
ከ 9 ሰአት በፊት
ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ሰዎችን ማገት በናይጄሪያ በተለይም በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተለመደ ነው። ባለፉት አስር ዓመታትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታግተዋል። በሚሊዮኖች ዶላሮችም አጋቾች እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።
በዓመታት ውስጥ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያገኙ አጋቾች፣ ታጋቾቻቸውን ቢለቁም መገደልም አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ ነው።
አገሪቷ እየተበራከተ ያለውን መታገትም ላለማበራታት በሚል ለታጋቾች መክፈልን ሕገወጥ አድርጋለች። ለአጋቾች መክፈል ሕገወጥ ቢሆንም፣ በርካቶች አሁንም የሚወዷቸውን ሰዎች ላለማጣት ሲሉ ማስለቀቂያ ገንዘብ ይከፍላሉ።
በእነዚህ አጋቾችን በማስለቀቅ ሁኔታዎች ውስጥም አንድ ሰው በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
ቢቢሲ ለደኅንነቱ ሲል ስሙን ቀይሮ ሱለይማን በሚል የሚጠራው ይህ ግለሰብ ታጋቾችን ተደራድሮ ያስለቅቃል።
ሱለይማን መኖሪያው በቅርቡ 280 ህጻናት ከትምህርት ቤት ታግተው በተወሰዱባት የካዱና ግዛት ነው። ሱለይማን ወደ ማደራደሩ የገባው የገዛ ዘመዶቹ ታግተው ስለነበር ሲሆን፣ ከዚያ በኋላም ለሕይወቱ ሳይሳሳ ተደራድሮ ሰዎችን ያስለቅቃል።
“መደራደር አለብን። ታጋቾችን ለማስመለስ ኃይል መጠቀም አይቻልም። ካለበለዚያ የምንወዳቸው ቤተሰቦቻችን ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል” ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሱለይማን ለመጀመሪያ ጊዜ የተደራደረው በሰሜን ናይጄሪያ አካባቢዎች ‘ሽፍቶች’ ተብለው ከሚጠሩ የአጋቾች ቡድን ጋር ነበር። መደራደር የጀመረውም ከሦስት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ናይጄሪያም ከዓመት በኋላ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚከፈል ገንዘብን ሕገወጥ አድርጋለች።
ሱለይማን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ200 በላይ ታጋቾችን በድርድር ለማስለቀቅ እንደቻል ይናገራል።
ከአጋቾች ጋር መደራደር ቀላል አይደለም፤ ሱለይማን እንደሚለው ትዕግስት አና ድፍረትን ይጠይቃል። ይህም ብቻ አይደለም በተለያዩ አካላት እንደ ጠላትም መታየት አለ።
“መንግሥት እኔ ሽፍቶችን እየረዳሁ እንደሆነ ያምናል። ሽፍቶቹ ደግሞ ከመንግሥት ገንዘብ እንደማገኝ ስለሚያስቡ ለእገታ ኢላማ ነኝ” ይላል።
በመጀመሪያው ድርድሩ ወቅት ሁለት ዘመዶቹን ከታጋቾች ለማስለቀቅ የተጠየቁትን 12 ሺህ 500 ዶላር ማሰባሰብ ነበረበት።
“በወቅቱ ምን እያደረግኩ እንደነበር አላውቅም። ካገቷቸው ሽፍቶች ጋር እየተነጋገርኩ እንዲሁም እየለመንኳቸው ነበር” ይላል።
- “የልጄን ሕይወት በአንድ ሚሊዮን ብር ገዛሁ” ልጃቸውን ከእገታ ያስለቀቁ አባት3 ሀምሌ 2023
- በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ እገታዎች የፈጠሩት ስጋት5 ሀምሌ 2023
- በናይጄሪያ ተጨማሪ ተማሪዎች ቅዳሜ ዕለት በታጣቂዎች ተጠልፈው ተወሰዱ10 መጋቢት 2024

ዘመዶቹን ለማስለቀቅም ትዕግስት በተሞላበት መልኩ ሽፍቶቹን ማናገሩ ውጤታማ ሆነ።
ምንም እንኳን የተጠየቀውን ገንዘብ ለመሸፈን በትውልድ ቀየው የሚገኘውን የእርሻ መሬት መሸጥ ቢኖርበትም ዘመዶቹ ተለቀቁ።
