የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

25 መጋቢት 2024, 15:39 EAT

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማጭበርበር ወንጀል ክስ እንዲከፍሉ የተጣለባቸውን የዋስትና ገንዘብ ካልስያዙ ንብረታቸው ሊያዝ ነው።

ለዋስትና 464 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ የታዘዙት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የተሰጣቸው ቀነ ገደብ ዛሬ [ሰኞ] ይጠናቀቃል።

ትራምፕ ገንዘቡን ካልስያዙ አሊያም ቀነ ገደቡ እንዲራዘም ካላስደረጉ የኒው ዮርክ ባለሥልጣናት የባንክ ሒሳባቸውን ሊዘጉባቸው ወይም ንብረታቸውን ሊይዙባቸው ይችላሉ።

ትራምፕ የተጣራ ሀብታቸውን አሳንሰው በመናገራቸው ነው ይህ ክስ የተመሠረተባቸው።

በሌላ ክስ የወሲብ ፊልም ተዋናይቷ ስቶርሚ ዳንኤልስ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት የከሰሰች ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ቀነ ቀጠሮ እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል።

ትራምፕ የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ በአካል ተገኝተው እንደሚታደሙ እና ጠበቃዎቻቸው ክሱ ውድቅ እንዲሆን ሲከራከሩላቸው ሊከታተሉ እንደሚችሉ ተገምቷል።

ባለፈው ሳምንት የትራምፕ ጠበቃዎች ፕሬዝዳንቱ ገንዘቡን ለማቅረብ ከበርካታ ኩባንያዎች የገንዘብ እርዳታ ጠይቀው እንዳልተሳካላቸው ተናግረው ነበር።

አንድ ግለሰብ የዋስትና ገንዘብ ከአንድ ኩባንያ ለማግኘት ገንዘቡን መመለስ የሚያስችል አቅም በጥሬ ገንዘብ አሊያም በአክሲዮን መልክ እንዳለው ማስተማመኛ ማቅረብ አለበት።

የአደባባይ ሰዓት

ትራምፕ ቀነ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የዋስትና ገንዘባቸውን መከፍል ከቻሉ ንብረታቸው በመንግሥት ከመያዝ ይድናል ማለት ነው።

ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው እንደጠቆሙት 500 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ጥሬ ገንዘብ እጃቸው ገብቷል።

የኒው ዮርክ ግዛት ዳኛ ናቸው ፕሬዝዳንቱ ብድር ለማግኘት ሲሉ የተጣራ ሀብታቸውን አዛብተዋል በሚል የዋስትና ገንዘብ እንዲከፍሉ የወሰኑባቸው።

ትራምፕ ብቻ ሳይሆኑ ወንድ ልጆቻቸውም የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

የኒው ዮርክ ዐቃቤ ሕግ ሌቲኣ ጄምስ፤ ትራምፕ ገንዘቡን ፈልገው እንዲያመጡ የ30 ቀናት ዕድሜ የሰጧቸው ሲሆን ቀነ-ገደቡ ከሰዓታት በኋላ ይጠናቀቃል።

ዐቃቤ ሕጓ ትራምፕ በታዘዙት መሠረት ገንዘቡን የማይከፍሉ ከሆነ በግዛቱ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉ ንብረቶቻቸውን ለመያዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሰሜን ኒው ዮርክ ሰቭን ስፕሪንግስ የተባለ ሪዞርት፣ የጎል መጫወቻ እና 82 ሄክታር የሚሆን መሬት አላቸው።

ኒው ዮርክ ከተማ የሚገኘው 58 ፎቅ ትራምፕ ታወር፣ ማር-አ-ላጎ የተሰኘው ታዋቂ ሪዞርታቸውንና ሌሎች ፍሎሪዳ ገዛት የሚገኙ ንብረቶቻቸውም የመያዝ አደጋ ተደግኖባቸዋል።

ፎርብስ የተሰኘው ጋዜጣ ባስቀመጠው ግምት መሠረት ትራምፕ 2.6 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ሀብት አላቸው። እሳቸው ግን ባለፈው ዓመት 400 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ተንቀሳቃሽ ሀብት ነው ያለኝ ብለው ነበር።

ባለፈው ጥር ኢ ጂን ካሮል የተባሉ ሴት ስሜን አጥፍተዋል ብለው ከሰዋቸው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ 83 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ወስኖባቸዋል። ትራምፕ በዚህም ክስ ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ክስ ቀርቦባቸው የተፈረደባቸው ብቸኛው ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፣ በአራት የተለያዩ ክሶች ገና ውሳኔ እየጠበቁ ይገኛሉ።