

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መለሰ
ዜና ‹‹የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራ ፖለቲካዊ መፍትሔ ይሻል›› ወ/ሮ…
ቀን: March 24, 2024
በፅዮን ታደሰ
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ድረስ የቀጠሉ ግጭቶች በመኖራቸው፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለሱ ሥራ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መለሰ አስታወቁ፡፡
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ይህንን ያሉት ከክልል ተወካዮችና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ 3.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ በግጭት ዓውድ ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች መድረስ ባለመቻሉ እንጂ ቁጥሩ ከተጠቀሰው በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሕግና የተቋማት ማዕቀፍ መኖር እንዳለበት ተናግረው፣ የተፈናቃዮችን ፍላጎት ታሳቢ ማድረግም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ሲደረግ የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለው፣ ‹‹የወደመባቸውን ወይም የተወሰደባቸውን ንብረት፣ መኖሪያ ቤትና መሬት በሙሉ ሊያገኙና ሊካሱ የሚችሉበት ሁኔታ ስለሚያስፈልግ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡ 74 በመቶ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በግጭትና በማኅበራዊ ቀውስ በመፈናቀላቸው ወደ ቀዬአቸው በሚመለሱበት ወቅት ደኅንነታቸውና ሥጋታቸው ታሳቢ ሊደረግ እንደሚገባ አክለዋል፡፡
ከተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ተወክለው በውይይቱ ላይ የተገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው፣ ለዓመታት በመጠለያ ጣቢያዎች መቆየታቸውን ገልጸው ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ አንድ ተወካይ፣ ከ400 በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ቢደረጉም እንዲቋቋሙ እንዳልተደረገ ገልጸዋል፡፡ ተመላሾቹ የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸው፣ የዕገታ ወንጀል እየተፈጸመባቸው እንደሆነ፣ ቤት የሌላቸውና ኪራይ መክፈል የማይችሉት ሜዳ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የቦሳ ጎኖፋ ምክትል ኮሚሽነር ሜሌቻ ሎጊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከተመላሾች መካከል የታገቱ አለመኖራቸውንና የፀጥታ ሥጋት እንደሌለባቸው ገልጸዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በአራት ዞኖች 1.3 ሚሊዮን የሚገመቱ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡
‹‹ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑትን ብቻ መልሰናል›› ያሉት የአማራ ክልል ተወካይ፣ የተመለሱትን ተፈናቃዮች ለመቀበል ፈቃደኛ የሆነው የኦሮሚያ ክልል የገባውን ቃል ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የትግራይ ክልል በአገሪቱ ካለው የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የማኅበራዊ ጉዳይና መልሶ ማቋቋም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘውዴ ኪሮስ ተናግረው፣ ከክልሉ አራቱም አቅጣጫዎች የተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖች አሉ ብለዋል፡፡ በአብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ኬላዎችና ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወድመዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት 1.5 ሚሊዮን ተፈናቃዮች በራሳቸው ፈቃድ ከመጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው ወደ ቀዬአቸው ቢመለሱም፣ እንደገና የመፈናቀል አደጋ እንደገጠማቸው ጠቁመዋል፡፡
ተፈናቃዮች ከሚያነሱት ዘላቂ መፍትሔ ባለፈ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሲኖሩ የመታወቂያና የመሠረታዊ አገልግሎቶች ችግር እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጥበቃና ድጋፍን አስመልክቶ በርካታ ስምምነቶችን እንደፈረመች ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም እ.ኤ.አ. 2009 የተፈረመው የካምፓላ ስምምነት ይጠቀሳል፡፡ የስምምነት ማዕቀፉ ፈራሚ አገሮች ሰዎችን በዘፈቀደ ከማፈናቀል ሊታቀቡ፣ ሊከለክሉና ሊከላከሉ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