ኪዬቭ

ከ 8 ሰአት በፊት

የዩክሬን መዲና ኪዬቭ በድንገተኛ የሩሲያ የአየር ጥቃቶች ድብደባ ደረሰባት።

ድንገተኛውን የሩሲያ ድብደባ ተከትሎ በመላ ዩክሬን የአገሪቱ ጦር በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።

የሩሲያ የአየር ድብደባ ከፖላንድ የምትዋሰነው ሊቪቭ ግዛትን መምታቱን ተከትሎ ፖላንድ የአየር ኃይሏ በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን አዛለች።

በመዲናዋ ኪዬቭ ላይ የአየር ድብደባው የጀመረው በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር እሑድ ንጋት 11 ሰዓት አካባቢ ነው።

የዩክሬን ጦር አየር ኃይሉ የሩሲያን ጥቃት በመከላከል ተጠምዷል ብሏል።

የጦሩ ዋና አስተዳዳሪ ሴርሂይ ፖፕኮ በርካታ የሩሲያ ሚሳኤሎች በኪዬቭ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ዒላማዎቻቸውን ከመምታታቸው በፊት ተመትተው ወድቀዋል ብለዋል።

ይህን የሩሲያ ጥቃት ተከትሎ እስካሁን ድረስ በዩክሬን ላይ የደረሰ ጉልህ የሆነ ጉዳት ወይም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰ ሞት ስለመኖሩ ሪፖርት አልተደረገም።

የሊቪቭ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው የሊቪቭ ከተማ ከንቲባ አንድሪይ ሳዶቨይ መላ ግዛቱን ዒላማ ያደረጉ 20 ሚሳኤሎች እና በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መተኮሳቸውን በቴሌግራም ገጻቸው አስታውቀዋል።

ከንቲባው ጥቃቶቹ እስካሁን ድረስ ከተማዋን ባይመቱም በግዛቱ የሚገኙ “ቁልፍ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን” ዒላማ አድርገዋል ብለዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ሩሲያ አንድ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን በሚሳኤል ከመታች በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው ይገኛል።

ይህ የሩሲያ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ሞስኮ የአየር ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል ማስጠንቀቂያ ወጥቶ መላው ዩክሬን በተጠንቀቅ ላይ እንድትሆን ከጦሩ ትዕዛዝ ተላልፎ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከፖላንድ በምትዋሰነው የዩክሬን ግዛት የአየር ጥቃት መድረሱን ተከትሎ የፖላንድ አየር ኃይል የአገሪቱን የአየር ክልል ደኅንነት ለማረጋገጥ ዝግጁ ሆኗል ተብሏል።

“የፖላንድን የአየር ክልል ደኅንነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ እርምጃቸዎች ተወስደዋል። የፖላንድ አየር ኃይል እና አጋሮቻችን ሁኔታን በትኩረት እየተከታተሉት ይገኛሉ” ብሏል አየር ኃይሉ ያወጣው መግለጫ።

በኪዬቭ ላይ የተፈጸመውን የአየር ድብደባ ተከትሎ በርካቶች እራሳቸውን ለማዳን ከምድር በታች በተቆፈሩ ባቡር ጣቢያዎች ውስጥ ተደብቀው ታይተዋል።

ዛሬ ንጋት የተፈጸመውን የሩሲያ ጥቃት በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከሞስኮ በኩል የተባለ ነገር የለም።