
ከ 2 ሰአት በፊት
አሜሪካ የታጋቾችን መለቀቅ ከጋዛ ተኩስ አቁም ጋር በማያያዝ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ሩሲያ እና ቻይና ውድቅ አደረጉት።
ሩሲያ እና ቻይና ይህንን የአሜሪካ የውሳኔ ሃሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውንም በመጠቀም ነው ተቀባይነት እንደሌለው ያሳወቁት።
ቀደም ሲል ሌሎች አገራት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የተለያዩ የውሳኔ ሃሳቦች ለፀጥታው ምክር ቤት ቢቀርቡም ሊሳኩ አልቻሉም።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የጋዛ ተኩስ አቁም ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ጭምር በመጠቀም ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት አሜሪካ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሃሳብ ማንሳቷ በእስራኤል ላይ እየጠነከረ የሄደውን አቋሟ አሳይቷል ተብሏል።
ነገር ግን አሜሪካ በዚህ ወቅት ያቀረበችውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ሩሲያ እና ቻይና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን በመጠቀም ውድቅ አድርገውታል።
ሩሲያ በበኩሏ የአሜሪካን የውሳኔ ሃሳብን “ግብዝነት የተሞላበት” ስትል ወርፋዋለች።
የእስራኤል ዋነኛ አጋር የሆነችው አሜሪካ ይህንን የውሳኔ ሃሳብ ያቀረበችው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው አለመግባባት አየሰፋ ባለበት ወቅት ነው።
እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን መጠነ ሰፊ ጥቃት እንድትቀንስም አሜሪካ እያሳሰበች ትገኛለች።
- ጥቂት “በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ተባባሪ አልሆንም” ብሎ ራሱን ስላቃጠለው የአሜሪካው አየር ኃይል አባል9 መጋቢት 2024
- በጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ እንደሆነ ዶ/ር ቴድሮስ ተናገሩ5 መጋቢት 2024
- ሚስቱን እና ሦስት ልጆቹን ጨምሮ 103 ዘመዶቹን ያጣው ፍልስጤማዊ አባት27 የካቲት 2024
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ሰርጥ ውስጥ በምትፈጽመው የማያባራ ጥቃት 31 ሺህ 988 ሰዎችን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በተጨማሪም ከሰሜናዊ ጋዛ ጥቃት የሸሹ ሚሊዮኖች በተጠለሉባት የራፋህ ከተማ ሰላማዊ ሰዎችን የመጠበቅ ዕቅድን ባላካተተ መልኩ እስራኤል ያቀደችውን ጥቃት አሜሪካ እንደማትደግፍም ተናግራለች። በተጨማሪም እስራኤል ወደ ጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ እንድታስገባም አሜሪካ አሳስባለች።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው እስራኤል በራፋህ ላይ ያቀደችውን የምድር ላይ ጥቃት ከዋነኛ አጋሯ ውጪም ቢሆን እንደምታካሂድ ገልጸዋል።
ከአምስቱ ቋሚ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ ከዚህ ቀደም በሐማስ እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም እና የታጋቾች መለቀቅ ውይይቶች እየተካሄዱ ባለበት ወቅት የተኩስ አቁም ውሳኔ ምክር ቤቱ ሊያሳልፍ አይገባም የሚል አቋም ይዛ ነበር። በወቅቱ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷ ተጠቅማ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
ነገር ግን አርብ ዕለት በይፋ አቋሟን መቀየሯን ያስታወቀችው አሜሪካ በጥንቃቄ የተዘጋጀ የረቂቅ የውሳኔ ሃሳብም አቅርባለች።
የፀጥታው ምክር ቤት “አፋጣኝ እና ቀጣይነት ያለው የተኩስ አቁምን አስፈላጊነት ይወስናል” እንዲሁም ከዚህም ጋር ተያይዞ “የቀሩት ታጋቾች በሙሉ እንዲለቀቁ እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ እየተካሄደ ያለውን ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማያሻማ ሁኔታ ይደግፋል” በማለትም የአሜሪካ ውሳኔ ሃሳብ አትቷል።
በዚህም አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የምትደግፈው በሐማስ የታገቱ 253 ሰዎች ከመለቃቃቸው ጋር በማያያዝ መሆኑንም ረቂቁ ያሳያል።
ሩሲያ እና ቻይና ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡን ውድቅ ቢያደርጉትም ከ15 የምክር ቤቱ አባላት ውስጥ 11 አገራት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። አልጄሪያ ስትቃወም ጋያና በድምጸ ተዓቅቦ አልፋዋለች።
ሌላ የተኩስ አቁም ስምምነትን የሚጠይቅ አዲስ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ ድምጽ ለመስጠት ለሰኞ መራዘሙንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እና ሮይተርስ የዲፕሎማቲክ ምንጮቻቸውን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።