አያቶላህ ኾሚኒ ከዓመታት ስደት በኋላ አብዮቱን ተከትለው ወደ አገራቸው ሲገቡ
የምስሉ መግለጫ,አያቶላህ ኾሚኒ ከዓመታት ስደት በኋላ አብዮቱን ተከትለው ወደ አገራቸው ሲገቡ

ከ 4 ሰአት በፊት

ኢራን የእስላማዊ አብዮቷን 45ኛ ዓመት እያከበረች ነው። በ1979* ለለውጥ የታገሉ ሰዎችም ሐሳባቸውን እየሰነዘሩ ነው።

አንዳንዶች ቁጭት ላይ ናቸው፤ ሌሎች ደግሞ ኢራን ትክክለኛው መስመር ላይ ናት ብለው ያስባሉ።

“ከ45 ዓመታት በፊት የትኛውም አብዮተኛ አንድ ቀን እንደ ወንጀለኛ እቆጠራለሁ ብሎ አያስብም” ይላሉ ሳዴግ ዚባካላም።

በ1979 አብዮት ሲፋፋም ወደ ጎዳና ወጥተው ድምፃቸውን ካሰሙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢራናውያን መካከል አንዱ ናቸው።

እነሆ አብዮቱ 45 ዓመት ደፈነ። በርካታ ወጣቶች ግን የኢራን መሪዎችን እና አብዮቱን የደገፉትን በጥያቄ ወጥረዋቸዋል።

የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ በ2022 በሥነ ምግባር ፖሊሶች ቁጥጥር ሥር ሳለች መሞቷን ተከትሎ የኢራንን አገዛዝ ለመቃወም በርካቶች አደባባይ ወጥተዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ማኅበረሰባዊ ነፃነት መገደቡ እና የኢራን ምጣኔ ሀብት መደቆሱ ሕዝቡ መንግሥት ላይ ያለው ቅሬታ እንዲጨምር አስተዋፅዖ ካበረከቱ ምክንያቶች መካከል ናቸው።

የምዕራቡ ዓለም ኢራን ላይ የጣለው ማዕቀብ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ባለፉት 12 ወራት 43 በመቶ እንዲያሻቅብ አድርጓል።

ከሰሞኑ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን በሚደገፉ አማፂያን ላይ የአየር ጥቃት መፈጸም ጀምራለች።

ወጣቱ ትውልድ አብዮተኞቹ ኢራን ወዴት እየመሯት ነው? የታገሉትስ ለዚህ ነው ወይ? ሲል ይጠይቃል።

በ2022 ኢራን ውስጥ የተቀሰቀሰው አመፅ
የምስሉ መግለጫ,በ2022 ኢራን ውስጥ የተቀሰቀሰው አመፅ

“ግትር ስለሆንኩ አሊያም ከጥላቻ በመነጨ መንፈስ አይደለም ይህን የምለው፤ ኩራት እና ትምክህትም አይደለም። ነገር ግን እንደገና ወደ 1979 ብለመስ ተመለሼ አደርገዋለሁ፤ በአብዮቱ እሳተፋሉ” የሚለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ ያጠናው ዚባካላም ነው።

“ምንድነው የምንፈልገው? ነፃ ምርጫ ነው የምንፈልገው፤ የፖለቲከኛ እሥረኞች እንዳይኖሩ ነው የምንፈልገው፤ አገሪቱን የሚመራው ሰው ያሻውን እንዳያደርግ ነው የምንፈልገው።”

ዚባካላም የኢራን የወቅቱ ችግር ምንጩ መሪዎቹ እንጂ አብዮቱ አይደለም ይላል።

“እኔ እና አኔን የመሰሉ ሰዎች የሠራነው ጥፋት አብዮቱ ነፃነት እና ዲሞክራሲን የመሳሰሉ ግቦቹን እንዲመታ ከማድረግ ይልቅ “ሞት ለአሜሪካ”፣ “ሞት ለእስራኤል”፣ “እስራኤልን እናጠፋታለን” የሚሉ ፀረ-ኢምፔሪያሊስት መፈክሮችን እያሰማን መውጣታችን ነው።”