ዘመዶቹ ከነዚህ ሽፍቶች ነጻ መውጣታቸውም ሲሰማ ሌሎች የመታገት ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦች መጉረፍ ጀመሩ።
እርዳን የሚሉ ቤተሰቦችም ይማጸኑት ጀመር።
“በመንደራችን ያሉ ሁሉም ሰዎች ቢያንስ አንድ የቤተሰብ አባላቸው ታግቷል” የሚለው ሱለይማን ያለ ክፍያም እንደሚረዳቸው ይናገራል።
ለአጋቾች የሚከፈል ገንዘብ ሕገ ወጥ ቢሆንም የእሱን እርዳታ ሽተው የሚመጡ ሰዎች አሁንም በርካታ ናቸው።
“መንግሥት ከነዚህ ሽፍቶች ጋር መደራደርን አይፈልግም እንዲሁም አይወድም። ከሽፍቶቹ ጋር የሚደራደሩ ሰዎችም ከተገኙ ወደ እስር ቤት ሊላኩ ይችላሉ” በማለት ሱለይማን ያለበትን አጣብቂኝ ያስረዳል።
ታጋቾችን ተደራድሮ የማስፈታት ስኬቱም ቀውሱን ከስር መሠረቱ በመረዳቱ እንደሆነም ነው ሱለይማን የሚገልጸው።
እገታዎች አገሪቷን እያናወጧት ያሉት በናይጄሪያ በሰፈነው ድህነት እና የከፋ የወጣቶች የሥራ አጥነት መባባስ ነው ይላል።
በተጨማሪም በአርብቶ አደሮች እና በአርሶ አደሮች መካከል ለመሬት የሚደረገው ፉክክርም ለችግሩ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ያምናል።
አብዛኞቹ አጋቾች የቀድሞ አርብቶ አደሮች የነበሩ የፉላኒ ማኅበረሰብ አባላት ናቸው ይላል። እነዚህ አጋቾችም በዋናነት የሃውሳ ማኅበረሰብ አርሶ አደሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ እንደሚያነጣጥሩም ይገልጻል።
“ሽፍቶቹን ሳናግራቸው በጥልቀት እረዳቸዋለሁ” ይላል።
ድርድሩ በዋናኝነት የሚካሄድበት ቋንቋ ሙስሊም የሚበዙበት የሰሜን ናይጄሪያ መግባቢያ በሆነው የሐውሳ ቋንቋ ነው። ሆኖም የአብዛኛዎቹ ታጋቾች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ፉላኒዎች የሚናገሩት ፉልፉልዴ የተሰኘው ቋንቋ ነው።
“መብራት እና መሠረተ ልማቶች በሌሉበት በጫካ ውስጥ በፈታኝ ሁኔታ ኑሮን እንደሚገፉ እነግራቸዋለሁ። መንግሥት ረስቶናል የሚል ስሜት እንዳላቸውም እረዳለሁ” ይላል።
አጋቾቹ መሳሪያ ታጥቀው እና በሞተር ሳይክሎች ነው የሚመጡት። ሰዎችን የሚያግቱትም እንዲሁ በዘፈቀደ አይደለም። ማን ምን አለው? የሚለውን መረጃ የሚሰጧቸው ተከፋይ ጠቋሚዎች አሏቸው።
ይህ ሰፊ እና ውስብስብ ሂደት ያለው ነው። በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ሽፍቶች ከ100 በሚበልጡ ቡድኖች ውስጥ ታቅፈው እንደሚሠሩ ሴንተር ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ከተባለው ተቋም የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ሱለይማን አጋቾቹን እንዴት ማናገር እንዳለበት ማወቁ ለስኬቱ አንዱ ቢሆንም፣ የድርድሩ ስኬት ወሳኙ የአጋቾቹ መሪ ነው ይላል። “አንዳንዶቹ ሽፍቶች ከተከፈላቸውም በኋላ ታጋቾችን አይለቁም። ተጨማሪ ገንዘብ ይፈልጋሉ” በማለት ያስረዳል።
አንዳንዶች ደግሞ ወዲያው የጠየቁት ገንዘብ እንደተከፈላቸው ታጋቾቹን ይለቋቸዋል።
ሂደቱ በጣም አሰልቺ እና አድካሚ ሊሆን ይችላል።
ታጋቾችን ለማስለቀቅ እስከ 50 ቀናቶች የሚወስድ ሲሆን ተደጋጋሚ እስከ 30 የሚደርሱ የስልክ ጥሪዎችም መደረግ አለባቸው።
“በተረጋጋ ሁኔታ እና ለስለስ ባለ መልኩ ልታናግራቸው ይገባል። ብልግና ይቃጣቸዋል፤ ይሳደባሉ። በዚሁ ሁሉ መካካል መረጋጋቱ ዋነኛ ጉዳይ ነው” ይላል።

በናይጄሪያ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ቢኖርም አጋቾች ጥሬ ገንዘብ አምጡ ይላሉ። በባንክ በሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች በቀላሉ ሊገኙ ስለሚችሉ የባንክ ሂደቱን አይመርጡትም። ክፍያውም ዝም ብሎ አይደለም የሚፈጸመው።
