
22 መጋቢት 2024
ከአንድ ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያጋጠመውን የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት እክልን ተከትሎ ባንኩ እስካሁን ትክክለኛ መጠኑን ያልገለጸው ከፍተኛ ገንዘብ በደንበኞቹ ወጪ ተደርጎበታል።
በባንኩ ላይ የተከሰተውን የሲስተም ብልሽት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞች የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ማውጣታቸው እና ማዘዋወራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከዚህ ጋር በተያያዘ ስማቸው ሲነሳ ቆይቷል።
በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ እና አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. በባንኩ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ተከትሎ የራሳቸው ያልሆነ ብር በማውጣት ጥቅም ላይ ያዋሉ ተማሪዎች “ጭንቀት” ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ።
ቢቢሲ በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተማሪዎችን በማናገር ባገኘው መረጃ መሠረት በርካታ ተማሪዎች ከአስር ሺዎች እስከ መቶ ሺዎች የሚቆጠር የራሳቸው ያልሆነ ብር ከባንኩ ለመውሰድ ችለው ነበር።
ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ባንኩ ከዩኒቨርስቲዎች እና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ገንዘቡን ለማስመለስ እያደረገ ባለው ጥረት፣ ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች በእጃቸው ላይ የቀረውን ብር መመለሳቸው ቢነገርም ለተለያዩ ጥቅም ያዋሉት ግን ግራ በመጋባት በቀጣይ የሚመጣውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ በተፈጠረው ችግር የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ የወሰዱ ተማሪዎች ሂደቱን “ሥራ” በሚል ቃል ነበር የገለጹት።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪም “እኔ ወደ 150 ሺህ ብር ሠርቻለሁ። 300 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ የሠሩ ተማሪዎች አሉ። . . . ቀድሞ የሰማ [የሲስተም ብልሽቱን] ብዙ ሠርቷል” ብሏል።
ተማሪው አክሎም በዕለቱ “150 ሺህ ብር ‘ሠርቼ’ ነበር። ሁሉንም ብር ተመላሽ አድርጊያለሁ። ወደ ሌላ ባንክ ያዘዋወሩ ጓደኞቼ ግን ጭንቀት ላይ ናቸው” ሲል የተፈጠረውን ሁኔታ ገልጿል።
ንግድ ባንክ በገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ላይ ብልሽት ከማጋጠሙ በፊት በሂሳቡ ውስጥ የነበረው ከ5 ሺህ ብር በታች እንደነበረ የሚገልጸው ይህ ተማሪ፣ የተፈጠረውን ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ 150 ሺህ ብር መውሰዱን አምኗል።
ባንኩ ችግሩ መከሰቱን ተከትሎ ያላግባብ ብር የወሰዱ ደንበኞቹ ተመላሽ እንዲያደርጉ ባሳሰበው መሠረት እና ከዩኒቨርስቲው በኩል በወጣው ማስጠንቀቂያ ምክንያት ተማሪው ገንዘቡን መመለሱን ተናግሯል።
በድንገት እጃቸው ላይ የገባውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ የተለያዩ እቃዎች የገዙበት ወይም ከንግድ ባንክ አካውንታቸው ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ ያዘዋወሩ ተማሪዎች ደግሞ ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ይገኛሉ።
ተማሪው እንደሚለው የሲሰተም ብልሽት ባጋጠመበት ወቅት ካላቸው ገንዘብ በላይ ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ ያዘዋወሩ ተማሪዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ በመደረጉ ገንዘቡን ለመመለስ ባለመቻላቸው በግራ መጋባት ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ ብሏል።
- ንግድ ባንክ ገንዘቡን እስከ ቅዳሜ የማይመልሱ ሰዎችን ፎቶ እና ማንነት በሚዲያ ይፋ አደርጋለሁ አለ21 መጋቢት 2024
- በአንድ ምሽት ተማሪዎችን “ባለሃብት” ያደረገው የንግድ ባንክ የሲስተም ብልሽት18 መጋቢት 2024
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሰዓታት ባጋጠመው “የሲስተም ችግር” ምን ያህል ብር ወጪ ሆነ?20 መጋቢት 2024
ተማሪዎቹ ገንዘቡን ምን አደረጉበት?