እሱ እንደሚለው በ1970ዎቹ የታገለለትን ዓላማ አንግቦ አሁንም ለመታገል ዝግጁ ነው።

ባለፈው ዓመት ፖለቲካል ሳይንስ ከሚያስተምርበት የቴህራን ዩኒቨርሲቲ የተባረረው “ሴቶች፣ ሕይወት፣ ነፃነት” በተሰኘው ፀረ-አገዛዝ ተቃውሞ ላይ በመሳተፉ ነው።

ዚባካላም ያስታውሳል። ከ45 ዓመታት በፊት የአብዮቱ መሪ የነበሩት አያቶላህ ሩሆላህ ኾሚኒ ለሕዝባቸው በተደጋጋሚ ቃል የገቡት አንድ ነገር ነበር – ነፃነት።

“ነፃነት የሕዝቦች መብት ነው። አገሪቱ ነፃ መሆኗ ለሁሉም ነፃነት ሊያጎናፅፍ ይገባል። ማንኛውም ሰው ያሻውን ነገር በነፃነት ከመናገር ሊገደብ አይገባም” ይህ ኾሚኒ በስደት ፈረንሳይ እያሉ በ1978 ያሰሙት ንግግር ነው።

የእነዚህ ንግግሮች ዘንድሮ መሰማት በተለይ በአብዮቱ ያልተሳተፉ ሰዎች፣ አሁን መንግሥት አክቲቪስቶች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንዲያጤኑ የሚያደርግ ነው።

ሻህ እና ቤተሰቦቹ በ1970ዎቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለሽርሽር በወጡ ጊዜ የተነሱት ፎቶ
የምስሉ መግለጫ,ሻህ እና ቤተሰቡ በ1970ዎቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለሽርሽር በወጡ ጊዜ የተነሱት ፎቶ

ሻህ እና ኾሚኒ በአብዮቱ የነበራቸው ሚና

ሞሐመድ ሬዛ ፓህላቪ የኢራንን ዘውዳዊ አገዛዝ እየመሩ ለ37 ዓመታት ያክል ቆይተዋል።

በወቅቱ አገሪቱ ምዕራባዊነት የሰፈነባት፣ ምጣኔ ሀብት ያላት፣ በኢራን ጥንታዊ እና ቅድመ-እስላማዊ ታሪክን መልሶ ብሔራዊ ኩራት ለማስረጽ የሚደረግ ሙከራም ነበር።

ሴቶች የመምረጥ መብት ያገኙት በ1960ዎቹ ሲሆን፣ በተነፃፃሪ ከወንዶች እኩል ነፃነት ነበራቸው።

ቴህራን፤ መሸታ ቤቶች ደምቀው የሚታዩባት የድግስ [ፓርቲ] ከተማ ነበረች። የፋርስ ወይን ጠጅ ወደ ተቀረው ዓለም እንደጉድ ይላካል።

ኢራን አንፃራዊ ነፃነት ብትጎናፀፍም የሻህ አገዛዝ አምባገነን እና ዲሞክራሲ የሚጎለው ተብሎ ይተች ነበር።

የሺዓ ሙስሊሞች የእስልምና ሃይማኖትን የሚቃረን ተግባር ይፈጽማሉ ሲሉ ሻህን በተደጋጋሚ ይወቅሷቸዋል። ግራ ዘመም ፓርቲዎች ደግሞ በሰሜናዊ ጎረቤታቸው ሶቪየት ኅብረት ጫና ተነሳስተው እኩልነት እንዲሰፍን ይጠይቃሉ።

እስከ 1978 አጋማሽ ድረስ ኢራናውያንን አንድ የሚያደርግ አብዮት ይመጣል ብለው ያሰቡ እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ነገር ግን አብዮቱ ሲመጣ ግራ ዘመም ምሑራንን፣ ብሔርተኞችን፣ ከሃይማኖት ጫና ነፃ መውጣት አለብን የሚሉትን እና እስላማውያንን ጠቅልሎ ያዘ።

ዓመቱ እየገፋ ሲመጣ የፀረ-ሻህ ተቃውሞዎች ሃይማኖታዊ ቅርፅ እየያዙ መምጣት ጀመሩ። ዓመቱ ሲገባደድ አደባባይ ላይ ይሰሙ የነበሩት መፈክሮች እስላማዊ ሆኑ።

