የሻማ ማብራት ሥነ-ስርዓት

24 መጋቢት 2024, 09:07 EAT

ተሻሽሏል ከ 3 ሰአት በፊት

በሩሲያ ባሳለፍነው አርብ መጋቢት 13/2016 ዓ.ም. “አሸባሪዎች” በፈጸሙት ጥቃት 113 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታወጀ።

ሰንደ ዓላማዎች ዝቅ ብለው እየተውለበለቡ ሲሆን ቅዳሜ እና እሁድ ሊካሄዱ የነበሩ በርካታ ሥነ-ሰርዓቶች በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ እንዲሰረዙ ተደርገዋል።

ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ኃላፊነቱን በወሰደበት ጥቃት ከተገደሉት 113 ሰዎች በተጨማሪ 140 ሰዎች ቆስለዋል።

ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ እሁድ መጋቢት 15/2016 ዓ.ም. በመላው ሩሲያ ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲሆን አውጀዋል።

ይህን ተከትሎ በሞስኮ እና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ቢልቦርዶች የሚበራ ሻማ “እናዝናለን” ከሚል ጸሑፍ ጋር እያሳዩ ነው።

ከሩሲያ በተጨማሪ በበርካታ አገራት በሚገኙ የአገሪቱ ኤምባሲዎች የሻማ ማብራት ሥነ-ስርዓቶችን እያካሄዱ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የሙዚቃ ድግስ በሚደረግበት አዳራሽ ውስጥ ጥቃት ያደረሱት አራቱም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይፋ አድርገዋል።

አራቱ ተጠርጣሪዎቹ ወደ አዳራሹ በመግባት ያገኙት ሰው ላይ በመተኮስ ባደረሱት ጥቃት 133 ሰዎች ሲገደሉ 140 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ባለሥልጣናት እንደገለጡት በጠቅላላው 11 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ አራቱ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ዩክሬን ድንበር ሲያቀኑ ነው የተያዙት።

ቅዳሜ ዕለት አማቅ የተሰኘው የአይኤስ የቴሌግራም ቻናል ጥቃቱን ያደረሱት ናቸው ያላቸውን ሰዎች ፎቶ ለጥፏል። ሩሲያ አይኤስ ኃላፊነት ስለመውሰዱ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

ቡደኑ ጥቃቱ ሲፈጸም የሚያሳይ ለመመልከት ከባድ የሆኑ አሰቃቂ ቪድዮዎችን ለቋል።

ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ይህ ቪድዮ ታጣቂዎች በርካታ ሰዎች ላይ ጥይት ሲያርከፈክፉ ያሳያል።

ፑቲን በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ጅምላ ግድያውን አውግዘው “ጭካኔ የተሞላበት የሽብር ተግባር ነው” ብለውታል።

ፕሬዝደንቱ አክለው ታጣቂዎቹ ወደ ዩክንሬን ሊያመልጡ ሲሉ መያዛቸውን ገልጠዋል።

ዩክሬን በጥቃቱ እጇ አለችበት የተባለውን ክስ አስተባብላ “የማይመስል ነገር ነው” የሚል አስተያየት ሰጥታለች።

“ተጠርጣሪዎቹ ወደ ዩክሬን እያቀኑ ነበር ማለት እነዚህ ሰዎች ደደቦች እና ራሳቸውን ለማጥፋት የተዘጋጁ ናቸው ማለት ነው” ሲሉ የዩክሬን ጦር ሠራዊት ደኅንነት ቃል አቀባይ አንድሪ ዩሶቭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዩክሬኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቮሎድሚር ዜሌንስኪ፤ ፑቲን ለጥቃቱ ዩክሬንን “ተወቃሽ” ለማድረግ እየሞከሩ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን

“ይህ የማይረባ ፑቲን ለሩሲያ ዜጎች እንደመድረስ ቀኑን ሙሉ ዝም ብሎ የቆየው ዩክሬንን እንዴት ወደዚህ ላምጣት የሚለውን በማሰብ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት “ሰዎች በሚበዙበት ቦታ” ጥቃት ሊኖር ይችላል ብለን ለሩሲያ ቀድመን ማስጠንቀቂያ ሰጥተን ነበር ብሏል።