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውሩ ላይ ችግር ባጋጠመው ጊዜ በርካቶች ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ላይ እንዲሁም በሞባይል ባንኪንግ አማካይነት በሂሳባቸው ካላቸው የገንዘብ መጠን በላይ ማንቀሳቀስ ችለዋል።
ባንኩ እንደሚለው በዚያ ወቅት ከአስር ሺህ በላይ ግለሰቦች ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ዝውውር አድርገዋል። በዚህ ሂደትም አንዳንዶች እንደሚሉት ከሚሊዮኖች እስከ ቢሊዮን መጠን ያለው ብር ተንቀሳቅሷል።
በዚህ ሁኔታ ያላሰቡትን ገንዘብ ያዘዋወሩ ተማሪዎች ብሩን የተለያዩ ውድ ቁሶችን መግዛታቸውን እና ለሌሎች ሰዎች ማስተላለፋቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲው ተማሪ እንደሚለው ብዙ ጓደኞቹ በወሰዱት ገንዘብ የተለያዩ ውድ ነገሮችን በመግዛታቸው ገንዘቡን መልሰው ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ስላሉ ጭንቀት ላይ ይገኛሉ ይላል።
በተለይ ላፕቶፕ እና ዘመናዊ ስልኮችን የገዙ ተማሪዎች ጥቂት አለመሆናቸውን የሚጠቅሰው ተማሪው “100ሺህ ብር የሠራ አንድ ልጅ በሁለተኛው ቀን ላፕቶፕ እና ስማርት ስልክ ገዝቷል” በመግዛቱ እጁ ላይ የሚመልሰው ገንዘብ እንደሌለ ገልጿል።
“ሌሎች ደግሞ ያልተገደበ የአንድ ዓመት የኢንተርኔት ጥቅል ገዝተዋል። የነበረባቸውን ብድር የከፈሉ አሉ። . . . ብዙዎቹ ገንዘቡን ተጠቅመውበታል።”

ቢቢሲ ያነጋገረው ሌላ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሲስተም ችግር ባጋጠመበት ሌሊት ጓደኞቹ በተደጋጋሚ እየደወሉ ገንዘብ ወጪ እንዲያደርግ ቢነግሩትም “ምንም አልሠራሁም” ይላል።
ነገር ግን የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ለማውጣት የቻሉት ጓደኞቹ ወደ እርሱ አካውንት 50 ሺህ ብር ካዘዋወሩ በኋላ የባንክ ሂሳቡ መታገዱን ይገልጻል።
“ገንዘቡን ለላከልኝ ልጅ ልመልስ ብል እንኳን አካውንቴ ታግዷል። ፈልጌ አይደለም ገንዘቡ የተላከልኝ። ትራንስፈር ስለተደረገ አካውንቴ ተዘግቶብኛል” ይላል።
ቢቢሲ ያነጋገረው ሌላኛው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ገንዘብ መውሰዱን አምኖ የወሰደውን ለመመለስ ፍቃደኛ ቢሆንም አካውንቱ በመታገዱ ተመላሽ ማድረግ አለመቻሉን ይገልጻል።
ይህ ተማሪ በሞባይል ባንኪንግ አማራጭ ወደ 70 ሺህ ብር ወደ ሌላ ባንክ አካውንት ገንዘብ ማዘዋወሩን ነገር ግን “ከሰኞ ጀምሬ ለመመለስ ብጥርም አካውንቱ እንዳይንቀሳቀስ በመደረጉ አልቻልኩም” ይላል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ችግሩ ባጋጠመበት ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የገንዘብ ዝውውሮች መደረጋቸውን አመልክቶ፤ በወቅቱ ግብይት ሲፈጸምባቸው የነበሩ የባንክ ሂሳቦች ማጣራት እስኪደረግባቸው ድረስ እንዲታገዱ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ባንኩ ካጋጠመው ችግር ጋር በተያያዘ የወሰዱ ሰዎች እስከ ነገ ቅዳሜ መጋቢት 14/2016 ዓ.ም. ድረስ እንዲመልሱ በድጋሚ ጠይቋል። በቀነ ገደቡ ያልመለሱትን ግለሰቦች ስምና ፎቶ በመገናኛ ብዙኃን ይፋ በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግም አስጠንቅቋል።
በዚህም ምክንያት ገንዘቡን ወስደው የተጠቀሙበት እንዲሁም ወደ ታገዱ አካውንቶች ያዘዋወሩ ተማሪዎች “ድንጋጤ እና ጭንቀት” ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ከባንኩ የወሰደውን ገንዘብ ወደ ሌላ አካውንት አዘዋውሮ ገንዘቡን ለመመለስ ተቸገርኩ ያለ ተማሪ በቅርቡ ፈተና እንዳለበት እና “ከክስተቱ ጋር በተያያዘ የስሜት መረበሽ ውስጥ እንደሚገኝ” ገልጿል።
“ዋነኛ ተዋንያን”
በአገሪቱ ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ላይ ችግሩ የተከሰተው አንድ ሂሳብ ማስታረቅ ቅልጥፍና እንዲያመጣ ታስቦ የተዘጋጀ የሲስተም ማሻሻያ ሲተገበር የተፈጠረ ስህተት ደንበኞች በሂሳባቸው የሌላቸውን ገንዘብ እንዲያንቀሳቅሱ ምክንያት ነው ብሏል።
አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ የተከሰተውን እና ለሰዓታት በቆየው ችግር አማካይነት ባንኩ እስካሁን ያልገለጸው የገንዘብ መጠን ወጪ ተደርጓል። የተፈጠረውን ችግር ለመቆጣጠርም የባንኩ የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ተደርጎ ነበር።