ኾሚኒ ራሳቸውን የእስላማዊ መንግሥት አለቃ አልፎም የልዩነት ጠበቃ አድርገው ለሕዝቡ አቀረቡ።

ሚሊዮኖች እሳቸውን የማይወቀሱ የማይከሰሱ አድርገው ይስሏቸው ጀመር። ኢራንን በቅዳስ ቁርዐን ቃል በተገባው መሠረት የቃል-ኪዳን አገር ሊያደርጉልን ነው አሉ። ኾሚኒ፤ ኢማም ሆኑ።

ኾሚኒ ከ15 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ በ1979 ወደ ኢራን ሲመለሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በእምባ ሲቀበሏቸው በቴሌቪዥን መስኮት ታይተዋል።

በወቅቱ የተቀዱ ቪድዮዎች እንደሚያሳዩት ሕዝቡ መኪናቸውን አላስኬድ ብሎ ይዞ ብጣሽ ጨርቁን እየዘረጋላቸው እንዲባርኩት ይጠብቅ ነበር።

አያቶላህ ኾሚኒ ወደ ኢራን ሲገቡ በርካቶች መንገድ ወጥተው ተቀብለዋቸዋል
የምስሉ መግለጫ,አያቶላህ ኾሚኒ ወደ ኢራን ሲገቡ በርካቶች መንገድ ወጥተው ተቀብለዋቸዋል

ኾሚኒ ኢራን ከመግባታቸው በፊት አንድ ምሽት 4፡00 ሰዓት ላይ ሰዎች ወደ ሰማይ ሲያንጋጥጡ የእሳቸው ፊት ጨረቃ ላይ ተስሎ ይታያል የሚል ወሬ ተሰራጨ። በርካቶች ሰዓት ጠብቀው ወደ ሰማይ አንጋጠጡ።

“በጣም ያስደነግጣል፤ ምን ሆኖ ነው ሰዉ ይህን አምኖ የተቀበለው?” ይላሉ አሁን ስደት ላይ የሚገኙት የቀድሞዋ የኢራን ንግሥት ፋራህ ፓህላቪ።

ንግሥቲቱ ከባሏ ሻህ እና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር “ሽርሽር” ለማለት ኢራንን በ1979 መባቻ ለቀው እንደወጡ አልተመለሱም ።

“ባለቤቴ ለአገሩ ሲል ያን ሁሉ ነገር ካደረገ በኋላ ምላሹን ሲመለከት ልቡ ተሰብሮ ነበር” ይላሉ።

በእንግሊዝኛው ‘ዘ ሻህ’ እየተባሉ የሚጠሩት ሞሐመድ ሬዛ ፓህላቪ ግብፅ ውስጥ ስደት ላይ እያሉ ነው በ1980 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

ኾሚኒን ከደገፉ ግራ ዘመም እና ፀረ-ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል ኮሚዩኒስቱ ቱዴህ ፓርቲ ይገኝበታል።

ሻህራን ታባሪ አሁን የምትኖረው ለንደነው ነው። የፓርቲው አባል ነበረች። አጎቷ ደግሞ የፓርቲው መሪ። አሁን የሻህን አገዛዝ ለመጣል መነሳቷን ስታስበው ጥያቄ ይጫርባታል።

“ዲሞክራሲ ምን እንደሆነ አልገባንም ነበር” ትላለች። እሷ እንደምትለው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እየሆነ ባለው ነገር ባይስማሙም በጊዜው ዝምታን ነበር የመረጡት።

“ሁሉም ሰው የፈለገው ሻህ ምንም ዓይነት ዋጋ ተከፍሎ ከሥልጣን እንዲወርዱ ነበር።”

ሻህ እና ሚስቱ
የምስሉ መግለጫ,ሻህ እና ሚስቱ ከአብዮቱ በኋላ ወደ ኢራን ተመልሰው አያውቁም

‘የአስተሳሰብ መደብዘዝ’

