ያውቃል” ይላል ከሦስት ዓመት በፊት በለንደን በግዞት ለመኖር የተገደደው ሩሲያዊው ጋዜጠኛ አንድሬይ ሶልዳቶቭ።
“በዚህ ረገድም የጠለቀ እውቀት ስላለው የፖለቲካ ተቃዋሚዎቹን በማስወገድ ረገድ ከፍተኛ ችሎታ አለው” ሲልም አክሏል።
በዘንድሮው የሩሲያ ምርጫ በተፎካካሪነት የቀረቡት ሌሎች ሦስት ዕጩዎች ሲሆኑ፣ ከመካከላቸው አንዳቸውም ፑቲንን የሚገዳደሩ አይደሉም።
ሁሉም ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ለፑቲን እንዲሁም ለዩክሬን ጦርነት ያላቸውን ድጋፍ በግልጽ ያሰሙ ናቸው።
የፕሬዝዳንት ፑቲንን ሥልጣን ሊገዳደሩ ይችላሉ የሚባሉ ተቃዋሚዎች ታስረዋል፣ ተገድለዋል ወይም እንዲወገዱ ተደርገዋል። ክሬምሊን በእነዚህ እስሮችም ሆነ ግድያ ውስጥ እጄ የለበትም ይላል።
ምርጫው ሊካሄድ አንድ ወር ሲቀረው ነው ፑቲንን በሰላ በመተቸት የሚታወቀው ተቃዋሚው የ47 ዓመቱ አሌክሲ ናቫልኒ በእስር ቤት ሳለ ሕይወቱ አልፎ የተገኘው።
ፖለቲከኛው በማጭበርበር፣ ፍርድ ቤትን በመዳፈር እንዲሁም በጽንፈኝነት ተከሶ የረጅም ጊዜ የእስር ቅጣት ላይ ነበር። ለእስር ናቫልኒ የበቃው በርካቶች በፖለቲካ ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ።
“ፑቲን ተቃዋሚዎቻቸውን በማጣጣል የታወቁ ናቸው” ይላል ሶልዳቶቭ።
“በፖለቲካው ትልቅ ስፍራ ያላቸው ሰዎች ሲገደሉ ፑቲን የሚሰጡት ምላሽም ‘ኢምንት ናቸው’ የራሳቸውን እውቅ እና ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ ‘ለምን እገድላቸዋለሁ?’ እያሉ ይጠይቃል። ክሬምሊንም እነዚህን ምክንያቶች በማቅረብም ይታወቃል።
በርካታ ታዋቂ የፑቲን ተፎካካሪዎች ከፖለቲከኞች እስከ ጋዜጠኞች ሞተዋል።
ባለፈው ዓመት ነው የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር መሪ ይቭጌኒ ፕሪጎዢን ፑቲን ላይ ካመጸ ከጥቂት ወራት በኋላ በአውሮፕላን አደጋ ሕይወቱ አለፈ።
በአውሮፓውያኑ 2015 ፑቲንን በግልጽ በመተቸት የሚታወቀው ፖለቲከኛው ቦሪስ ኔምትሶቭ ከክሬምሊን አቅራቢያ ባለው ድልድይ ተመትቶ ተገደለ። እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2006 የቼቺኒያ ጦርነትን በሰላ ሁኔታ በመተቸት የምትታወቀው ጋዜጠኛዋ አና ፖሊትኮቭስካያ በሞስኮ በጥይት ተመትታ ተገኘች።
“ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሚገደሉባት እና በሚታሰሩባት አገር ውስጥ መኖር በጣም አስፈሪ ነው” ይላል ሶልዳቶቭ።
“ለሥነ ልቦናም አስፈሪ ነው። ሕዝቡ የክሬምሊንን ትረካ አምኖበት ሳይሆን ከሁኔታዎች ጋር ራስን አጣጥሞ ለመኖር ነው” ሲል ይገልጻል።
ፑቲን በሕዝቡ ውስጥ የሚነሱ የግለሰቦችንም ተቃውሞ ለመቆጣጠር ሞክረዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን የ2022 ወረራ ተከትሎ ክሬምሊን በአገሪቱ ውስጥ አዲስ የሳንሱር ሕጎችን አስተዋውቋል።
በዚህም የሩሲያን ጦር ማጣጣል የሚሉ አዳዲስ ወንጀሎች እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጡ ሆነዋል። በእነዚህም ሕጎች መንግሥትን የሚጻረሩ ስሜቶችን ለመግታት ተጠቅመውበታል ተብሏል።
“በአሁኑ ወቅት ቢቢሲ ወይም ራዲዮ ፍሪ ዩሮፕ ስለ ሩሲያ መዘገባቸው አይደለም፤ በርካቶች በሩሲያ የሚያዩትን ነገር ወዲያውኑ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ይለጥፉ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለማችን ሕዝብ ይጋራዋል” ይላል ሶልዳቶቭ።
