የክሬምሊን ፕሮፓጋንዳ አራማጅ ዲሚትሪ ኪሴልዮቭ

ከ 7 ሰአት በፊት

የሩሲያ የመንግሥት መገናና ብዙኃን የ137 ሰዎችን ሕይወት ለቀጠፈው ጥቃት ዩክሬን እና ምዕራባውያንን ተጠያቂ አደረጉ።

በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው ክሮከስ አዳራሽ የሮክ ሙዚቃ ለመታደም በተገኙ ሰዎች ላይ የተከፈተውን ተኩስም በምዕራባውያኑ እንደተቀነባበረ በክሬምሊን የተነገረውን መገናኛ ብዙኃኑ አጽንኦት ሰጥተው ዘግበዋል።

ዩክሬን በጥቃቱ ላይ ምንም ተሳትፎ የለኝም ስትል አስተባብላለች።

ኤንቲቪ የተሰኘው የሩሲያ የመንግሥት ሚዲያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) የተቀነባበረ የሚመስለውን የዩክሬን ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን ኦሌክሲ ዳኒሎቭን ስለ ጥቃቱ አሉ የተባለውን ንግግር አሰራጭቷል።

ይህ ቪዲዮ ጥቃቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በሩሲያ ከፍተኛ ተደማጭነት ካላቸው አንዱ በሆነው በዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ታይቷል።

ዳኒሎቭ “ዛሬ በሞስኮ አስደሳች ቀን ነው። እንዲህ ዓይነቱን አስደሳች ሁኔታዎች ከዚህ በኋላ እንደምናዘጋጅላቸው ልነግራችሁ እፈልጋለሁ” ሲሉም ይሰማል።

ነገር ግን በቢቢሲ ግኝት መሠረት ቪዲዮው ባለፈው ሳምንት የተሰጡ ሁለት የተለያዩ ቃለ መጠይቆችን በማጣመር የተቀነባበረ ሲሆን፣ በቪዲዮው የሚሰማውም ድምፅም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም የተሠራ ሊሆን እንደሚችልም አረጋግጧል።

የሩሲያ የቴሌቪዥን አቅራቢዎች እና ታዋቂ የክሬምሊን ጦማሪዎች ከሞስኮው ጥቃት ጀርባ የእስላማዊ መንግሥት ቡድን (አይኤስ) አለ መባሉን በጥርጣሬ ከመዘገብም በተጨማሪ ይህንንም የምዕራባውን ትርክት ብለውታል።

“ሁሉም ሰው የተሳሳተ ፍንጭ እንዲያሳድድ ለማድረግ ቀድሞውንም ቢሆን ሙከራዎች አሉ” ሲልም ታዋቂው ተንታኝ እና የክሬምሊን ፕሮፓጋንዳ አራማጅ ዲሚትሪ ኪሴልዮቭ በዜናዎች ግምገማው አስተያየቱን ሰጥቷል።

“አይኤስ የተለየ መለያዎች አሉት። በአይኤስ ስም የሚፈጸሙ የሽብር ተግባሮች የሚፈጸመው በአጥፍቶ ጠፊዎች ነው፤ ከዚያ በኋላም ለመሸሽ አይሞክሩም” ሲልም ተናግሯል።

“አሸባሪዎቹ ጥቃቱን ከፈጸሙ በኋላ መጠለያም ለመፈለግ ያቀኑት ወደ ዩክሬን መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው” ብሏል።

እነዚህ አስተያየቶች እየተሰጡ ያሉት የእስላማዊ መንግሥት ቡድን (አይኤስ) ለጥቃቱ ኃላፊነቱን በወሰደበት ሁኔታ ነው። ቡድኑ የጥቃቱን ቪዲዮም ይፋ ያደረገ ሲሆን ቢቢሲም የተንቀሳቃሽ ምስሉን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ችሏል።

“ይህ ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን ጥቃቱን ለመፈጸም ለምን እንደወሰነ ግልጽ አይደለም። የአሜሪካ ባለሙያዎች እየሰጡ ያለው አስተያየት የተጠና ይመስላል” ሲልም ቻናል ዋን የተሰኘው የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።

የራሺያ ቱደይ ዋና አዘጋጅ ማርጋሪታ ሲሞንያም ተመሳሳይ አስተያየቶችን ሰጥታለች።

“አጥቂዎቹ የሻሂድ ቀበቶዎች (የፈንጂ ቀበቶዎች) አልታጠቁም። አንዳቸውም አልሞቱም፣ አክራሪ ሃይማኖተኞችም አልነበሩም። አይሲስ ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢም ዝር አላለም” ስትልም በቴሌግራም ገጿ ላይ አስፍራለች።

ለጥቃቱ ዩክሬን እና ምዕራባውያንን ተጠያቂ ያደረጉ ሌሎች ዘገባዎችም በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርበዋል።

የመንግሥት ጋዜጣ የሆነው ሮሲይካያ አጥቂዎቹ ያነገቡት መሳሪያ ቢጫ እና አረንጓዴ ቀለማት ያሉት ሲሆን፣ “የሩሲያ ወዶ ገብ ተዋጊዎች ከሚጠቀሙበት ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው” ሲል አስነብቧል።

ቡድኑ ከዩክሬን ጎን ሆኖ የሚዋጉ ሩሲያውያንን የያዘ ነው። የኮሚኒስት ፓርቲ መሪ ጀኔዲ ዚያጋኖቭ በበኩላቸው “እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙዎቻችን የአንግሎ ሳክሰንስ አገራት ጥምር የሆነው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሩሲያን ለማጥፋት ያወጁት ጦርነት መሆኑን ሙሉ በሙሉ አልተገነዘብንም” ብለዋል።

“ይህ አጸያፊ አረመኔያዊ የሽብር ጥቃት ለዚህ ማስረጃ ነው” ያሉት ኃላፊ የ9/11 የአሜሪካ የሽብር ጥቃትንም ራሷ እንዳቀነባበረች የሚወራውን የሴራ ጽንሰ ሃሳብ ደግመውታል።