በ2016 የሞተችው ታዋቂዋ ፀሐፊ እና የግራ ዘመሙ አስተሳሰብ የአብዮት መሪ ተብላ የምትጠራው ሆማ ናቴግ ናት።

ናቴግ በአብዮቱ ወቅት በቴህራን ዪኒቨርሲቲ አስተማሪ ነበረች። በርካታ መጽሐፍትን ጽፋለች፣ ተርጉማለች አብዮቱን በብዕሯ ደግፋለች።

አብዮታዊው አመራር ወደ ሥልጣን በወጣ በጥቂት ወራት ውስጥ ከሃይማኖታዊ መሪዎች ጋር ባለመስማማቷ ወደ ፈረንሳይ አቀናች።

በፈረንሳይ ሳለች ከቢቢሲ ጋር በርካታ ቃለ-መጠይቅ አድርጋለች፤ “በ1990ዎቹ በጻፍኳቸው ጽሑፎች አሁን አልስማማም” ስትል ቁጭቷን ተናግራለች።

ሳዴግ ግን ሰዎች አስተሳሰባቸው ደብዝዞ ነበር፤ አሊያም ተታለዋል ብሎ አያስብም።

“አይደለም፤ ምሥሎቹን ተመልከታቸው። ሁላችንም ምንም ዕውቀቱ አልነበረንም ልትለኝ አትችልም። አብዮተኞቹ እነ ማን ነበሩ? ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች አልነበሩም? በፕሮፖጋንዳ ተታለዋል ማለት ንቀት ነው።”

ከአብዮቱ በኋላ አብዛኛዎቹ ግራ ዘመም ፓርቲዎች ሲታገዱ፤ ኾሚኒ ሥልጣን ላይ እንዲወጡ እና እስላማዊ ሪፐብሊክ እንዲመሠረት ያገዙ አባላት እና አብዮታውያን ተገደሉ።

እሱ እንደሚለው አብዮቱ የሚተቸው “ሕዝቡ በአሁኑ አገዛዝ ላይ ቅሬታ ስላለው ነው።”

የኢራን መሪዎች አብዮቱ ኢራንን ከውጭ ኃይሎች በተለይ ደግሞ ከአሜሪካ እና ከምዕራባውያን ጫና ገላግሏል ይላሉ።

የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እና ብሔራዊ የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪውን በመጥቀስም በመከላከያ አቅም ራስን መቻል አንዱ ማሳያ ነው ይላሉ።

በተለይ ደግሞ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ትምህርት እና ጤና በማዳረሳችን ምሥጋና ይገባናል ባይ ናቸው።

ኢራናዊያን የአብዮቱን 45ኛ ዓመት ሲያከብሩ
የምስሉ መግለጫ,ኢራናዊያን የአብዮቱን 45ኛ ዓመት እያከበሩ ነው

“በቀል ተሸክሜ መጓዝ አልሻም”

የፓህላቪ መንግሥት ከወደቀ አራት አስርታት ቢያልፉም አብዮታዊው አገዛዝ አሁንም ተቃውሞ እየገጠመው ነው። ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡ ሰዎች የሻህን አገዛዝ ስም ሲያነሱ ተደምጠዋል።

“ሬዛ ሻህ ነብስህ ትባረክ” እና “ኢራን ያለ ንጉሥ ኢራን አይደለችም” የሚሉ መፈክሮች ተደምጠዋል።

አንዳንድ የቀድሞ አብዮተኞች ደግሞ ይቅርታ እንዲደረግላቸው እየጠየቁ ነው።

“ለዓመታት ፕሮፖጋንዳ ቢነዛም ሰዎች ንጉሡ ያደረጉትን ነገር ማየት መቻላቸው አንድ ነገር ነው” ይላሉ የቀድሞዋ ንግሥት ፋራህ ፓህላቪ።

“በርካቶች በአብዮቱ እንደተሳተፉ፣ ነገር ግን አሁን እንደሚቆጫቸው የሚያትትል ኢሜል ይልኩልኛል። ይቅርታ እንዳደርግላቸው ይጠይቁኛል።”

“ይቅርታ ታደርጊላቸዋለሽ?”

“እንዴታ!” ትላለች ፋራህ። “እኔ በቀል ተሸክሜ መጓዝ አልሻም።”

_____

* የተጠቀሱት ሁሉ ዓመታት በአውሮፓውያን አቆጣጠር ናቸው