አቶ ጌታቸው ረዳ

25 መጋቢት 2024, 14:37 EAT

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ የአማራ ክልል በመማሪያ መጽሐፍት ላይ ያውጣ ካርታ ላይ በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ አስጠነቀቀ።

ካቢኔው እንዳለው የአማራ ክልል የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች የሚያካትተው ካርታን የማያርም ከሆነ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን ይወስዳል ሲል አስጠንቅቋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ መግለጫውን ያወጣው ሁለቱ ክልሎች ይገባናል የሚሏቸው እና በአማራ ክልል ቁጥጥር ስር የሚገኙ አወዛጋቢ ቦታዎችን ያካተተ ካርታ የአማራ ክልል በማውጣቱ ነው።

እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በአማራ ክልል ውስጥ እየተሰራጩ ባሉ የመማሪያ መጽሐፍት ላይ ሁለቱ ክልሎች የሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች በአማራ ክልል ስር ተካተው ቀርበዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔም የትግራይ ክልል ግዛቶች ናቸው ያላቸው ቦታዎች የአማራ ክልል አካል ያደረገ ካርታ በመማሪያ መጽሐፍ ላይ መካተቱን በመቃወም ሌላ ችግር ሊያስከትል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

በሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ እየተነሳባቸው ያሉት አካባቢዎች የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ በአማራ ክልል ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ይታወቃል።

በትግራይ ክልል ስር የነበረው አወዛጋቢው ምዕራብ ትግራይ/ወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ከሱዳን እና ከኤርትራ ጋር የሚዋሰን ሠፊ ለም መሬት ሲሆን፣ በአማራ ክልል ያላግባብ ወደ ትግራይ ተካሏል በሚል ጥያቄ ሲነሳባት የቆየ ነው።

በትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎም በአማራ ክልል ኃይሎች ስር የሚገኝ ሲሆን፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላም በፌደራል መንግሥቱ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል ለይገባኛል ጥያቄው ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ነበር።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አሁን፤ የትግራይን መሬት የያዘ ካርታ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ማካተት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ብቻ ሳይሆን፤ “የትግራይ ሕዝብን ከፋፍሎ የማጥፋት ዘመቻ እንዳይቆም . . . እየተሠራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው” ብሏል።

ክልሉ ይህንን የማስተካከል እርምጃ የማይወስድ ከሆነ “በቀጣይ ለሚፈጠር ችግር የአማራ ክልል ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳል” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያው አስተላልፏል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት መፍትሄ እንደሚሰጠው አመልክቷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መግለጫ የአማራ ክልል በኃይል ተቆጣጥሮ በያዛቸው አካባቢዎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ግፍ እና መከራ እየተፈጸመ ነው ሲልም ከሷል።

ክልሉ “በዚህ ዓይነት ታሪካዊ ስህተት ውስጥ መግባቱ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን አውቆ በአስቸኳይ እራሱን ማረም አለበት” ሲልም ከሷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ባወጣው መግለጫ ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዳይፈጸም የአማራ ክልል እክል ሆኗል ሲልም ወቅሷል።

አስተዳደሩ የፕሪቶሪያን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ለማድረግ ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ መሆኑን የገለጸው የትግራይ ካቢኔ መግለጫ “የአማራ ክልል መንግሥት ሆን ብሎ እክል እየፈጠረ ነው” ብሏል።

በትግራይ እና በአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ ለሚነሳባቸው አካባቢዎች በሕዝበ ውሳኔ ምላሽ ለመስጠት የፌደራል መንግሥቱ ፍላጎት እንዳለው ቢገልጽም ከሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም።