
ከ 5 ሰአት በፊት
በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ከተማ ነዋሪ የሆነው ምሎትሽዋ ፔንሰን ላለፉት ስድስት ዓመታት የትም ቦታ ሲሄድ ሽጉጡ ተለይቶች አያወቅም። ወደ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች እና ጂም ሲሄድ ሁሉ ታጥቆ ነው።
በየዕለቱ ከፍተኛ ወንጀል በሚፈጸምባት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚታጠቀው ሽጉጥ የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን ለሚያዘጋጀው ለፔንሰን ወሳኝ የሆነ ነገር ነው።
“ጠንቋይ ስላልሆንኩ መቼ ጥቃት እንደሚፈጸምብኝ አላውቅም” በማለት እራሱን ለመከላከል ሽጉጡን ዘወትር ታጥቆ እንደሚንቀሳቀስ ፔንሰን ለቢቢሲ ተናግሯል።
“እራሴን ለመከላከል ሽጉጤን ለመጠቀም የተገደድኩባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው” በማለትም አንድ ምሽት ከእራት ሲመለስ በስለት አስፈራርቶ የኪስ ቦርሳውን ለመውሰድ ስለተደረገበት ሙከራ ያስታውሳል።
በዚህ ጊዜ ሽጉጡን አውጥቶ ቦርሳውን ሊወስድ የነበረው ቀማኛ ያየዘውን ቢላ በማስጣል ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ከትቶታል። ነገር ግን አንድም ጥይት አልተኮሰም።
ፔንሰን ቁጥራቸውን ያልገለጻቸው የጦር መሳሪያዎችን ለመታጠቅ የተገደደው የአገሪቱ መንግሥት እና ፖሊስ ሊያስጠብቁለት ያልቻሉትን ደኅንነቱን ለመከላከል ብቻ እንደሆነ ይናገራል።
በፔንሰን ሃሳብ የምትስማማው የጆሃንስበርግ ነዋሪዋ ሊኔት ኦክስሌይ፣ እንዲህ ዓይነቱን አደጋ “ፊት ለፊት መጋፈጥ የግድ ነው” ትላለች።
ለዚህም የጦር መሳሪያ ባለቤት የሆኑ ሴቶች እራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችል ሥልጠናን የሚሰጥ ድርጅት አቋቁማለች።
የ12 የጦር መሳሪያዎች ባለቤት የሆነችው የ57 ዓመቷ የጆሃንስበርግ ከተማ ነዋሪ “ቆንጆ ጫማ ከምገዛ ይልቅ አዲስ ሽጉጥ መግዛትን እመርጣለሁ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
‘ገርልስ ኦን ፋየር’ የተባለው ድርጅቷ የተደፈሩ፣ የተዘረፉ ወይም አንዳች ዓይነት ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶችን የሚያግዝ ነው። በደቡብ አፍሪካ የሚፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት መጠን በዓለም ላይ ከፍተኛ ከሚባሉት መካከል ይመደባል።
- ሦስት የግብፅ ኦርቶዶክስ መነኮስት በደቡብ አፍሪካ ገዳም ውስጥ ተገደሉ13 መጋቢት 2024
- የደቡብ አፍሪካው ኦፕሬሽን ዱዱላ፡ “የውጭ ሃገር ዜጎችን የምንጠላበት ምክንያት”18 መስከረም 2023
- በደቡብ አፍሪካ በልደት ድግስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 8 ሰዎች ተገደሉ30 ጥር 2023

ነፍሰጡር እያለች በቤቷ ላይ ዘረፋ በተፈጸመበት ወቅት በእሷ እና በስድስት ዓመት ልጆ ፊት ባሏ ተተኩሶ የተመታባት ሴት ድጋፍ ፍለጋ ድርጅቱን ተቀላቅላለች።
የጦር መሳሪያ አጠቃቀም አሠልጣኝ የሆነችው ኦክስሌይ እንደምትለው “አሁን ሰዎች ከራሳቸው ውጪ ማንም የሚከላከላቸው እንደሌላ እየተረዱ ነው።”
ስለዚህም “በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ያለው የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ባህል እራስን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ ነው” ትላለች።
የጦር መሳሪያ መታጠቅን በተመለከተ የደቡብ አፍሪካ ሕግ የአገሪቱ ዜጎች ደብቀው አስከያዙ ድረስ ፈቃድ ያለው መሳሪያ ይዘው መንቀሳቀስ ይችላሉ።
ከሦስት ዓመት በፊት የጦር መሳሪያ መታጠቅን በሚቃወመው ድርጅት ‘ገን ፍሪ ሳውዝ አፍሪካ’ በተደረገ ጥናት በአገሪቱ ውስጥ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ሕጋዊ የጦር መሳሪያ ባለቤቶች አሉ፤ ይህም ከአጠቃላይ የደቡብ አፍሪካ አዋቂዎች መካከል ስምንት በመቶዎቹ የታጠቁ ናቸው ማለት ነው።
በወንጀል ላይ ከሚደረገው ዘመቻ አንጻር ሲታይ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ሽንፈት የገጠመው ሆኖ ነው የሚታየው።