ነገር ግን ክሬምሊን ይህን ማስጠንቀቂያ በወቅቱ በሩሲያ ምርጫ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ “ፕሮፖጋንዳ ነው” በሚል አጣጥሎታል።

ቅዳሜ ዕለት ዋይት ኃውስ “አሰቃቂ” ያለውን ጥቃት አውግዞ ኢስላሚክ ስቴት “የሁሉም የጋራ ጠላት እና ካለበት ቦታ ሁሉ ሊጠፋ የሚገባ ነው” ብሏል።

አርብ ምሽት ከሞስኮው በቅርብ ዕርቀት በሚገኝ አዳራሽ 6200 ሰዎች አንድ የሙዚቃ ኮንሰርት ለመታደም በስፍራው እየተሰባሰቡ ነበር።

ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ምስሎች ታጣቂዎች ሰዎች ላይ እየተኮሱ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ያሳያሉ።

ታጣቂዎቹ ያገኙት ሰው ላይ እየተኮሱ ወደውስጥ ሲዘልቁ በርካቶች እየጮሁ ለማምለጥ ሲሞክሩ አንዳንዶች ደግሞ የተቀመጡበት ወንበር ሥር በመግባት ለመደበቅ ሲሞክሩ ታይተዋል።

አንዳንዶች ወደ ሕንፃው ጣራ በመሮጥ ለማምለጥ ሲሞክሩ ሌሎች ደግሞ ወደ ታችኛቸው የሕንፃው ክፍል ገብተው ለመደበቅ ሲሮጡ ነበር።

አዳራሹ በእሣት ከተያያዘ በኋላ

“እየተራመዱ ያገኙትን ሰው በጥይት ሲደፉ ነበር። ድምፅ ያስተጋባ ስለነበር ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ሊገባን አልቻለም” ትላለች ኮንሰርቱን ለመታደም ወደ ስፍራው አቅንታ የነበረችው አናስታዚያ ሮዲዮኖቫ።

ታጣቂዎቹ የኮንሰርቱን ታዳሚዎች በጥይት ከመግደላቸው ባለፈ ሕንፃውን በእሣት ያያዙት ሲሆን ታስ የተሰኘው የዜና ወኪል የሕንፃው ሶስት አራተኛው ክፍል በእሣት ተያይዞ ነበር ሲል ዘግቧል።

ከጥቃቱ በኋላ የልዩ ኃይል አባላት ወደ ሕንፃው ሲላኩ በርካታ አምቡላንሶች እና የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ ሰዎች ወደ አዳራሹ ተልከዋል። ሄሊኮፕተሮች ደግሞ ሕንፃውን እየዞሩ እሣት ለማጥፋት ሲሞክሩ ታይተዋል።

የሩሲያ ምርመራ ኮሚቴ እንዳለው ታጣቂዎቹ ተቀጣጣይ ፈሳሽ ተጠቅመው ነው የኮንሰርቱን አዳራሽ በእሣት ያያዙት። ይህን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በጥይት እና በመመረዝ ሊሞቱ ችለዋል።

ቅዳሜ ዕለት ከአዳራሹ አቅራቢ የሞቱትን ለማሰብ በርካታ ዜጎች የአበባ ጉንጉን ሲያስቀምጡ እና ሻማ ሲያበሩ ታይተዋል።

ፕሬዝደንት ፑቲን እሑድ ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲሆን አውጀው በመላው ሩሲያ ለቅዳሜ እና እሑድ የታሰቡ ፕሮግራሞች እንዲሰረዙ አዘዋል።

ሚስቱ ኮንሰርቱን ለመታደም እንደወጣች የጠፋችበት ሴምዮን ኽራፕስቶቭ አምስት ሆስፒታሎች ደውሎ መስመሩ በመያዙ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን ይናገራል።

“ድንጋጤ ውስጥ ነኝ። ምን አንደማደርግ አላውቅም። ተስፋ አጥቻለሁ” ይላል።

ጥቃቱ ባለፉት 20 ዓመታት በሩሲያ ታይቶ የማይታወቅ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ነው ተብሏል።