
ከ 4 ሰአት በፊት
እንደ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ በመላው ዓለም በየቀኑ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች ይያዛሉ።
ነገር ግን በትክክል በወሲብ የሚተላለፍ በሽታ ምንድን ነው? ዓይነቶቹ እና ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው? ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?
የአባላዘር በሽታ (በወሲብ የሚተላለፍ ኢንፌክሽን) ማለት በወሲባዊ ግንኙነት አማካይነት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ የሚተላለፍ በሽታ ማለት ነው።
እነዚህ በሽታዎች በአብዛኛው ምልክት አያሳዩም፤ ለመለየትም ከባድ ናቸው።
እነዚህ የአባለዘር በሽታዎች በአመዛኙ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ሲሆን፤ አልፎ አልፎም በወሲብ ወቅት በሚፈጠር የቆዳ ንክኪ አማካይነት ሊተላለፉ ይችላሉ።
አንዳንዶቹም በእርግዝና ወቅት፣ በወሊድ እና በጡት ማጥባት ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ ይተላለፋሉ።
ሌሎቹ ደግሞ ደም በመስጠት ወይም መርፌ በጋራ በመጠቀም ይተላለፋሉ።
እነዚህ በሽታዎች ካንሰርን ጨምሮ የዳሌ አጥንት ህመም፣ ከማህጸን ውጪ እርግዝና መሃንነትን የመሰሉ የጤና ቀውሶችን የማስከተል ዕድል አላቸው።
- አሳሳቢ እየሆኑ የመጡት አዳዲሶቹ የአባላዘር በሽታዎች30 ታህሳስ 2019
- ለወሲብ ትክክለኛው ዕድሜ የቱ ነው?15 ጥር 2019
- በየቀኑ አንድ ሚሊየን ሰው በአባላዘር በሽታ ይያዛል8 ሰኔ 2019
የአባላዘር በሽታ ዓይነቶች
ከ30 የሚበልጡ የተለያዩ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች እና ተዋህሲያን በወሲብ ንክኪ ይተላለፋሉ።
አንዳንድ ሰዎች በአንድ ጊዜ በርከት ባሉ በወሲብ በሚተላለፉ በሽታዎች ሊያዙ ይችላሉ።
በስፋት የሚታወቁት ቂጥኝ፣ ጨብጥ፣ ክላሚዲያ፣ ታራይኮሞኒያሲስ ናቸው። እነዚህ በሽታዎች በሙሉ የሚድኑ ናቸው።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
የአባላዘር በሽታዎች ምልክት አያሳዩም አሊያም አነስተኛ ምልክቶችን ብቻ አላቸው።
ሰዎች እንደተያዙ ሳያውቁ ነገር ግን በሽታው በውስጣቸው ሊኖር ይችላል።
ነገር ግን ካለ ምልክትም ቢሆን እነዚህ በሽታዎች በወሲብ ተላልፈው ጎጂ ይሆናሉ።
ምልክት ካሳዩ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡
- በወንድ እና በሴት ብልት ያልተለመደ ፈሳሽ መውጣት
- በብልት አካባቢ ህመም እና ቁስል መከሰት
- በተደጋጋሚ መሽናት ወይም ህመም መሰማት
- ብልት አካባቢ ማሳከክ እና መቅላት
- አፍ አካባቢ ውሃ መቋጠር እና ህመም
- የሴት ብልት እንግዳ የሆነ ጠረን
- ፊንጢጣን ማሳከክ፣ መድማት እና ህመም
- የሆድ ህመም

የአባላዘር በሽታዎች ለምን ተስፋፉ?
