ክፉ ቀን ሲዘከር
የዶ/ር ተስፋየ ደበሳይ የመጨረሻ ጽዋ ( ዶክተር መንግስቱ ሙሴ )
========================

መጋቢት 15 1969 ዓም ከእንጨት አልጋየ እንደተጋደምሁ ያንዘመን የአጭር ሞገድ ሬዲዮ ዜና ስርጭትን ማዳመጥ የኢንፎርሜሽን ዋና መንገድ ነበር። ድፍን 1969 ዓም መልካም ዜና የሚሰማበት ዘመን አልነበረም ቀደም ብሎ በጥር 29 1969 የሆነው የድፍን ኢትዮጵያን ሕዝብ አፍ ያስጨበጠ የርእሰብሔሩን ጄ ተፈሪ በንቲ እና ሌሎች ባለስልጣናት መርዶን ሰምተን ነበር። ጄኔራሉ ያን ቀን ስለእርቅ መውረድ እና ሰላም ነበር ለሕዝብ ያቀረቡት የገጠማቸው ግን ሌላ ነበር።
በሁለተኛው ወር አጋማሽ መጋቢት 15 ቀን ግን የብዙ ዜጎች የሐገር ተስፋ የነበረው ምሁር እና የኢሕአፓው መሪ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ማለፉን የምታውጀዋ ዜና በብዙ ወታደራዊ ማርሽ ታጅባ በተለመደው መርዶኛ ተነበበች።
እኔም ከተጋደምሁበት እንኳን ንቅንቅ ሳልል የዜናው ክፋት እና ምንነት አደመጥሁ በእጅጉም አስደነገጠኝ። ወቅቱ የትግል በመሆኑ ቀደም በነበሩ ቁልፍ እና አሳቢ የሐገር ልጆችን ገድሎ ያነን ለሕዝብ ለማርዳት የሚከተለው የዜና የፉከራ የፍየል ወጠጤ እና መሰል ዜናወች ልቤን ያነዱት ያበሳጩት እንጅ እንደዚህ ቀን ድንጋጤ ምርር ያለ ሐዘን አስከትለውብኝ አያውቁም ነበር።
“ተስፋየ ደበሳይ” ማን መሆኑን ያወቅሁም በዚህ ዜና ነው። ከወራት በፊት የእነ ብርሐነ መስቀል ረዳ፤ ጌታቸው ማሩ (ሀ እና ለ) አንጃ ፈጥሮ በመሰረቱት ድርጅት ላይ ተቃራኒ መሆናቸውን በድርጅት አስራር አውቄ ነበር። በተለየ የብርሐነ መስቀል ረዳ ጉዳይ በዚያ ዘመን የኢትዮጵያ አብዮታውያን ሁሉ የአፍ መፍቻ የነበር ግዙፉ ሰው በልዩነት መለየት በድርጅቱ እንቅስቃሴ በግዜው ያስከተለው እንቅፋት ባለመኖሩ (ለግዜም ቢሆን) ከብረት በጠነከረ ዲስፕሊን እና ሕቡዕነት የሚመራው ድርጅታችን በእርግጥም ከባድ እና ግዙፍ አካሄዳቸውን የሚያውቁ እና ህልመኛ መሪወች እንዳሉት በግሌ በጽኑ እንዳምን ያደረገ ለአባላቱም ተስፋ የሰጠ በመሆኑ በነበረን ድርጅታዊ እንቅስቃሴ ከመተማመን ውጭ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አላደረብኝም አብረውኝ ከሚሰሩ ጓዶችም ላይ ያደረሰው ተጽእኖ አልነበረም። እንአንድ የዘመኑ ሪቮ ከመሪ ድርጅቴ ጋር ወደፊት የሚል የቆረጠ አላማ ስለነበረኝም በጎመራው አብዮታዊ ተግል ውስጥ የግሌን ድርሻ ከማበርከት ባለፈ ሌላ ሕይወት እንዳልነበረኝ እኔም የትግል ጓዶቸውም አምነን ቀጥለናል።
ፍፁም ነው እምነቴ!! ለትግሉ ነው ህይወቴ!
ልጓዝ በድል ጎዳና!! በወደቁት ጓዶች ፋና!