የጠየቁትን ገንዘብ የሚያደርሱትም የታገቱት ሰዎች ወላጅ ወይም ዘመድ እንደሆነም ነው ሱለይማን የሚያስረዳው።
“ሽፍቶቹ ይደውሉላቸው እና በሚቆዩባቸው ጫካዎች እንዴት ሊያገኟቸው እንደሚችሉ ደረጃ በደረጃ መመሪያ ይሰጧቸዋል። እዚያም ከደረሱ በኋላ ሽፍቶቹ ገንዘቡን ይቆጥሩታል” በማለትም ሱለይማን ሂደቱን ያስረዳል።
አንዳንድ ጊዜ አጋቾቹ ገንዘብ ሳይሆን ሞተር ብስክሌቶች፣ አልኮል ወይም ሲጋራዎችን በክፍያነት ይጠይቃሉ።
ሱለይማን በቅርበት የሚያውቀው አንድ ተማሪ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ከዩኒቨርስቲያቸው ሲታገቱ መንግሥት ለእያንዳንዱ ተማሪ 2 ሺህ 370 ዶላር ከፍሏል ይላል። መንግሥት ጉዳዩንም በምሥጢርነት ነበር የያዘው።
ይህ የሆነው መንግሥት ለአጋቾች የሚፈጸም ክፍያ ሕገወጥ ነው ብሎ ከመደንገጉ በፊት ነው።
“መንግሥት አሁን አይደለም በዚያንም ወቅትም ቢሆን በይፋ መክፈሉን በጭራሽ አያምንም። ምከንያቱም ለባለሥልጣናቱ ይህንን ማድረግ ማለት ውድቀትን መቀበል ነው። ነገር ግን እንደ ውስጥ አዋቂዎች በወቅቱ ምን እንደተፈጠረ እናውቃለን። ይህንን የሚያህል ገንዘብ አልነበረንም” ሲልም ያስረዳል።
ሱለይማን በእነዚያ ድርድሮች ውስጥም ተሳትፏል። አጋቾቹ በመጀመሪያ ለእያንዳንዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ታጋች 32 ሺህ ዶላር ጠይቀው የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ በድርድር ዝቅ ያለ ገንዘብ ላይ ስምምነት መደረሱን ያስረዳል።
መንግሥት ክፍያን ሕገወጥ ማድረጉን ተከትሎም አጋቾች የሚጠይቁትን ክፍያ የማሰባሰብ ሸክሙ የወደቀው በቤተሰቦቻቸው ላይ ነው። ጥቂቶች ናቸው የተጠየቁትን መክፈል የሚችሉት።
በርካቶች በእርዳታ ነው ገንዘብ የሚያሰባስቡት። አገሪቱ የምትናጥበት ያለመረጋጋት ችግር ምጣኔ ሃብቱን ማዳከሙን ተከትሎም ማሰባሰቡም ችግር ሆኗል።
ሽፍቶቹ አንዳንድ ጊዜም ታጋቾችን ይገድሏቸዋል ወይም የመክፈል ተስፋ በማይኖርበት ጊዜም ይለቋቸዋል።
በቅርብ ጊዜ ደግሞ እገታው ወደ ትምህርት ቤቶች ዞሯል።
ከትምህርት ቤቶች በጅምላ የሚታገቱ ተማሪዎች እና የግድያ ማስፈራሪያዎች የባለሥልጣናቱን ትኩረት ለመሳብ የተደረገ እንደሆነ ሱለይማን ያስባል።
“መንግሥት ይከፍለናል ብለው የሚያስቡ አሉ” ይላል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ባያምኑም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ክፍያ እንደፈጸሙ ሪፖርቶች ይወጣሉ።
በቅርቡ የታገቱ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ “አንድ ሳንቲም አንከፍልም” ሲሉ የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኒቡ አሳስበዋል።
ተማሪዎቹን እንዲያስቅቁም ለፀጥታ ኃይሎቻቸው መመሪያ ሰጥተዋል። በአውሮፓውያኑ 2022 – 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ የታጠቁ አጋቾች ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ መጠየቃቻቸውን ኤስቢኤም ኢንተለጀንስ የተባለ የደኅንነት አማካሪ ድርጅት ሪፖርት አመልክቷል።
የታጋቾቹ ተደራዳሪ ሱለይማንም ቢሆን የመንግሥት ባለሥልጣናት በክፍያቸው የሚቀጥሉ ከሆነ የመታገት ንግዱን ያበረታታል ይላል።
“ለታጋቾች የሚፈጸመው ክፍያ መታገትን ያበረታታል። ሽፍቶቹ በቀላሉ ገንዘብ እንደሚያገኙ ነው የሚያስቡት።”
ነገር ግን ታጋቾችን ለማስለቀቅ ምላሹ መንግሥት እንደሚለው ወታደራዊ ኃይል አይደለም ብሎ ያምናል። “መንግሥትን መመምከር የምፈልገው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ነው” በማለት ሱለይማን መልዕክቱን አስተላልፏል።