በአገሪቱ የሚፈጸሙ የግድያ ወንጀሎች በ20 ዓመታት ውስጥ ከታዩት ከፍተኛው ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ለዚህ ደግሞ ሽጉጦች ተመራጭ የጦር መሳሪያዎች ናቸው።
የጦር መሳሪያ መስፋፋት ተቃዋሚ የሆነው እንቅስቃሴ ዳይሬክተር አዴሌ ኪርስተን ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ ወንጀል በደቡብ አፍሪካ እየጨመረ ብቻ ሳይሆን፣ በጦር መሳሪያ የሚፈጸሙ ጥቃቶች “ባህሪም እየተቀየረ ነው” ይላል።
በጦር መሳሪያ የሚፈጸሙ የጅምላ ጥቃቶች እና ግድያዎች በአሁኑ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ መለያ “ገጽታ እየሆኑ ነው” ይላል።
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከፒተርማሪትስበርግ ከተማ አቅራቢያ የ13 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ 10 የአንድ ቤተሰብ አባላት ቤታቸው ውስጥ በጥይት መገደላቸው አገሪቱን ድንጋጤ ውስጥ ከቶ ነበር።
አብዛኞቹ የወንጀል ድርጊቶች የሚፈጸሙት በሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች ነው። የጦር መሳሪያ መስፋፋት ተቃዋሚው ድርጅት እንደሚለው በአገሪቱ 2.35 ሚሊዮን ያህል ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች በዝውውር ላይ አሉ።
ለእነዚህ ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች ምንጭ ናቸው ተብለው ከሚታመኑት መካከል ደግሞ ዜጎችን ይጠብቃል የሚባለው የአገሪቱ የፖሊስ ተቋም አንዱ ነው።

እንደ ማሳያም በመጥፎነት የሚጠቀሰው የቀድሞው የፖሊስ መኮንን ክርስቲያን ፕሪንስሉ ጉዳይ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2007 አስከ 2015 ባሉት ዓመታት ውስጥ የፖሊስ አባሉ 2,000 የሚሆኑ ሽጉጦችን ለወሮበሎች ሸጧል። እነዚህ የጦር መሳሪያዎች ደግሞ ከ1,000 በላይ ለሚሆኑ ግድያዎች እና ከ89 ልጆች ሞት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሏል።
ኪሪስተን እንደምተለው ሕዝቡ በፖሊስ ላይ ያለው መተማመን ክፉኛ ተሸርሽሯል።
በዚህም የተነሳ የተፈጠረውን የደኅንነት ክፍተት ለመሙላት ከመቼውም በላይ በርካታ ሰዎች ደኅንታቸውን ለመጠበቅ የሚችሉትን ሁሉ በራሳቸው አቅም እያደረጉ ነው።
በደቡብ አፍሪካ ዜጎች መሳሪያ የመታጠቅ ፍቃድ ለማግኘት ከ21 ዓመት በላይ መሆን፣ ሰፋ ያለ የመሳሪያ አጠቃም ሥልጠና፣ በርከት ያሉ ፈተናዎችን እና የአእምሮ ጤና ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
ስለዚህ የመሳሪያ ባለቤትነት ፈቃድ ማግኘት የተራዘመ እና አሰልቺ ሂደት ሊሆን ይችላል።
ይህም ሆኖ ግን ባለፉት አስር ዓመታት መሳሪያ ለመታጠቅ የሚቀርቡ ማመልከቻዎች ቁጥር በአራት እጥፍ መጨመሩን የደቡብ አፍሪካ የዜና ድረ ገጽ የሆነው ‘ኒውስ24’ ባደረገው ምርመራ አመልክቷል።
በደቡብ አፍሪካ “የጦር መሳሪያ መታጠቅ እራስን ለማዳን ዋነኛ ተዋናይ ለመሆን መወሰን ነው” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገረው የጦር መሳሪያ አማካሪው ጊዲዮን ጁበርት ነው።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ጦር መሳሪያ የመታጠቅ ባህል መሠረት የያዘው፣ አስከ አውሮፓውያኑ 1994 ድረስ በነበረው የጥቂት ነጮች አገዛዝ ስር አገሪቱ ባለፈችበት የግጭት ታሪክ ነው። ኋላ ላይ ቢፈቀድም ለዘመናት ጥቁሮች በሕጋዊ መንገድ መሳሪያ መታጠቅ አይችሉም ነበር።
አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ የጦር መሳሪያ ይዘው የገቡት በ1600 አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ የደች ሰፋሪዎች ወራሽ የሆኑት አፍሪካነርስ እስካሁን ድረስ የሚስተዋል በመሳሪያ ባለቤትነት ላይ ልዩነትን ፈጥረው ቆይተዋል።
በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በሶቪየት የሚመራው የምሥራቁ ዓለም ለደቡብ አፍሪካ ፀረ አፓርታይድ ታጋይ ቡድኖች በሺዎች የሚቆጠሩ ኤኬ-47 (ካላሽንኮቭ) ጠመንጃዎችን አስታጥቀዋል። ይህም የነጻነት እንቅስቃሴው ዓርማ ሆነ።