በሚለው መፈክራዊ መዝሙራችን ትግሉን ከመቀጠል ውጭ የልብ ወላዋይነት በማናችንም ልቦና የለም አልነበረም። እናም ይህች የመጋቢት 15 ቀን 1969 ዓም የምሽት ዜና ከልቤ ምርር ያደረገች ሀዘን ብትጥልብኝም ለኋለኛው እና ቀጣዩ ማንነቴ እና የተጋድሎው ትግል ግን ይህ ነው የማይባል ወኔ አይበገሬነትን አሳቅፋኝ አለፈች።
ዜናዋ የጓድ ተስፋየ ደበሳይን ሞት አርጅ ናት። የተለመደው መርዶኛው አንባቢ አጉልቶ ለማሳየት ደርጉ (የመንግስቱ ቡድን) አቸናፊነትን፤ አይበገሬነትን፤ እና በዚያን ዘመን የሰጋው ያስፈራው የኢሕአፓ ታጋዮች ተስፋ ይቆርጡ ዘንድ የተሰላ የደርጉ (የመንግስቱ ቡድን) አላማ ነበር።
ሆኖም ግን ዶ/ር ተስፋየ ደበሳይ እጁን አልሰጥ ብሎ ከሰባተኛው ፎቅ ተወርውሮ ተፈጠፈጠ። ሆኖም እዚያ ከእርሱ ሬሳ ዙሪያ አሰፍስፎ በድንጋጤ የተኮለኮለው ገዳዩ ቡድን እንኳን እጁን እስከህይወቱ ሊይዝ ቀርቶ ፈራሽ ስጋውን ሰባስቦ ለመያዝ ያላስቻለ የመስዋ’እትነት ገድል አሳየ። ይህ በቀጣይ ቀናት፤ ሳምንታት እና ወራት ከላይ ያሰፈርኋት የድርጅቴ መዝሙር እውን ሆና በመሪው የተተገበረች የአይበገሬነትን አሻራ በሁሉም ታጋይ ልብ አስጨበጠች። ለዚህም ይመስለኛል አያሌ ጓዶች በአራጁ የመንግስቱ ቡድን ሲያዙ “ፍጹም ነው እምነቴ! በሚል ጽኑ እምነት ተረብሸው ሳይሆን በጀግንነት መሰዋትን መሆን ባህል ያዳበሩት። በበኩሌም ደርጉ ከያዘኝ በኋላ እንዲገድለኝ ሳልፈቅድለት እራሴን መልሶ ነጻ የማውጣት ተጋድሎየን የፈጸምሁ ውጤቱም የቀጣዩ ህይወቴ ምሰሶ የሆነው።
ፀሃፊው ዶክተር መንግስቱ ሙሴ ( ቴክሳስ ፤ አሜሪካ )
መሪ ሲባል 400000 ሽህ ወታደር ሜዳ ላይ አፍስሶ እንደፈረጠጠው እንደመንግስቱ ኃይለማርያም ሳይሆን እንደተስፋየ ደበሳይ ገዳይ አስገዳይ እንደ ነገደ ጎበዜ ወይንም እንደ ኃይሌ ፊዳ ማለት አለመሆኑን ዶ/ር ተስፋየ ደበሳይ በእሬሳው አስተምሮን አልፏል። መሪ ሲሉ አገር ልቀቅ እና ይህን የመጣውን የአሰሳ ሳምንት ዘወር ብለህ ቆይ ሲባል አይሆንም ብሎ አዲስ አበባን ከዚያ ቀሳፊ የመጋቢት 15 ቀን 1969 ዓም አሰሳ የሚችለውን ያህል ጓዶችን ቦታ ለማስያዝ ክፍለ ሐገር አውቶቡስ ተራ እራሱን ደብቆ ለጓዶቹ የመጭዋን የሲዖል ቀንን እንዲያመልጡ ሲሸኝ እና ቦታ ሲያሲዝ ሰንብቶ የዋናዋን ቀን የሞት ጽዋ እራሱ የተጎነጨ ማለት ነው (ተስፋየ ደበሳይ ማለትም ይህን የመሪነት መርህ በአሻራው አስፍሮ ያሳየ ማለት ነው)!! ለዚያ ነው መሪነት በተስፋየ ደበሳ ወርድ እና ቁመት ሳይሆን የት የለሽ ጽናት የተከታይ ፍቅር፤ ማሰብን እና ቀድሞ መሰዋትን ያህል ልክ እንዳለው ያስተማረ ብርቅየ የሚገባውን ያህል እስካሁን ያልተባለለት ሰማዕት ማለት ነው!!
እናም ሁሌ ይህች የመጋቢት 15 ዞራ በመጣች ቁጥር ለአለፉት 47 አመታት በእዝነ ልቦናየ የሚመጣው የሰማሁአት የሞት ዜና፤ የነበርሁባት ሁኔታ እና በማንነቴ ውስጥ የተጨመረው አይበገሬነት ወኔ ሆኖ ይሰማኛል። ዛሬም ተስፋየን አይነት መሪወች እንዲወጡልን፤ የግል ዝናን፤ የመኮፈስን፤ የስግዱልኝ እዩኝ ባይነትን የተጸየፉ ግን ለሚመሩት ፍጹም እርህራሄን እስከ እራስን መስጠት የሚዘልቁ እንዲፈጠርልን በበኩሌ የሁልግዜ ፀሎቴ ነው!!!