በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር

ከ 8 ሰአት በፊት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ውሳኔ አስተላለፈ። በውሳኔው ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ያልተጠቀመችው አሜሪካ በቀደመ አቋሟ አለመቀጠሏ ታይቷል።

ውሳኔው ታጋቾች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና በፍጥነት እንዲለቀቁም ጠይቋል።

መስከረም ማብቂያ ላይ ከተጀመረው ጦርነት በኋላ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲወሰን ይህ የመጀመሪያው ነው።

አሜሪካ ያሳየችው አቋም ከእስራኤል ጋር ያላትን ልዩነት እየሰፋ መምጣቱን ያሳየ ነው ተብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት አሜሪካ ቀደም ሲል የተኩስ አቁሙን ከታጋቾች መለቀቅ ጋር ያስቀመጠችበትን አቋም “የቀየረ” ብሎታል።

“በሚያሳዝን ሁኔታ አሜሪካ አዲሱን ሃሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ አላስቀረችውም” ብሏል።

ይህም ሐማስ ታጋቾችን ሳይለቅ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በእስራኤል ላይ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲፈጠር መንገድ በመጥረግ ታጋቾችን ለማስፈታት የሚደረገውን ጥረት ጎድቶታል ብሏል መግለጫው።

ኔታንያሁ በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን የእስራኤል ልዑካን እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሊያደርጉት የነበረውን ውይይት እንዲሰርዙ መገደዳቸውንም አስታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በበኩላቸው ታጋቾች በተያዙበት ሁኔታ እስራኤል በጋዛ ያለውን ጦርነት አታቆምም ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ተወካይ የሆኑት ሪያድ መንሱር የውሳኔ ሃሳቡን በደስታ ቢቀበሉትም “የዘገየ” ሲሉ ገልጸውታል።

“ይህ ምክር ቤት በመጨረሻ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለመጠየቅ ከ100 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን እስኪገደሉ እና የአካለ ጉዳት እስኪደርስባቸው፣ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት እስኪፈናቀሉ እና በረሃብ እስኪረግፉ ቆይቷል” ብለዋል።

ጋዛን የሚያስተዳድረው የፍልስጤሙ እስላማዊ ቡድን ሐማስ ውሳኔውን በደስታ ተቀብሏል። “ከሁለቱም ወገን እስረኞችን ወደ መፍታት የሚያመራ ፈጣን የእስረኞች ልውውጥ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ” ብሏል።

ቡድኑ ታጋቾችን ለመልቀቅ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን የሚፈቱበትን ሂደት በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጧል።

እስራኤል እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንድታግዝ አሜሪካ ጫና እያደረገች ነው

የፀጥታው ምክር ቤት ሰኞ ዕለት በሰጠው ድምፅ አሜሪካ ድምፀ ተአቅቦ ስታደርግ፣ የተቀሩት 14 አባላት ደግሞ ለውሳኔው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

አሜሪካ ቀደም ሲል የተኩስ አቁም የሚጠይቁ የውሳኔ ሃሳቦችን ስትሽር ቆይታለች። እንደ ምክንያት ስታቀርብ የነበረው ደግሞ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚደረግ ድርድር እና ታጋቾችን የመፈታት ውይይት በሚካሄድበት ወቅት ተገቢ አይደለም የሚል ነበር።

አሜሪካ ሐሙስ ዕለት የራሷን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረበች ሲሆን፣ በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ የተኩስ ማቆም ጥሪን ከታጋቾች መለቀቅ ጋር በማያያዝም ማቅረቧ በእስራኤል ላይ ጠንከር ያለ አቋም የያዘችበት ሆኖ ታይቷል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንዳሉት፣ አሜሪካ ውሳኔው እንዲጸድቅ መወሰኗ “የፖሊሲ ለውጥ ነው” ማለት አይደለም ብለዋል።

አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደምትደግፍ ገልጸው፤ የውሳኔ ሃሳቡ ሐማስን ስለማያወግዝ እንዳልደገፈችው ተናግረዋል።

ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫው የሰጡት ኪርቢ “ታጋቾችን ያካተተ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ድጋፍ ስንሰጥ ነበር። የታጋቾች ስምምነት የተዋቀረው በዚያ መልኩ ነው። ውሳኔው እየተካሄደ ላለውን ድርድርም እውቅና ይሰጣል።”

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የውሳኔ ሃሳቡ የተኩስ አቁምን ለማረጋገጥ እና “ታጋቾችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመፍታት” ተግባራዊ መሆን አለበት ብለዋል።

አሜሪካ ቀደም ሲል በምክር ቤቱ እስራኤልን ለመከላከል ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ስትጠቀም ቆይታለች ተብላ ስትከሰሰ ነበር።

ይሁን እንጂ በጋዛ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እስራኤል ላይ ያላት ትችት መጨመሩ ታውቋል። ከ32 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በእስራኤል ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል ሲል በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ጠቅላላው ሕዝብ በከፍተኛ የምግብ እጦት እየተሰቃየ ነው ከማለት ባለፈ አሜሪካ ወደ ጋዛ እርዳታ እንዲደርስ እስራኤል የበለጠ እንድትሠራ ጫና አድርጋለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል እርዳታ እንዳይደርስ እየከለከለች ነው ሲል ከሷል። እስራኤል በበኩሏ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ሥርጭቱን አላከናወነም ስትል ወቅሳለች።

የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ በዚህ ሳምንት መጨረሻ የልዑካን ቡድኗ ወደ ዋሽንግተን ሊያደርጉት ያቀዱትን ጉብኝት እስራኤል ለመሰረዝ ወስናለች።

ነገር ግን በእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት እና በአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሰሊቫን ለመገናኘት የያዙት ቀጠሮ በታቀደው መሠረት እንደሚቀጥል ኪርቢ ተናግረዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ “እስራኤል ሐማስን በምትዋጋበት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ከጎኗ መቆሟን እንደቀጠለች ለመከላከያ ሚኒስትሩ ግልጽ ለማድረግ እንጠባበቃለን” ብለዋል።