
ከ 3 ሰአት በፊት
ታጣቂዎች በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው ታዋቂው የክሮከስ አዳራሽ ላይ ተኩስ ከፍተው ቢያንስ 60 ሰዎች ሲገድሉ፣ 100 ሰዎች መቁሰላቸውን የሩሲያ የደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
ቢያንስ አራት ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች የበርካቶችን ሕይወት በቀጠፈው ጥቃት ውስጥ መሳተፋቸውንም ቢቢሲ ያረጋገጠው ቪዲዮ ያሳያል።
ክራስኖጎርክስ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ በሚገኘው የክሮከስ አዳራሽ የሮክ የሙዚቃ ዝግጅት ሊቀርብ በነበረበትም ወቅት በአዳራሹ ታጣቂዎች ገብተው ተኩስ እንደከፈቱ እና መድረክ ላይም መውጣታቸው ተነግሯል።
ፒክኒክ የተሰኘው ታዋቂው የሮክ ባንድ ሙዚቃን ለመታደም 6 ሺህ የሚሆኑ ሩሲያውያን በክሮከስ ሲቲ ሆል ተገኝተው ነበር። ጥቃቱ የተከፈተውም ባንዱ ወደ መድረክ ከመምጣቱ ከደቂቃዎች በፊት እንደሆነ አንድ የዐይን እማኝ ተናግሯል።
የፒክኒክ ባንድ አባላት ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም።
አብዛኛው የአዳራሹ ህንጻ በእሳት የተቃጠለ ሲሆን፣ የተወሰነው ጣራው ተደርምሶ ወድቋል።
ከተገደሉት መካከል ህጻናት ይገኙበታል የተባለ ሲሆን፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱ “የሽብር ጥቃት ነው” ሲል አውግዟል።
ለጥቃቱ ታጣቂው የእስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ቡድን ኃላፊነቱን መውሰዱን በበይነ መረብ የወጣ አንድ ያልተረጋገጠ መግለጫ አመልክቷል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው አይኤስ ሩሲያን ለማጥቃት እንደሚፈልግ የሚያሳይ መረጃ ማግኘታቸውን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናግረዋል።
- በሊቢያ የስደተኞች የጅምላ መቃብር መገኘቱን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀከ 4 ሰአት በፊት
- ንጉሣዊውን አገዛዝ የገረሰሰው የኢራን እስላማዊ አብዮት ግቡን አሳካ ወይስ. . .?ከ 4 ሰአት በፊት
- ‘ጭንቅ ውስጥ’ ነን የሚሉት ተማሪዎች ከንግድ ባንክ የወሰዱትን ገንዘብ ምን ላይ አዋሉት?22 መጋቢት 2024
ይህንንም አስመልክቶ ዋይት ሐውስ በሞስኮ “ሕዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች” ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሩሲያን አስጠንቅቃ እንደነበረ ተገልጿል።
የሩሲያ ብሔራዊ ዘብ (ናሽናል ጋርድ) ጥቃት ፈጸሚዎቹን አድኖ ለመያዝ በስፍራው የተሰማሩ ልዩ ኃይሎች እንዳሉት ገልጿል። የሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናትም ጥቃቱ ወደተፈጸመበት ክራስኖጎርስክ አካባቢ አምርተዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት በሩሲያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ በርካታ ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው ሕዝባዊ ስፍራዎች እንዳይሄዱ ማስጠንቀቂያ አስተላልፎ ነበር።
በዚህም ማስጠንቀቂያው ላይ “ጽንፈኞች በሞስኮ ሕዝብ በሚሰባሰቡባቸው ስፍራዎችን የጥቃት ዒላማ ለማድረግ ዕቅድ አላቸው” የሚል ሪፖርትን እየተከታተልኩ ነው ብሎ ነበር።
ኤምባሲው አርብ ምሽት ባወጣውም መግለጫ ጥቃቱ ወደደረሰበት ስፍራ ዜጎቹ ዝር እንዳይሉም ምክሩን አስተላልፏል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጥቃቱን አስመልክቶ ለሕዝባቸው መግለጫ ባይሰጡም፣ ምክትላቸው በጥቃቱ የቆሰሉ በፍጥነት እንዲያገግሙ ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።