
25 መጋቢት 2024, 15:55 EAT
በናይጄሪያ በአንድ የተራድዖ ዝግጅት ላይ በተፈጠረ ግርግር አንዲት የስምነት ዓመት ሕፃንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ።
ዕለተ ሰንበት አንድ ባለሀብት በሰሜን ምሥራቅ የባውቺ ግዛት ነዋሪዎች ከመጡ ለእያንዳንዳቸው 5 ሺህ ናይራ [የናይጄሪያ ገንዘብ] ለመስጠት ቃል ገብቶ ነበር።
አምስት ሺህ ናይራ ወደ ዶላር ሲመነዘር 3 ዶላር ከ70 ሳንቲም ሲሆን፣ ወደ ብር ሲቀየር 210 ግድም ይሆናል።
የባለሀብቱን ጥሪ ተከተሎ በርካታ ሰዎች የወጡ ሲሆን፣ “ድንገት ሁሉም ነገር ተደበላለቀ” ይላል አንድ ታዳሚ ስለሁኔታው ለቢቢሲ ሲናገር።
የናይጄሪያ ምጣኔ ሀብት መላሸቁን ተከትሎ በርካቶች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።
አምስት ሺህ ናይራ አንድን ቤተሰብ ለአንድ ቀን መመገብ ይችላል።
በተፈጠረው ግርግር ምክንያት ዕድሜያቸው ከ8 እስከ 55 የሚሆን ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ ያረጋገጠ ቢሆንም፣ አንዳንድ ነዋሪዎች ግን የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው ይበልጣል ይላሉ።
ባለሥልጣናት የተፈጠረውን ነገር ለማጣራት ምርመራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለሀብቶች ታጣቂዎችን በገንዘብ ይደግፋሉ ሲሉ ወቀሱ25 መጋቢት 2024
- የአማራ ክልል በመጽሐፍት ላይ ያወጣውን ካርታ በአስቸኳይ እንዲያስተካክል የትግራይ ክልል አስጠነቀቀ25 መጋቢት 2024
- ዶናልድ ትራምፕ በሰዓታት ውስጥ 464 ሚሊዮን ዋስትና ካልከፈሉ ንብረታቸው ሊያዝባቸው ነው25 መጋቢት 2024
እንዲህ ባሉ ጥሬ ገንዘብ በሚታደልባቸው ዝግጅቶች ላይ ብዙውን ጊዜ የሚታደሙት ሴቶች ናቸው። ወንዶች ገንዘብ ሲቀበሉ መታየት ስለማይፈልጉ ሴቶችን ነው የሚልኳቸው።
በግርግሩ ታዳጊ ሴት ልጁ አይሻን ያጣው ባባንጊዳ አዳሙ “ልጄ እንዲህ ዓይነት ቦታ ስትመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” በማለት እንባ እየተናነቀው ተናግሯል።
ቢሮው አካባቢ ጥሬ ገንዘብ ልገሳ ያሰናዳው ባለሀብቱ አልሃጂ ያኩቡ ማይሻኑ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ባለሀብቱ ደሀ የሚባሉ የአካባቢው ሙስሊም ማኅበረሰብ አባላትን ሲረዳ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ናይጄሪያ ለእንደዚህ ዓይነት ዜና አዲስ አይደለችም።
ባለፈው ሳምንት በማዕከላዊ ናይጄሪያ የናሳራዋ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ሩዝ ሲታደል ለመቀበል የወጡ የተወሰኑ ተማሪዎች ተረጋግጠው መሞታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ወር ደግሞ የናይጄሪያ ገቢዎች አገልግሎት ሩዝ በቅናሽ ዋጋ ሲሸጥ በተፈጠረ ግርግር የተወሰኑ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አሳውቆ ነበር።
መንግሥት ከዚህ ቀደም ያደርግ የነበረውን የነዳጅ ደጎማ ማቆሙ ለኑሮ ውድነት አስተዋጽዖ ያደረገ ሲሆን፣ በርካቶች የሚቀበሉት ደመወዝ ከወር ወር ሊያደርሳቸው አልቻለም።