በ2020 የዓለም የጤና ድርጅት 374 ሚሊዮን ሰዎች ቢያንስ በአንድ የአባላዘር በሽታ ተይዘዋል ሲል ይገምታል።
ከእነዚህ ውስጥም በትራይኮሞኒያሲስ 156 ሚሊዮን ሰዎች፣ በክላሚዲያ 129 ሚሊዮን ሰዎች፣ በጨብጥ 82 ሚሊዮን ሰዎች፣ በቂጥኝ ደግሞ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች እንደተያዙ ገልጿል።
በ2016 ከ490 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ብልት አካባቢ የሚከሰት ህመም እንዳለባቸው የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ጠቁሟል።
300 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ካንሰር የሚያመጣው ኤችፒቪ የተባለ በሽታ አለባቸው ተብሎ ይታመናል።
የዓለም የጤና ድርጅት የኤችአይቪ፣ የሄፒታይተስ እና የአባላዘር በሽታዎች ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድራ ኤልቪራ ዊ “ወሲብ የሥነ-ሕይወት ፍላጎት ነው። እንደ መጠጣት እና መመገብ ማለት ነው። የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ አካል ነው” ይላሉ።
“ወሲብ ሲፈፀም በሽታ ሊተላለፍ ይችላል። ለዚህም ነው የበሽታው መያዝ ዕድል ከፍተኛ የሆነው።”
ዶ/ር ዊ የአባላዘር በሽታዎች በአብዛኛው ምልክት ባለማሳታቸው ምክንያት ሰዎች ሳያውቁ በሽታውን ሊያስተላልፉ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ።
የእነዚህ በሽታዎች መስፋፋት እየጨመረ የመጣው በድንገት ወሲብ የመፈፀም ልማድ በመጨሩ እና አልፎም ሰዎች በቀላሉ ወሲብ ማድረግ መቻላቸው ነው ይላሉ።
አክለውም ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ ማበጀት መስፋፋቱን የሚጠቅሱት ዶክተር ዊ የፍቅረኛ አጣማሪ መተግበሪያዎች [ዴቲንግ አፕስ] መብዛትንም እንደ አንድ ምክንያት ያነሳሉ።
ምንም እንኳ በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ያላገቡ ወጣቶች ድንገት ወሲብ ማድረግ እየቀነሱ መምጣታቸውን ቢጠቁምም ኮንዶም የመጠቀም ልምድ ግን እየቀነሰ ነው።
ለኤችአይቪ ምንም ህክምና ባልነበረበት ጊዜ ሰዎች ድንገት ወሲብ የማድረግ ልምዳቸውን እየተዉ በተለይ ኮንዶምን ይጠቀሙ እንደነበር ዶ/ር ዊ ይናገራሉ።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ሰዎች በኤችአይቪ ቢያዙም ህክምና ተከታትለው እንደሚሻላቸው በማመናቸው “ኮንዶም መጠቀም ቀንሷል” ይላሉ።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ በ2022 ብቻ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች በኤችኤእቪ ተይዘዋል ይላል።
ኤችአይቪ እንደያዛቸው ባለማወቅ እና ህክምና ባለማግኘት ወይም በመዘግየት በየዓመቱ ከ600 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው ያልፋል።
ራስን እንዴት መከላከል ይችላሉ?
ዶ/ር ዊ “እባካችሁ ኮንዶም ተጠቀሙ፤ በወሲባዊ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች የሚጠብቃችሁ እሱ ነው” ይላሉ።
“ከማታውቁት ሰው ጋር ወሲብ የምትፈጽሙ ከሆነ ወይም ድንገተኛ ግንኙነት ከሆነ ልትጠነቀቁ ይገባል። ኮንዶም እንዴት መጠቀም አንዳለባችሁ ማወቅ እና እርካታ እንዴት ማግኘት እንዳለባችሁ ማወቅ ያስፈልጋል” ብለዋል።
የላቴክስ ኮንዶሞችን በአግባቡ መጠመቀም በበሽታዎቹ ከመያዝ አሊያም ከማስተላለፍ በእጅጉ ሊከላከል ይችላል የሚሉት ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ እንደማያግደው ግን ያስጠነቅቃሉ።
ሰዎች የላቴክስ ኮንዶሞች አለርጂ ካለባቸው ፖሊዩሬቴን ኮንዶሞችን እንዲጠቀሙ ይመከራሉ።
የአባላዘር በሽታዎች ምልክቶች ከታዩ ወደ ጤና ተቋማት በአፋጣኝ በማቅናት መመርመር እና ህክምናውን ማግኘት ወሳኝ እንደሆነም ይናገራሉ።
ዶ/ር ዊ “ወደ ፋርማሲ ሄዳችሁ ራሳችሁን ለማከም አትወስኑ፤ ይሄ ምንም አይረዳችሁም። በአግባቡ ካልታከማችሁ እንደ መካንነት ያለ ከባድ ጣጣ ሊኖረው ይችላል” ይላሉ።
“የአባላዘር በሽታዎችን ችላ ማለት ለጤና አደገኛ ነው። የሴቶችን የመራቢያ አካል ሊጎዱ ይችላሉ። ቂጥኝ እና ጨብጥ ካልታከሙ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን የበሽታው ሴት ተጠቂዎች አንድ መሃንነትን ያስከትላል፤ በእርግዝና ወቅትም ከባድ እክል ይኖረዋል” በማለት ያብራራሉ።
በእርግዝና ወቅት ቂጥኝ በየዓመቱ 355 ሺህ ከባድ የወሊድ እክሎችን ሲያስከትል፤ 143 ጨቅላዎች ሕይወታቸው አልፎ ይወለዳሉ እንዲሁም 61 ሺህ ህጻናት ደግሞ ከተወለዱ በኋላ ሕይወታቸው ያልፋል። ኤችፒቪ ደግሞ በሚያስከትለው የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምክንያት 342 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸው ያልፋል ሲሉ አክለዋል።
የአባላዘር በሽታ ህክምናዎች
በባክቴሪያ እና በተህዋሲያን የሚከሰቱ የአባላዘር በሽታዎች በፀረ ትህዋሲያን (አንቲባዮቲክስ) ማከም ይቻላል። ነገር ግን በቫይረስ የሚከሰቱት ኤችፒቪን የመሰሉ በሽታዎችን ግን መዳን የሚችሉ አይደሉም።
ነገር ግን ምልክቶቹን ለማከም እና እንዳይስፋፋ ለማድረግ የሚያግዙ በርካታ መድኃኒቶች አሉ።
ነገር ግን ኤችፒቪ እና ሄፒታይተስ ቢ ክትባቶች አሏቸው።
ዶ/ር ዊ የዓለም የጤና ድርጅት የጨብጥ ክትባት ለማበልጸግ እየሠራ ነው ይላሉ። የኮቪድ 19 ክትባት የተገኘበትን ዘዴ በመከተልም ብልት ላይ የሚከሰት ሽፍታን ለመፈወስም ክትባት እየበለጸገ እንደሆነ ተናግረዋል።
የክላሚዲያ ክትባት ለማግኘትም ጅምር ሥራዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዶ/ር ዊ፤ ለቂጥኝ በሽታም ክትባት ማግኘት የሚያስችሉ መሠረታዊ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው።
በሽታዎቹን ለመቆጣጠር የአገራት ሚና
በአብዛኛው ዓለም የአባላዘር በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር መንግሥታዊ መርሃ ግብሮች የበጀት ውስንነት አለባቸው።
“የአባላዘር በሽታዎች መጥፎ ስም በማግኘታቸው ምክንያት ትኩረት አይሰጣቸውውም። በፖለቲካ ዕይታም ለወሲብ ኢንፌክሽን አገልግሎት ገንዘብ መመደብ ያን ያህል ሳቢ አይደለም፤ በምርጫ ጊዜ ድምጽ አያስገኝም” ይላሉ ዶ/ር ዊ።
መንግሥታት ቀላል እና በአቅም የሚገኝ የህክምና አገልግሎት ማቅረብ እንዲሁም የምርመራ እና ህክምና መንገዶችን ለማመቻቸት ትልቅ በጀት ሊመድቡ ይገባል ሲሉ ያብራራሉ። ይህም አፋጣኝ ምርመራ እና ህክምና እንዲሁም ክትባትን ያካትታል።
“የአባላዘር በሽታዎች እንደ ተላላፊ በሽታ ሙሉ ለሙሉ ችላ ተብለዋል። መጥፎ ስሙን መቀነስ አለብን፤ እናም እንደማንኛውም ተላላፊ በሽታ ልናክመው ይገባናል” ይላሉ።