የጀርመን ተጫዋች የአዲዳስ ዓርማ ያለበት መለያ ለብሶ
የምስሉ መግለጫ,አዲዳስ ከ70 ዓመታት በላይ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ትጥቆችን ሲያቀርብ ቆይቷል

ከ 3 ሰአት በፊት

የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ለአገሪቱ ብሔራዊ ቡድን ትጥቆችን ከሚያቀርበው ከአዲዳስ ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጦ ሌላ አቅራቢ በመለወጡ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ተቃውሞ ገጠመው።

የእግር ኳስ ማኅበሩ ለበርካታ ዓመታት ለብሔራዊ ቡድኑ ትጥቆችን ሲያቀርብ የነበረውን የጀርመን ኩባንያ አዲዳስን በመተው ከአውሮፓውያኑ 2027 ጀምሮ የአሜሪካው ናይኪ ትጥቆችን እንዲያቀርብ ተስማምቷል።

ይህንን ውሳኔ ከተቃወሙት ውስጥ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ሚኒስትር ሮበርት ሃቤክ በብሔራዊ ቡድኑ ትጥቆች ላይ በተወሰነ ደረጃ “አገር ወዳድነት” እንዲታይ ይፈልጉ እንደነበር ሲናገሩ፤ የጤና ሚኒስትሩ ካርል ሉተርባህ ደግሞ ውሳኔውን “የተሳሳተ” ብለውታል።

የጀርመን የእግር ኳስ ማኅበር ግን ስምምነቱ መሠረት ያደረገው የሚያስገኘውን የገንዘብ ጥቅም እና በዝቅተኛ ደረጃ ያለውን የአገሪቱን እግር ኳስ መደገፍን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ገልጿል።

የጀርመን የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት የሆነው አዲዳስ፣ ለአገሪቱ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከ70 ዓመታት በላይ ትጥቆችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

አሁን ማኅበሩ የትጥቅ አቅራቢነቱን ውል ወደ አሜሪካው ድርጅት ናይኪ ሲያዞር፣ ናይኪ በየዓመቱ 108 ሚሊዮን ዶላር ለማኅበሩ ለመክፈል ተስማምቷል። ይህም አዲዳስ ከሚከፍለው 50 ሚሊዮን ዶላር በእጥፍ የሚበልጥ ነው።

በእግር ኳስ ማኅበሩ እና በናይኪ መካከል ሐሙስ ዕለት ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የተለያየ አቋም ያላቸው የጀርመን ፖለቲከኞች ተቃውሞ እና ትችት አቅርበዋል።

“የጀርመን ብሔራዊ ቡድን መለያን ከአዲዳስ አርማ ውጪ ላስበው አልችልም” ያሉት የምጣኔ ሀብት ሚኒስትሩ ሃቤክ “ለእኔ የጀርመን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት እና አዲዳስ አንድ ላይ የሚቆሙ የጀርመን መለያዎች ናቸው” ሲሉ ከናይኪ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተችተዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ሉተርባህ በበኩላቸው በኤክስ (የድሞው ትዊተር) ላይ ባሰፈሩት አስተያየት “ውሳኔው ንግድ ባህልን እና የአገር መለያን ያበላሸበት የተሳሳተ ውሳኔ ነው” ብለዋል።

የባቫሪያ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ማርከስ ሶደር ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ ሁልጊዜም የሚጫወተው ባለሦስት መሥመሩን የአዲዳስ አርማ ያለበትን ትጥቅ ለብሶ ነው፤ “ይህም ኳስ ድቡልቡል መሆኗን እና እግር ኳስ የ90 ደቂቃ ጨዋታ የመሆኑን ያህል ግልጽ ነበረ” በማለት ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

ጨምረውም የጀርመን እግር ኳስ “ዓለም አቀፍ ንግድ ተቋማት የሚያካሂዱት ፉክክር መጠቀሚያ መሆን የለበትም፤ ንግድ ሁሉም ነገር አይደለም” ብለዋል።

የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ለቀረቡበት ተቃውሞዎች በኤክስ ገጹ ላይ በሰጠው ምላሽ፣ ከ70 ዓመታት በኋላ የቡድኑን ትጥቅ አቅራቢ መቀየር “መሠረታዊ ለውጥ” እንደሆነ እና ቢሆንም ግን “የሚያስከፋ” አይደለም በማለት ውሳኔውን ተከትሎ የተፈጠረውን ስሜት እንደሚረዳ ገልጿል።

አክሎም በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ከታች ጀምሮ ያሉ የእግር ኳስ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው በማንሳት “ከ24 ሺህ በላይ የእግር ኳስ ቡድኖች፣ 2.2 ሚሊዮን ተጫዋቾች፣ በርካታ በጎ ፈቃደኞች እና 55 ሺህ የሚደርሱ ዳኞችን” እንደሚደግፍ አመልክቷል።

“ለእነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት የእግር ኳስ ማኅበሩ ከገቢው አንጻር መወሰን ነበረበት። ግልጽ በሆነ እና አድልዎ ባልነበረበት የጨረታ ሂደት ናይኪም የበለጠ ገንዘብ አቀርቧል” በማለት ውሳኔውን አስረድቷል።

ከናይኪ ጋር የተደረሰው ስምምነት ይፋ የሆነው በጀርመን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ውድድር ዩሮ2024 ሊካሄድ ወራት ሲቀሩ ነው። በዚህ ውድድር ላይ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከኑረምበርግ አቅራቢያ የሚገኘውን የአዲዳስ ዋና መሥሪያ ቤት እንደመሰብሰቢያ ማዕከሉ ይጠቀማል።

አዲዳስ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ ከእግር ኳስ ማኅበሩ ጋር የነበረው ስምምነት መቋረጥን በተመለከተ ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ይህ የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ለብሔራዊ ቡድኑ ናይኪ ትጥቅ እንዲያቀርብ ከተስማማ በኋላ ከአገሪቱ ፖለቲከኞች ተቃውሞ የተሰማው፣ የእንግሊዝ ፖለቲከኞች ናይኪ ለአገራቸው ብሔራዊ ቡድን ያቀረበውን ትጥቅ እየተቹ ባለበት ጊዜ ነው።

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ሳይቀሩ ናይኪ ለብሔራዊ ቡድኑ ባቀረበው ትጥቅ ላይ ያለው ዓርማ ቀለም መለወጥን ተቃውመው አስተያየት ሰጥተዋል።

ነገር ግን የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር የአሁኑ ዲዛይን ጥቅም ላይ ሲውል የመጀመሪያ ጊዜ አለመሆኑን በመግለጽ፣ የተለያዩ ቀለማት ሲጠቀም መቆየቱን አንስቶ ትችቱን ተከላክሏል።