
ከ 4 ሰአት በፊት
ሊቢያ ውስጥ ቢያንስ የ65 ስደተኞችን አስከሬኖች ያያዘ የጅምላ መቃብር መገኘቱን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።
ስደተኞቹ የሞቱበትን ሁኔታ እና የየት አገር ዜጎች ስለመሆናቸው አስካሁን የታወቀ ነገር እንደሌለ ድርጅቱ ገልጾ፣ ነገር ግን በሊቢያ በረሃ በኩል ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር በድብቅ ሲወሰዱ ሳይሞቱ እንደማይቀሩ ይታመናል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አካል የሆነው ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በተገኘው የጅምላ መቃብር “በጥልቅ መደንገጡን” ገልጿል።
የስደተኞቹ የጅምላ መቃብር የተገኘው በደቡብ-ምዕራብ የሊቢያ ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ አገሪቱም የጅምላ መቃብሩን በተመለከተ ምርመራ እያካሄደች መሆኗን አይኦኤም ገልጿል።
የአይኦኤም ቃል አቀባይ እንዳሉት “በእያንዳንዱ ስደተኛ ላይ የሚደረስ ደብዛ መጥፋት ወይም ሞት በቤተሰቦች ላይ የሚደርስን ሐዘን ከመወከሉ ባሻገር ስላጋጠማቸው ሰቆቃ ለማወቅ ያለው ጥረትም ሌላው አሳዛኝ ሁኔታ ነው” ብለዋል።
አክለውም አስፈላጊው እርምጃ ባለመወሰዱ ይህ ክስተት እየጨመረ ያለው የሰዎች ሞት እና ስደተኞች ያሉበት የሚረብሽ ሁኔታ ማስረጃ ነው ሲሉ በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።
- ሩዋንዳ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞችን ከሊቢያ ተቀበለች22 መጋቢት 2024
- ባሕር ሲያቋርጥ የሞተው ኢትዮጵያዊ ሚስት እና ልጆቹ የፈረንሳይ መንግሥትን ከሰሱ16 መጋቢት 2024
- በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ሲጓዙ የነበሩ ቢያንስ 60 ስደተኞች ሕይወት አለፈ15 መጋቢት 2024
የስደተኞቹ ድርጅት እንዳለው አሁን የተገኘው የጅምላ መቃብር በሕገወጥ መንገድ በድብቅ የሚካሄድን ፍልሰት እና ሕጋዊ የስደት መስመሮችን በተመለከተ የተቀናጀ እርምጃ እንደሚያስፈልግ አመልካች ነው ብሏል።
ሊቢያ በአደገኛው የሜዲትራኒያን ባሕር በኩል በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚፈልጉ ስደተኞች ከሚጠቀሙባቸው መስመሮች መካከል ዋነኛዋ ናት።
መቀመጫውን ስዊትዘርላንድ ጄኔቭ ያደረገው ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በጀምላ መቃብር የተገኙትን ስደተኞች አስከሬኖች በተገቢው ሁኔታ እንዲለዩ ለማድረግ የሊቢያ ባለሥልጣናት እና የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማት አስፈላጊውን እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የአሁኑ ከስልሳ በላይ ስደተኞች የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር የተገኘው፣ ከሊቢያ ባሕር ዳርቻ በትንሽዬ ጀልባ ተነስተው ሜዲትራኒያን ባሕርን ሲያቋርጡ በደረሰባቸው አደጋ ቢያንስ 60 ስደተኞች መሞታቸው ከታወቀ በኋላ ነው።
ድርጅቱ እንዳለው ያለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የፍልሰተኞች ቁጥር መመዝገብ ከጀመረበት ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የበርካታ ስደተኞች ሕይወት የጠፋበት ነው።
በዚህም በመላው ዓለም በሚገኙ የስደተኞች መተላለፊያ መስመሮች ላይ ቢያንስ የ8,565 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን አይኦኤም ገልጿል።
በሊቢያ ውስጥ ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታን የሚያቀርበው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም አይኦኤም እንዳለው ይህ አሃዝ ቀደም ካለው ዓመት በ20 በመቶ ከፍ ያለ ነው።