በባንኩ ሥርዓት ላይ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ “ጤናማ ባልሆነ” የገንዘብ ዝውውር ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደዋነኛ ተዋንያን መሆናቸውን ባንኩ ጠቅሷል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖም “የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በወንጀሉ ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸው አሳዝኖናል። በየአካባቢው ያሉ የዲስትሪክት ኃፊዎች በየአካባቢው ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ተማሪዎች የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ እየተደረገ ነው” ብለዋል።
ከቅዳሜ ጀምሮም የተወሰኑ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸው ያንቀሳቀሱትን ገንዘብ ተመላሽ እንዲያደርጉ የሚያስጠነቅቁ ማስታወቂያዎችን በተቋሞቹ ውስጥ የለጠፉ ሲሆን፣ በተጨማሪም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይም አሰራጭተዋል።
በአንዳንድ የትምህርት ተቋማት ውስጥም የፀጥታ ኃይሎች መታየታቸውን እና በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ ደግሞ የምርምራ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተማሪዎች በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ክስተቱ ካጋጠመ በኋላ አሁንም ድረስ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ይህ የገንዘብ ዝውውር ጉዳይ እና የተከተለው ማስጠንቀቂያ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል።
ባንኩ የበይነ መረብ ጥቃት እንዳልተፈጸመበት በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ የራሳቸው ያልሆነውን ገንዘብ ለማዘዋወር የደፈሩት ባንኩ ከባድ ችግር እንዳጋጠመው እና “ሊደረስብን አይችልም በሚል የተሳሳተ ግምት ምክንያት” መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ የዜና ምንጮች እና ኤፒ ዜና ወኪል እንደዘገቡት በተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቶ ሚሊዮኖች ከሚቆጠር ብር እስከ ቢሊዮኖች ወጪ ሳይደረግበት እንዳልቀረ አመልክተዋል።
ባንኩ ግን ይህንን በማስተባበል የገንዘብ መጠኑን ለማወቅ እየተካሄደ ያለው ምርመራ እና ኦዲት መጠናቀቅ እንዳለበት በመግለጽ፣ የደረሰበት ጉዳት ባንኩ ካለው ሀብት እና አቅም አንጻር የጎላ ተጽእኖ የለውም ሲል አቃሎታል።
የተማሪዎቹ ጉዳይ ከሕግ አንጻር
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ሃብታሙ ለገሰ የማይገባቸውን ገንዘብ ወጪ ያደረጉት ግለሰቦች በወንጀል እንደሚጠየቁ ይናገራሉ።
የሕግ መምህሩ፤ “የሲስተም ችግሩን መሠረት በማድረግ ለራስ ወይም ለሌሎች የማይገባን ጥቅም ለማግኘት የተፈጸመው ተግባር የኮምፒዩር ወንጀልን ለመደንገግ በወጣ አዋጅ ሊታይ የሚችል የወንጀል ድርጊት ነው” ይላሉ።
ንግድ ባንክ ካጋጠመው ክስተት ጋር በተያያዘ የተፈጸመው ተግባር በዚህ የኮምፒዩር ወንጀልን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ሊታይ አይችልም ቢባል እንኳ ጉዳዩ በመደበኛው የስርቆት ወንጀል ሊዳኝ እንደሚችል ሃብታሙ ይናገራሉ።
የሕግ መምህሩ እንደሚሉት የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ ያወጡ ተማሪዎች በ3 ዓመት የቀላል እስራት እና ከ30ሺህ ብር ባልበለጠ የገንዘብ ቅጣት ሊቀጡ ይችላሉ ይላሉ።
“ወንጀሉን የተፈጸመበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ብዙ ርቀት ሄደው ብዙ ገንዘብ የወሰዱ ግለሰቦች ቅጣት ከዚህም በላይ ከባድ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል”
ከእውቅናቸው ውጪ ገንዘብ ገቢ የተደረገላቸውም ግለሰቦች ቢሆኑ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ ወይም የወንጀል ድርጊት ውጤት የሆነን ገንዘብ ይዞ በማቆየት በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑ ጨምረው አስረድተዋል።
የንግድ ባንክ የሲስተም ችግርን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ገንዘብ የወሰዱ ተማሪዎች የማይገባቸውን ገንዘብ በአስቸኳይ ተመላሽ እንዲያደርጉ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያዎችን ማውጣታቸው ይታወሳል።
የሕግ መምህሩ ግን ዩኒቨርሲቲዎች ይህን የወንጀል ጉዳይ የመመልከት ሥልጣን የላቸውም ይላሉ።
“ዩኒቨርሲቲዎች መመልከት የሚችሉት የባሕሪ ወይም የዲስፕሊን ግድፈቶችን እንጂ የወንጀል ጉዳዮችን ማየት አይቻላቸውም። ሊያደርጉ የሚችሉት ከሚመለከተው አካል ጋር ትብብር ማድረግ ነው” ይላሉ።
ምንም እንኳ ጥሬ ገንዘብን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢዎች ውስጥ ከሚገኙ ገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም) ወጪ ቢያደርጉም ተማሪዎች ያለ አግባብ የተጠቀሙት የንግድ ባንክ ሥርዓትን እንጂ የኤቲኤም ማሽኑን አይደለም ይላሉ።