
ከ 4 ሰአት በፊት
በሴኔጋል በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ አሸናፊ እንደሚሆኑ ግምት ተሰጠ።
በርካታ ተቀናቃኞች ሽንፈታቸውን አምነው መቀበላቸውም ተሰምቷል።
ከሦስት ዓመታት አለመረጋጋት እና በስልጣን ላይ በነበሩት ማኪ ሳል ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ሚሊዮኖች እሑድ በተደረገው ሰላማዊ ምርጫ ተሳትፈዋል።
ለፕሬዝዳንትነት 19 እጩዎች በምርጫው ቀርበው ነበር።
የገዢው ፓርቲ ተወካይ አማዱ ባ ተሸንፈዋል የሚሉ ሪፖርቶችን ውድቅ በማድረግ አሸናፊውን ለመወሰን ሁለተኛ ዙር ምርጫ ይካሄዳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የ44 ዓመቱ ፋዬ ከምርጫው በፊት ታስረው በነበሩት በኡስማን ሶንኮ የሚመራው የፓስቴፍ ፓርቲ አባል ናቸው። ሶንኮ በቀረበባቸው የስም ማጥፋት ክስ ከውድድሩ ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በቴሌቭዥን በታወጀው የመጀመሪያው ውጤት ፋዬ አብላጫ ድምጽ ማግኘታቸው ሲነገር በዋና ከተማዋ ዳካር ጎዳናዎች ላይ በርካቶች ደስታቸውን ገልጸዋል።
ደጋፊዎቹ ርችቶችን ሲተኩሱ፣ የሴኔጋልን ባንዲራ ሲያውለበልቡ እና ቩቩዜላዎችን ሲነፉ ታይተዋል።
- በፖሊስ ላይ ተስፋ የቆረጡ ደቡብ አፍሪካውያን የጦር መሳሪያ እየታጠቁ ነውከ 5 ሰአት በፊት
- በሞስኮው ጥቃት ተሳታፊ ናቸው የተባሉት ላይ ክስ ተመሠረተከ 4 ሰአት በፊት
- እንግሊዛዊቷ የዓለማችን ከባዱን የሩጫ ውድድር በመጨረስ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነች24 መጋቢት 2024
ውጤቱን ተከትሎ አምስት የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ፋዬን አሸናፊ አድርገው አውጀዋል።
አንታ ባባካር ንጎም ከፍተኛ ግምት ካገኙ እጩዎች አንዱ የነበሩ ሲሆን ባወጡት መግለጫ ለፋዬ ስኬትን ተመኝተዋል።
ሌላኛው ተቀናቃኝ ሶንኮ እንዲሁ ፋዬን ደግፈዋል።
የወቅቱ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳለ በዚህ ፕሬዝዳንታዊ ውድድር ተሳታፊ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይህን በሴኔጋል ታሪክ በእጩነት ያልቀረቡ በስልጣን ላይ ያሉ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት አድርጓቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሚመሩት የገዥ ፓርቲያቸው ጥምረት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የ62 ዓመቱን ባ እጩ አድርጎ አቅርቦ ነበር።
የባ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን “ከእኛ ባለሙያዎች ቡድን የተገኘውን ውጤት ከግምት ውስጥ በማስገባት በጣም ከከፋ ወደ ሁለተኛ ዙር ምርጫ እንደምንሄድ እርግጠኞች ነን” ብሏል።
ሴኔጋል ወደ 18 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7.3 ሚሊዮን ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል ።
እስካሁን ከ15 ሺህ 633 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ምን ያህሉ እንደተቆጠሩ ግልጽ አይደለም። የመጨረሻ የምርጫ ውጤቶች ማክሰኞ ይጠበቃሉ።
ምርጫው ባለፈው ወር ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ሳል ለሌላ ጊዜ ማስተላለፋቸው የተቃዋሚዎችን ሕይወት የቀጠፈ ተቃውሞ አስከትሎ ነበር።