የጦር መሳሪያ መስፋፋትን በሚቃወመው የደቡብ አፍሪካ ቡድን የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየው በ1986 እና 1996 (እአአ) መካከል ባሉ ያለመረጋጋት እና የስጋት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ የጦር መሳሪያ ባለቤትነት አሃዝ በ40 በመቶ አሻቅቧል።
ምክንያቱ ደግሞ በአብዛኛው አናሳዎቹ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን በኔልሰን ማንዴላ የሚመራው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ሥልጣን መያዝ ስጋት ስለፈጠረባቸው ነው።

ከአፓርታይድ ሥርዓት መወገድ በኋላ ኤኤንሲ ላለፉት 30 ዓመታት በሥልጣን ላይ ይገኛል፤ በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ምርጫ ፓርቲው በአገሪቱ ፓርላማ ውስጥ ያለውን የበላይነት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያጣ ይችላል።
አሁንም በድጋሚ ደቡብ አፍሪካውያን ፊታቸውን ወደ ጦር መሳሪያ እያዞሩ ነው፣ ነገር ግን ከዚህ በፊት ከትጥቅ ጋር ያለው ባህል ገጽታ በተወሰነ ደረጃ እየተቀየረ ነው።
ጁበርት እንደሚለው ቀደም ባለው ዘመን የጦር መሳሪያ የሚታጠቁ ደቡብ አፍሪካውያን “በ30ዎቹ አጋማሽ ያሉ፣ ነጮች፣ ወንዶች እና በአጠቃላይ ደግሞ አፍሪካነርስ ነበሩ” ይላሉ። አሁን ግን ይህ ገጽታ ተለውጦ “ሰፊ ስብጥር ያለው” መሆኑን ይገልጻሉ።
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አገልግሎት የፖሊሲ እና ጥናት ክፍል ሪፖርት እንደሚያመልከተው በአውሮፓውያን 2014 በአገሪቱ ውስጥ መሳሪያ ከታጠቁ ዜጎች መካከል የሴቶች አሃዝ እስከ 19 በመቶ ይደርስ ነበር።
ኪሪስተን እንደምትለው ምንም እንኳን የጦር መሳሪያ በባለቤትነት የያዙ ሰዎች ዓይነት እየተቀየረ ቢሆንም፣ የቅኝ ግዛት ዘመን የመታጠቅ አስተሳሰብ በተለይም በዕድሜ በገፉ ነጭ ወንዶች ዘንድ ባለበት ቀጥሏል።
በብዙኃኑ የጥቁሮች መንግሥት ላይ እምነት ስለሌላቸው ሽማግሌ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን “በእነሱ እና ‘በሌሎች’ መካከል ያለው አንድ ነገር የጦር መሳሪያቸው እንደሆነ ያምናሉ” ትላለች።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች እራሳቸውን ለመጠበቅ እና ለመከላከል ከፖሊስ ይልቅ ፊታቸውን ወደ ግል የደኅንነት ጥበቃ ድርጅቶች ማዞራቸው ግልጽ ነው።
የአገሪቱ የግል ደኅንነት ተቋማት ተቆጣጠሪ ባለሥልጣን ያወጣው እና በፓርላማ የተጠቀሰ ሪፖርት እንዳሳየው የደኅንነት ጥበቃ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ባለፉት አስር ዓመታት የግል የደኅንነት ተቋማት ብዛት በ40 በመቶ ጨምሯል።
የደኅንነታቸው ነገር በእጅጉ ከሚያሳስባቸው መካከል አንዷ የሆነችው የ25 ዓመቷ ታይዋን የተወለደችው ደቡብ አፍሪካዊት ዙ-ሁይ ቻንግ ለቢቢሲ እንደተናገረችው፣ አባቷን ለመጀመሪያ ጊዜ ሽጉጥ ታጥቆ ያየችው ልጅ እያለች ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተዘዋወሩ በኋላ ነበር።
“ከመዋዕለ ሕጻናት ወደ ቤት ሊወስደኝ ሲመጣ ሁልጊዜም ሽጉጡን የታጠቀበት ቀበቶን በደረቱ ላይ እመለከት ነበር” ትላች።
ምንም እንኳን ለጦር መሳሪያ በጎ አመለካከት ከሌለባት ታይዋን ቢመጡም፣ በደቡብ አፍሪካ የተፈጠረባቸው ቋሚ ስጋት ቤተሰቡ የአገሪቱን የጦር መሳሪያ የመታጠቅ ባህልን እንዲላመድ አስገድዶታል።
አሁን እሷም የራሷን የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ የሚያስችላትን ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ ናት።
“ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የማልኖር ቢሆን ኖሮ፣ የጦር መሳሪያ እንዲኖረኝ ፈጽሞ አላስብም ነበር” ትላለች።
ለምሎትሽዋ ፔንሰንም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የጦር መሳሪያ መታጠቅ ብዙም ማሰላሰል የማያስፈልገው ቀላል ውሳኔ ነው። ሽጉጦቹንም እራሱን እና ቤተሰቡን የሚጠብቅባቸው ውድ እቃዎቹ እንደሆኑ ነው የሚገልጻቸው።