“ፑቲን አገሪቷ ያለችበትን ተጋላጭነት ይረዳዋል። ለዚያም ነው ሁሉንም ዓይነት ተቃውሞ ለማፈን የትኛውንም ነገር ለማድረግ ወደኋላ ማለት እንደሌለበት የሚያውምነው። ምክንያቱም የሚቀጥለው አብዮት ሁለት ሰዎች ወይም ታዳጊዎች በመንገድ ላይ ተቃውሞ በማሰማታቸው ሊጀምር ይችላል” በማለትም ያስረዳል።

2. የዩክሬን ጦርነት
ፑቲን ከምርጫው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው የሩሲያ ጦርነት እንደተጠበቀው ድሉ ፈጣን አልሆነም። ነገር ግን ፑቲን አሁንም ቢሆን የጦርነቱን መጓተት ለራሳቸው ፍላጎት እያዋሉት እንደሆነ በበርሊን መቀመጫቸውን ያደረጉት ሩሲያዊቷ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶ/ር ኢካተሪና ሹልማን ያስረዳሉ።
“ጦርነቱ ሲጀመር ሰፋ ያለ እና እንደ ክራይሚያ አጭር ሊሆን እንደሚችል ነበር የታሰበው፤ ነገር ግን በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ወይም ደም አፋሳሽ አይሆንም እንደተባለው አልሆነም። ጦርነቱ ሩሲያውያን ለራሳቸው፣ ለውጭው ዓለም እንዲሁም ለመሪያቸው ያላቸውን አመለካከት የቀየረ ነው” ይላሉ።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ስትጀምር ሌላው ዓለም በደነገጠበት መልኩ አይደለም ሩሲያውያን ያዩት፣ ቀለል አድርገው ነበር የተመለከቱት።
“በርካቶች ሰንደቅ ዓላማቸውን አውጥተው ሲያውለበልቡ የጫጉላ ሽርሽር ላይ የነበሩ ነው የሚመስሉት። በኋላ ግን ብሔራዊ ውትድርና ተጠናክሮ ሲቀጥል፣ የሕዝቡም ጭንቀት እና ፍራቻ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ። ለጦርነቱም የሚደረገው ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆለቆለ” ይላሉ።
ሶልዳቶቭም በፖለቲካ ሳይንቲስቷ ትንተና ይስማማል፤ ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ እያደረገችው ላለው ጦርነት ድጋፍ መቀነሱን ተከትሎ ፑቲን ትረካውን ቀይረውታል ይላል።
“አሁን ጦርነቱ ከዩክሬን ጋር አይደለም። ጦርነቱ ይልቁንም እየተደረገ ያለው ከምዕራባውያን ጋር ነው። ይህም ሁኔታ ሩሲያውያን እንዲኮሩ አድርጓቸዋል። ምክንያቱም ሩሲያ እያሸነፈች ያለችው ትንሿን ዩክሬን ሳይሆን፣ እየተዋጋች ካለው በጣም ትልቁ ተገደዳሪ ጋር ነው በሚል ነው” ይላል።
ከሳምንታት በፊትም ፑቲን ባደረጉት ዓመታዊ ብሔራዊ ንግግራቸው፣ ምዕራባውያን አገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን እንዳይልኩ አስጠንቅቀዋል።
“እኔን ጨምሮ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሁሉም ሕዝብ የሩሲያ ኢምፓየር (ግዛት) በዓለም ላይ ብቸኛው በሰላም የተገነባ እንደሆነ ነው በትምህርት ቤቶች የተማርነው” የሚለው ሶልዳቶቭ “ሁሉም ሊያጠቃን ይፈልጋል እናም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሊወረን ወደ ድንበራችን እያቀና ነው የሚለው ትረካ በርካቶች የሚያምኑት ነው” ይላል።
ሶልዳቶቭ በተጨማሪ ምዕራባውያን በዩክሬን ያለው ጦርነት ሌላው ዓለም ለምን ግድ ይሰጠዋል? የሚለውን ለማስረዳት በቂ ሥራ አልሠሩም ብሎ ያምናል።
“በአፍሪካም ሆነ በደቡብ አሜሪካ ያሉ ሕዝቦች ለምን የዩክሬን ጦርነት ሊያስጨንቃቸው እንደሚገባ አልተረዱትም። ይህንንም ክፍተት ፑቲን ተጠቅመውበታል” ይላል።
“ፑቲን በሶቭየት ኅብረት አሻራ ላይ በመመሥረት ረገድ የራሳቸውን ሚና በመጫወት ይታወቃሉ። ከዚህም ታሪካዊ ዳራ ጋር ተያይዞ ነው አንዳንዶቹ አገራት የመሠረተ ልማት እና ወታደራዊ እርዳታ ለመስጠት የጠየቁት” ይላል።

3. እያደገ ያለው የሩሲያ ምጣኔ ሀብት
