
ከ 3 ሰአት በፊት
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጦርነት በኋላ ጋዛን ለማስተዳደር እና ጸጥታውን ለማረጋገጥ ስለሚኖር እቅድ ለመወያየት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አቀኑ።
ብሊንከን በሳዑዲ አረቢያ ከአረብ መሪዎች እና ከግብፅ ጋር የሚኖራቸው ንግግር ዘላቂነት ያለው ሰላም በማምጣት ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል።
ብሊንከን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ያቀኑት የእስራኤል ኃይሎች በጋዛ ከተማ በሚገኘው አል ሺፋ ሆስፒታል አካባቢ የከፈቱት ዘመቻ መቀጠሉንና በርካታ የአየር ጥቃቶች መፈፀማቸውን የዓይን እማኞች መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
ቀደም ብሎ የእስራኤል ጦር ጥቃቱን ከከፈተበት ከሰኞ ዕለት ጀምሮ 90 ታጣቂዎችን መግደሉን አስታውቋል።
በሌላ በኩል በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረስ እና ታጋቾች ለማስለቀቅ የሚደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር በኳታር እንደቀጠለ ነው።
የሳዑዲ አስተዳደርን ለማግኘት ረቡዕ ዕለት ጂዳ የገቡት ብሊንከን፣በጋዛ ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ወደ ቀጠናው ሲያመሩ ይህ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።
ጂዳ ሲገቡም የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን በሆኑት ማዚን አል ሂማሊ ጨምሮ በሌሎች ባለሥልጣናት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ረቡዕ ምሽትም የሳዑዲውን አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንን በቤተ መንግሥታቸው እንደሚያገኙ ተነግሯል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር፣ሚኒስትሩ እስራኤልና ሐማስ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱ እና በጋዛ አፋጣኝ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ይወያያሉ ብለዋል።
በዚህ ሳምንት የወጣው በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የምግብ ዋስትና ጥናት በጋዛ 1.1 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ እና በጠኔ እየተሰቃዩ መሆናቸውን ያመለከተ ሲሆን በተለይ በሰሜኑ ክፍል እስከ ግንቦት ባሉት ጊዜያት ሰው ሰራሽ ረሃብ እንደሚከሰት አስጠንቅቋል።
- በጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ እንደሆነ ዶ/ር ቴድሮስ ተናገሩ5 መጋቢት 2024
- ጥቂት “በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ተባባሪ አልሆንም” ብሎ ራሱን ስላቃጠለው የአሜሪካው አየር ኃይል አባል9 መጋቢት 2024
- “በረመዳን ፆም በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን እየተራቡ እና እየሞቱ ነው”13 መጋቢት 2024
ብሊንከን ወደ ቀጠናው ላደረጉት ጉዞ ከያዟቸው አጀንዳዎች መካከል ሐማስ ከዚህ በኋላ እንዳይመራ፣ ጥቅምት ወር ላይ በእስራኤል ላይ የፈፀመውን ጥቃት እንዳይደግም እና ፍልስጤማውያንም ከእስራኤል የደኅንነት ዋስትና እንዲያገኙ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።
ከዚህም በተጨማሪ በቀጠናው ዘላቂ ሰላምን ማስፈንን ጨምሮ በጋዛ የድኅረ ጦርነት እቅድ ላይ እንደሚወያዩ ሚለር ተናግረዋል።
ብሊንከን ሐሙስ ዕለት የግብፅ መሪዎችን ለማግኘት ወደ ካይሮ ያቀናሉም ተብሏል።
አሜሪካውያን ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውና ከ17 ዓመት በፊት በሐማስ ተባሮ የወጣው የፍልስጤም አስተዳደር ( ፒኤ) ወደ ጋዛ እንዲመለስ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ፒኤ ጋዛን ይቆጣጠር የሚለውን ሃሳብ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል።
አንዳንድ እቅዱን የሚያውቁ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ውጤት ባለመኖሩ፣ የሰብዓዊ ቀውሱ በመባባሱ በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል ያለው ግንኙነት ያበቃለት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆኖም የአሜሪካ አስተዳደር ውጥኑን ለማሳካት ተስፋ ሰንቋል።

ብሊንከን አርብ ዕለት ወደ እስራኤል ያቀናሉ።
እንደ ቃል አቀባያቸው ከሆነ ሚኒስትሩ ከእስራኤል መሪዎች ጋር ታጋቾቹ እንዲለቀቁ ስለሚደረገው ድርድር እና በራፋህ ሰላማዊ ሰዎችን መጠበቅን ጨምሮ የሐማስን ሽንፈት ለማረጋጋጥ ባላቸው ቁርጠኝነት ላይ ይወያያሉ።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች በተጠለሉባት በደቡባዊ ከተማዋ ራፋህ ላይ ጥቃት መክፈት “ ስህተት “ ሊሆን እንደሚችል እስራኤልን አስጠንቅቀዋል።
ሆኖም ማክሰኞ ዕለት ኔታንያሁ እስራኤል በራፋህ ያሉ የሐማስ ተዋጊዎችን ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆኗን እና ለዚህም ከምድር ጥቃት ውጭ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ተናግረዋል።
በሐማስ እንደሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ከሆነ ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ ከ31 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የእስራኤል እና ሐማስ ግጭት የጀመረው ጥቅምት ወር ላይ የሐማስ ታጣቂዎች በደቡባዊ የእስራኤል ድንበር ዘልቀው በመግባት 1 ሺህ 200 የሚሆኑ ሰዎችን ከገደሉ እና 253 ሰዎችን አግተው ከወሰዱ በኋላ ነበር።