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ምዕራባውያኑ ታይቶ የማይታወቅ ማዕቀብ አዥጎድጉደውባታል። ነገር ግን ሩሲያ እንደተጠበቀው ሳይሆን በአውሮፓ ፈጣን የምጣኔ ሀበት እድገት እያስመዘገበች መሆኑ በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን ያስደነገጠ ሆኗል።
“የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። እናም ምዕራቡን ዓለም ተገዳድሮ አገሪቱን በምጣኔ ሀብት እያስመነደገ የሚገኝ በሚልም ፑቲንን ተወዳጅ አድርጓቸዋል” ሲልም የቢቢሲ የሩሲያ የቢዝነስ ዘጋቢ አሌክሲ ካልምኮቭ ያስረዳል።
የሩሲያ ምጣኔ ሀብት ይሽመደመዳል ብለው ብዙዎች ቢጠብቁትም በተቃራኒው በ2.6 በመቶ ማደጉን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) መረጃ ያሳያል። የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እያደገ ያለው የ300 ቢሊዮን ዶላር ንብረት እገዳን ጨምሮ በርካታ የምዕራቡ ዓለም ማዕቀቦች ባሉበት ሁኔታ ነው።
ነገር ግን እነዚህ ማዕቀቦች በመላው ዓለም ባሉ አገራት ተግባራዊ አልሆኑም። ይህም ሩሲያ እንደ ቻይና፣ ሕንድ እና ብራዚል ካሉ አገራት ጋር በነጻነት እንድትገበያይ አስችሏታል። እንዲሁም የሩሲያ ጎረቤት የሆኑት ካዛኪስታን እና አርሜንያ የምዕራባውያኑን ማዕቀብ ለማለፍ መንገድ እየፈለጉላት ይገኛሉ።
“ሩሲያ ባለ ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ናት። እሷን ለማንበርከክ በርካታ አስርት ዓመታት የሚፈጅ ማዕቀብ ያስፈልጋል ይህ በአሁኑ ወቅት የለም” ሲሉም ካልምኮቭ ይገልጻል።
“ሩሲያ ሸቀጦችን ወደ ውጭ በመላክ ገንዘብ ታገኛለች እናም በመሠረቱ የወደደችውን ለመሸጥ ነጻ ናት” ሲልም ጋዜጠኛው ይናገራል።
“የነዳጅ ማዕቀብ ለይስሙላ የተጣለ ነው። አገሪቷ እየሸጠች ያለችው የተፈጥሮ ጋዝ፣ እህል፣ የኑክሌር ነዳጅ በዋና ሸሟቾቹ የአውሮፓ ኅብረት አገራት ምንም ዓይነት ማዕቀብ አልተደረገባቸውም” ይላል።
ምንም እንኳን ዕቃዎች ዋጋቸው ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር የአራት ዕጥፍ ብልጫ ቢያሳይም፣ በቀላሉ መገኘታቸው የበለጠ ጠቃሚ እንደሆነ ዶ/ር ሹልማን ያስረዳሉ።
“ሩሲያውያን የዋጋ ጭማሪ የለመዱት ነገር ነው። ዋናው በአገር ደረጃ ያለን ፍራቻ የዋጋ ግሽበት ሳይሆን እጥረት ወይም መታጣት ብቻ ነው። በመደርደሪያዎች ላይ ዕቃዎች እና ሸቀጦች ሲታጡ ያ የሶቪየት ኅብረት መጨረሻ አስፈሪው ወቅትን የሚያስታውስ ነው” ይላሉ።
ይህ ግን ለዘላላም አይቆይም…
ምንም እንኳን ፑቲን ከምንጊዜውም በበለጠ ኃያል ቢመስሉም ዶ/ር ሹልማን ግን ሁሉም ነገር ማብቂያ አለው ይላሉ።
ሩሲያ ከአራት ዓመታት በፊት ባደረገችው ሕዝበ ውሳኔ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ሆኗል። በዚህም የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ፑቲን ለሁለት ተጨማሪ ስድስት ዓመታት የሥልጣን ዘመን እንዲያገለግል ፈቅዶላቸዋል። ይህም ማለት ፕሬዝዳንት ፑቲን እስከ 2036 ድረስ ፕሬዝዳንት መሆን ይችላሉ። በዚህያም ወቅት የ83 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ይሆናሉ።
“ጡረታ መውጣት የሚሆን አይመስለኝም። በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ሥልጣን ላይ እያለ ሞቶ እሱን በሚመስለው ሰው መተካት ነው” ይላሉ ዶ/ር ሹልማን።
ሆኖም ይህ ላይሆን እንደሚችል ገልጸው “የሩሲያ ሥርዓት እያረጀ እንደሆነ እና የዚህንም ሥርዓት እየመራ ያለው ሰው የበለጠ ጠንካራ ወይም ወጣት እየሆነ ካለመሄዱ አንጻር ሁሉም መረጋጋት በአንድ ሰው ላይ ያተኮረ ነው፤ ይህም ለዘላለም መኖር አይችልም” ብለዋል።